Popular Posts

Tuesday, March 14, 2017

የባለጠጋው ችግሩ

ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። ሉቃስ 16፡19-23
ይህንን ፅሁፍ ስናነብ የባለጠግነች ችግሩ ምንድነው ልንል እንችላለን፡፡ ባለጠግነቱ ምንም ችግር የለበትም፡፡ ይህም ሰው ምንም የተገለፀ ችግር አናይበትም፡፡ የደሃውን ገንዘብ አልቀማም፡፡ ታክስ አላጭበረበረም፡፡ ጉቦ ተቀብሎ ማግኘት ያለበትን አልከለከለም ፣ አለማግኘት ያለበትን አልሰጠም፡፡ ባለጠጋው ሰው ድርጊቱ ያደረገው ስህተት የለም፡፡   
ባለጠግነት ተሰርቶ ተጠራቅሞ በትክክለኛው መንገድ ይምጣ እንጂ ምንም ችግር የለበትም፡፡ እውነተኛ ባለጠግነት የእግዚአብሄር ስጦታ ስለሆነ ምንም የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ አሁንም ታዲያ የባለጠጋው ሰው ችግሩ ምንድነው ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡
ሰው ለድሃ ምፅዋት በመስጠቱ ወደመንግስተ ሰማያት ይገባል ብሎ መኝሃፍ ቅዱስ አያስተምርም፡፡ ምክኒያቱም የሃጢያተኛ ሰው ምንም አይነት መልካም ምግባር እግዚአብሄርን ሊያስደስተው አይችልም፡፡ ሃጢያተኛ የሚያደርገው የተሻለው መልካም ነገር በእግዚአብሄር ፊት እንደመርገም ጨርቅ ነው፡፡
ሰው ወደ መንግስተማያት የሚገባው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሃጢያ ዋጋ እንደተከፈለለት በእምነት ሲቀበል ብቻ ነው፡፡ ሰው የሚድነው በኢየሱስ ስራ ላይ ሲደገፍ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ያረካው ስራ የኢየሱስ የመስቀል ስራ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታ የሚቀበለውን ሰው እግዚአብሄር ይቀበለዋል፡፡   
ስለዚህ ሃብታሙ ወደ መንግስተ ሰማይ ያልገባው መልካም ስራ ስላልሰራ አይደለም፡፡ ሰው በኢየሱስ የመስቀል ስራ በማመን እንጂ በመልካም ምግባር ወደ መንግስት ሰማያት አይገባምና፡፡ ሰው ንስሃ ገብቶእግዚአብሄር ለመዳኛ ያዘጋጀውንም ልጁን ኢየሱስን መቀበል አለበት፡፡
የሃብታሙ ሰው ችግር ምን እንደነበር ማወቅ በእኛም ህይወት ከስህተቱ እንድንማር ይረዳናል፡፡
የሃብታሙ ሰው ችግር የሰብአዊነት ስሜት ማጣት ነው፡፡ የሃብታሙ ሰው ችግር የፍትህ ችግር ነው፡፡ የሃብታሙ ሰው ችግር ሰውን እንደሰውነቱ ያለማክበር ችግር ነው፡፡ የሃብታሙ ሰው ችግር ሌላውን ሰው እንደሰው አለመቁጠር ችግር ነው፡፡
እርሱ ሃብታም ነው ሁሉ ሞልቶለታል፡፡ ይህ ደሃ ደግሞ ተቸግሮዋል፡፡ ተጨንቋል ታሟል፡፡ በሃገራችን ኢትዮጲያ ሰሞኑን የደረሰው አደጋ ይህንን የድህነት ጩኸት ያስታውሰናል፡፡ ልባችን አዝኖዋል፡፡ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን   
ይህ ባለጠጋ ሰው ድሃውን ተቸግሮ ያየዋል፡፡ ቢያየውም አልደነገጠም ምንም ሊያደርግለት አልፈለገም፡፡ እንደሰው አልተመለከተውም፡፡ እንደሌላው የእግዚአብሄር ፍጥረት አላየውም፡፡ እርሱም ምግብ እንደሚገባው አላሰበም፡፡ ራሱን ብቻ የተመረቀ ኮከብ እድርጎ ነበር የሚያየው፡፡ ደሃው ደግሞ እንደረተረገመ የተሻለ ኑሮ እንደማይገባው ነገር የሚያየው፡፡ ሃብታሙ ሰው ትሁት አልነበረም፡፡ ሃብታሙ ሰው ለሌላው ግድ የሚለው አልነበረም፡፡ ሃብታሙ ሰው ለሌላው የሚያዝንን የሚራራ ልብ አልነበረውም፡፡ ይህ ባለጠጋ ከዚህ ደሃ ጋር ራሱን አላስተባበረም፡፡ ይህ ባለጠጋ ከዚህ ደሃ ጋር ሊሆን እልፈለገም፡፡
የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ሮሜ 12፡16
ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። (መደበኛው ትርጉም)
ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው። ያዕቆብ 1፡27
ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤ መዝሙር 82፡3
እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? ኢሳያስ 58፡7
ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤ እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤ ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥ ኢዮብ 31፡16-19
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #መስጠት #ድሃ #ምፅዋት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 


No comments:

Post a Comment