Popular Posts

Monday, October 15, 2018

ሰዎችን የምንቆጣጠርበት ስድስት መንገዶች



እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር እሺ እና እምቢ የሚልበት የራሱ ነፃ ፈቃድ እንዳለው ሁሉ ሰውን ነፃ ፈቃድ አለው፡፡ ሰው ፈቃዱን ተጠቅሞ ሊያምፅበት እንደሚችል ቢያውቅም እግዚአብሄር በቸርነቱ ሰውን ነጻ ፈቃድ ያለው አድርጎ ፈጠረው፡፡ ሰው ፈቃዱን ተጠቅሞ ሃጢያት ቢሰራም እንኳን እግዚአብሄር የሰውን ነጻ ፈቃድ አልነጠቀውም፡፡ የሰውን ነፃ ፈቃድ መግፋት የእግዚአብሄርን አሰራር መጋፋት ነው፡፡
የእግዚአብሄር መንፈስ ይመክራል እንጂ አይጫንም፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ ይመራል እንጂ አይነዳም፡፡ የእግዚአብሄር መንፈስ ፈቃዳችንን እንድንሰጠው ይጠይቃል እንጂ በርግዶ አይገባም፡፡
ነገር ግን የሰው ስጋዊ ፍላጎት እንደዚግህ አይደለም፡፡ የሰው ስጋዊ ፍላጎት ሌላውን ሰው መቆጣጠር እና ሁኔታዎችን መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ማመንና መጠበቅ ለስጋ የማይመቸው ነገር ነው፡፡ ለስጋ በእግዚአብሄር ጊዜ መተማን አይሆንለትም፡፡ ስጋ በራሱ ጉልበት ይተማመናል፡፡ ፡፡  
ስጋ ለሌሎች ነጻነትን መስጠት አይፈልግም፡፡ ስጋ ሌሎችን መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ስጋ ሌሎችን ካለአግባብ የሚቆጣጠርበትን መንገዶች ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡   
1.      ውሸት
ሰው እውነትን ማወቅ መብቱ ነው፡፡ ሰው በህይወቱ ላይ ትክክለኛውን ውሳኔ ለመወሰን እውነት ያስፈልገዋል፡፡ ነፃ የሚያወጣው እውነት ነው፡፡ እውነትን መደበቅ ሰውን በእስራት ውስጥ ማቆየት ነው፡፡ እውነትን መደበቅና ውሸትን እንደ እውነት አድርጎ ማቅረብ የስጋ የመቆጣጠሪያ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ውሸትን መናገር የሰውን ህይወት እኛ ወደምንፈልግው አቅጣጫ ለመመራት የምናደርገው የራስ ወዳድነት ስጋዊ ድርጊት ነው፡፡
ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡25
2.     ክርክር
የምናውቀውን እውቀት ለሰው ማካፈል ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ሰውን በግድ ለማሳመን መሞከር ሰውን የምንቆጣርነት የስጋ ስራ ነው፡፡ ስጋ በሚናገረው ቃል አይተማመንም፡፡ ስጋ የሚታመነው በጉልበቱ ነው፡፡ ስጋ በባህሪው አይተማነምንም፡፡ ስጋ የሚተማመነው በጉልበት ነው፡፡ ስጋ በመተማመን አያምንም ስጋ የሚያምነው በማስገደድ ነው፡፡ ስጋ የሌላውን ጥቅም ስለማይፈልግ ያለው አንድ አማራጭ ጉልበትን ተጠቀሞ ማስገደድ ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ ነው መንፈሳዊ መሪ ስጋዊ የሰዎችን ፈቃድ የሚያከብር ትሁትና የማይከራከር የግሉን ፍላጎት ሰዎች ላይ በግድ የማይጭን ሊሆን እንደሚገባው የሚመክረው፡፡
የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 1 ወደ ጢሞቴዎስ 3፡3
3.     ስድብ
ስድብ ሌላውን ሰው ዝቅ ማድረግ በው፡፡ ስጋ እርሱ ከፍ እንዲል ሌሎች ሰዎች ዝቅ ማለት ያለባቸው ይመሰለዋል፡፡ ስድብ ሌላውን ማዋረድ ነው፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1 የጴጥሮስ መልእክት 39
4.     ቁጣ
ቁጣ ድምፅን ከፍ በማድረግ ሌላው ላይ ክፉ ተፅእኖ ማድረግ ነው፡፡ ሰው ማደረግ ባይፈልግም በቁጣችን ደንግጦ የማይፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ማስገደድ ክፋት ነው፡፡  
አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ ወደ ቆላስይስ ሰዎች 38
5.     ምሬት እና ይቅር አለማለት
ሌላው ሰውን ያለአግባብ ለመቆጣጠር የምንፈልግበት መንገድ ምሬትና ይቅር አለማለት ነው፡፡ የበደለንን ሰው አለመልቀቅ የበደለን ሰው እንዳይከናወንለት መመኘት የበደለን ሰው እንዳይሳካለት ማሰብና መናገር ሌላኛው ሌላውን ሰው የምንቆጣጠርበት ክፉ መንገድ ነው፡፡ ይቅር ማለት ሰውን መልቀቅና መተው ለስጋ አርነት አለመስጠት ነው፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡13
6.     መሃላ
መሃላ በንግግር ብዛት ሰው የማይፈልገውን ነገር እንዲያደርግ የማስገደጃ የስጋ ጥበብ ነው፡፡ መሃላ ነገርን ሃይማኖታዊ በማስመሰል ሊያምነን ያልፈለገው ሰው እንዲያምንን የምንጫንበት ክፉ የስጋ መንገድ ነው፡፡
እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። የማቴዎስ ወንጌል 5፡34-37
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ውሸት #ሀሰት #ምሬት #ይቅርአለማለት #ቁጣ #መሃላ #ክርክር #ስድብ #ቁጣ #ውሸት ##ሰይጣን #ዲያቢሎስ #ጠላት #ማታለል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment