የሰይጣን አላማ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ከመጣ ከእነዚህ አላማዎች ውጭ ስለሌለ ስለምንም አላማ አይመጣም፡፡ ሰይጣን ሃሳቡን የሚያስፈፅምለት ሰው ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን ይህንን የሚያደርገው ደረጃ በደረጃ ነው፡፡
ሰይጣን አላማውን በሰዎች ተጠቅሞ ያስፈፅማል፡፡ ሰይጣን ሰዎችን በዋነኝነት የሚያጠቃውና የመስረቅ የማረድና የማጥፋት አላማውን በእነርሱም ይሁን በሌላ ሰው ህይወት ላይ የሚያሳካው በሃሳብ ነው፡፡ ሰይጣን የሰዎችን ህይወት ለመስረቅ በስፋት የሚጠቀመው ሃሳብን በመላክ ነው፡፡ ሰይጣን ወደ አእምሮዋችን እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነን ሃሳብ በመላክ ህይወታችንን ሊሰርቅ ይችላል፡፡ ሰይጣን ክፉና ሃሳብን ወደሰዎች አእምሮ በመላክ ብቻ የአላማው ማስፈፀሚያ ያደርጋቸዋል፡፡
ሰይጣን በክርስቶስ የመስቀል ስራ ሙሉ ለሙሉ የተሸነፈ ስለሆነ በተለይ እኛ ኢየሱስን የምንከተል የሚዋጋበት ዋነኛው መንገድ ክፉ ሃሳብን ወደ አእምሮዋችን በመላክ ነው፡፡
ሰይጣን ሃሳብን ልኮ አእምሮዋችንን ካበላሸ መንገዳችንን ያበላሻል፡፡ ህይወታችን የምንጠብቀው ሃሳባችንን በመጠበቅ ነው፡፡ ሃሳቡን መጠበቅ የቻለ ሰው ህይወቱን ጠብቋል፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡2-3
ሰውን የሚያረክሰው ከመንገዱ የሚያሰናክለው ክፉ ሃሳብ ነው፡፡ ሰው በልቡ የሰይጣንን ሃሳብ ካስተናገደ ክፋት ሁሉ የሚወጣው ከልብ ሃሳብ ነው፡፡ ሰይጣን በልባችን ላይ ክፉ ሃሳብ ማስቀመጥ ካልቻለ ክፋትን ሊያሰራን አይችልም፡፡
ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ማቴዎስ 15፡18-19
አእምሮዋችን ከዳነ እኛ እንድናለን፡፡ አእምሮዋችን ካልዳነ ሰይጣን በህይወታችን እድል ፈንታን ያገኛል፡፡ አእምሮዋችን የሚድነውና ከሰይጣን ጥቃት የሚጠበቀው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21
ልባችንን ከጠበቅን ህወታችንን እንጠብቃለን፡፡ ልባችን ለሰይጣን ጥቃት ከተጋለጠ ህይወታቸን ለሰይጣን ጥቃት ይጋለጣል በዚያም ሰይጣን አለላማውን መስረቅ ማረድና ማጥፋት በህይወታችን እንዲፈፅም እንፈቅድለታለን፡፡ ልባችንን በትጋት በእግዚአብሄ ቃል ካልጠበቅን ህይወታችን ለአደጋ ይጋለጣል፡፡
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። ምሳሌ 4፡23
በእግዚአብሄር ቃል ላይ መደገፍ የሚያስፈልገን ሰይጣን ህይወታችንን እንዳያጠፋ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ላይ እምነት የሚያስፈልገን በህይወታችን ላይ የሚላኩትን የሚንበለበሉትን የጠላት ጥቃቶች ለመቋቋም ነው፡፡
በሰው ህይወት ላይ ሰይጣን መግባትን የሚያገኘው በሃሳቡ ከተታለለ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ያላታለለው ሰው ህይወት ውስጥ የመግባትና የማጥፋት መንገድ አያገኝም፡፡
የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ ኤፌሶን 6፡11፣16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#አተረፈ #ንፅህና #ሃሳብ #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ስብከት #እምነት #ነፃነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment