Popular Posts

Follow by Email

Thursday, March 2, 2017

ፍቅር - ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ

ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡31
ከስጦታዎች ሁሉ የሚበልጠው ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ከፍ ያለ ነው፡፡ ፍቅር ተራ አይደለም፡፡ ፍቅር በውድቀት መደዳ አይገኝም፡፡ ፍቅር አሸናፊ ነው፡፡ ፍቅር ስኬታማ ነው፡፡
ፍቅር የሚበልጥበት ምክኒያት ፡-
1.      ምንም ምግባር ከፍቅር መነሻ ሃሳብ ካልተደረገ ከንቱ ነው፡፡ ሰው ምንም ያህል ስጦታ ቢኖረው ስጦታውን የሚተገብረው በፍቅር ካልሆነ ከንቱ ነው፡፡ ሰው ምንም ነገር ቢያከናውን ያከናወነው ከፍቅር ልብ ካልሆነ ምንም አይጠቅምም፡፡  
በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1 ቆሮንቶስ 13፡1-3
2.     ፍቅር የህግ ፍፃሜ ነው፡፡
ሰው የተፈጠረው ለፍቅር ነው፡፡ በፍቅር የሚኖር ሰው ህግን ይፈፅመዋል፡፡ በፍቅር የሚኖር ሰው ሌላውን ሊበድል አይችልም፡፡ ሰው በፍቅር ኖሮ አላማውን ሊስት አይችልም፡፡
አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። ሮሜ 13፡9-10
3.     እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የእግዚአብሄር መንገድ ነው፡፡ በፍቅር መኖር እግዚአብሄርን መምሰል ነው፡፡ ለእግዚአብሄር የምናደርገው ነገር ሁሉ በፍቅር ካልተደረገ ለእግዚአብሄር አልተደረገም፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16
4.     የእግዚአብሄር ትእዛዞች ሁሉ የተሰጡበት አላማ ሰው በፍቅር እንዲኖር ለማስቻል ነው፡፡
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡5
5.     በፍቅር ላይ የሚሰራ ህግ የለም፡፡ ፍቅር ፍፁም ነው፡፡ ፍቅር የሚወጣለት አንከን የለም፡፡ ለምን ለሰው መልካም አሰብክ ፣ ለምን ለሰው መልካም ተናገርክ ፣ ለምን ለሰው መልካም አደረግክ ተብሎ የሚቀጣ ሰው የለም፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። ገላትያ 5፡22-23
6.    ፍቅርን እግዚአብሄር ብቻ የሚያደርገው ስለሆነ ነው፡፡ ሌሎች ነገሮች መስሎ የተሰራ ማታለያ አላቸው፡፡ ፍቅርን ግን ማስመሰያውን መስራት የሚችል ሰው የለም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ካልሆነ በፍቅር ሊኖር አይችልም፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ካልተቀበለው በፍቅር ሊኖር የሚችልበት አቅም የለውም፡፡  
በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ሮሜ 5፡5
7.     ፍቅርን ሲያየው የማያውቀው ሰው የለም፡፡ የመጨረሻው እውቀት የሌለው ሰው ፍቅርን ያውቀዋል፡፡ ምንም የማይረዳ የሚባለው ሰው ፍቅርን ግን አይስተውም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስን አንብቦ የማያውቅ ሰው እንኳን ፍቅርን መረዳት ይችላል፡፡
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። ዮሃንስ 13፡35
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #መውደድ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment