Popular Posts

Saturday, October 6, 2018

እግዚአብሄር ልብን ይመዝናል


የፈጠረን እግዚአብሄር ሁለንተናችንን ያውቃል፡፡
እግዚአብሄር በውጫዊ ነገራችን አይወሰድም፡፡ እግዚአብሄር ፊትን አያየም፡፡ እግዚአብሄር የፊትን መልክ አይቶ አይሳብም፡፡ እግዚአብሄር ቁመናችንን አይቶ አይደነቅም፡፡
የአነጋገራችን አንደበተ ርእቱነት የልባችንን ሁኔታ አይሸፍንበትም፡፡
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። መጽሐፈ ምሳሌ 23፡6-7
የውጭው ፈገግታችን የልባችንን ሁኔታ ከሰው ሊከልል ይችላል እንጂ ከእግዚአብሄር አይከልልም፡፡ ሰውንም ያታልል ይሆናል እንጂ እግዚአብሄርን አያታልልም፡፡  
እግዚአብሄር የሰውን አለባበስ አይቶ አያከብርም፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ልብ ያከብራል፡፡ እግዚአብሄር ሰውን አይቶ አይንቅም፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ልብ አይቶ ይንቃል፡፡
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡7
ልብሳቸውን አነጋገራቸውንና የውጭው ነገራቸውን ብቻ ያሳምሩ የነበሩትን ፈሪሳዊያን ኢየሱስ ልባቸው ክፉ እንደነበር ንስሃ ካልገቡ መጨረሻቸው ጥፋት እንደሚሆን ያስጠነቅቃቸው ነበር፡፡
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 23፡25፣28
እግዚአብሄር ልብን ያያል፡፡ ለልብሳችን ከምናደርገው ጥንቃቄ በላይ ለልባችን እንጠንቀቅ፡፡ ለውጭ ነገር መጠንቀቅ ለጥቂት ይጠቅማል፡፡ ለልብ መጠንቀቅ ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል፡፡
ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡8
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡4
ከማንኛውም ነገር በላይ ንፅህናውን ማጣቱ ከፍተኛ አደጋ ያለው ልብ ነው፡፡ አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ስለዚህ ነው፡፡
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። መጽሐፈ ምሳሌ 4፡23
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ውበት #ቁንጅና #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment