ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
እግዚአብሄር እኛን የፈጠረው በአላማ ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር እኛን ከመፍጠሩ በፊት በምድር ላይ ምን እንድምናደርግ አላማውና እቅዱ ነበረው፡፡ በምድር ላይ ድንገት አልተፈጠርንም፡፡ እግዚአብሄር ከፈጠረን በኋላ አይደለም አሁን ምን ላድርጋቸው ብሎ ያሰበው፡፡ የተፈጠርንለት ልዩ የሆነ አላማ አለን፡፡ ዲዛይን የተደረግነውና የተፈጠርነው ስለዚያ ልዩ አላማ ነው፡፡
የተፈጠርንለትን ያንን አላማ በትጋት እግዚአብሄር እየሰራበት ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወት ንድፋችን ዝርዝር አፈፃፀም ላይ ዘወትር እየሰራበት ነው፡፡
እግዚአብሄር የህይወት እቅዳችንን የሚሰራው የፀሎት ጥያቄያችንን ሰብስቦና ቀጣጥሎ አይደለም፡፡ ወደምድር ከምምጣታችን በፊት እንድንፈፅመው አስቀድሞ የተዘጋጀ መልካም ስራ አለ፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠርን የህይወት እቅዳችንን ከእግዚአብሄር ተቀብለን በዚያ ላይ መስራት ብቻ ነው እውነተኛ ስኬታማ የሚያደርገን፡፡
ስለዚህ ነው ይህንን እግዚአብሄር ለእኛ ያሰበውን ሃሳብ ለማወቅ እግዚአብሄርን መፈለግ ያለብን፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ ማለት ጥበብ ነው፡፡ በአካሄዳችን ሁሉ በፍፁም ልባችን እግዚአብሄርን መፈለግ ፍሬያማ ያደርገናል፡፡
እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርምያስ 29፡12-13
እግዚአብሄርን ፈልገን መቀበል ያለብን እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበው ሃሳብ መልካም ሃሳብ ነው፡፡ እግዚአብሄር መልካም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የማይለወጥ ሁለንተናው መልካመ የሆነ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሃሳብ ለእኛ ሁልጊዜ መልካም ነው፡፡
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ 2፡4
ወደ እግዚአብሄር ፀልየን መረዳት ያለብን እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ሃሳብ ፍፃሜና ተስፋ ያለው ነው፡፡ እግዚአብሄር የመጨረሻውን ከመጀመሪያ ያያል፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ያለው የፍፃሜ እቅድ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሃሳብ መጨረሻው የያማረ ነው፡፡ በህይወት ወደፊታችንና ፍፃሜያችን እንዲያምር እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ ከመፈልግ ውጭ አስተማማኝ መንገድ የለም፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበው ሃሳብ 100% አስተማማኝ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ ስንከተል በህይወታችን ሰላምን ማጣጣም እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበው ሃሳብ በጥቅሉ ሙሉ እና ምንም የሚጎድለው ነገር የሌለ በመሆኑ እውነተኛ እርካታን የምናገኘው ያንን ሃሳብ ስንከተል ብቻ ነው፡፡ እውነተኛ እርካታና የሚገኘው እቅዳችንን አምጥተን እግዚአብሄን ለማስፈለም ሳይሆን እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ በማግኘትና በመከተል ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተሰፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment