Popular Posts

Tuesday, October 9, 2018

ባሪያህ ይሰማልና ተናገር


እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም፦ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፦ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3፡10
ብዙ ሰዎች እነርሱ የሚፈልጉትን ለእግዚአብሄር ለመናገር ቅርብ ናቸው፡፡ ለእግዚአብሄር መናገር የሚያስፈልግበት ጊዜ ቢኖረም ነገር ግን ለመስማት መቅረብ ብዙ ጊዜ አትራፊ ያደርገናል፡፡  
ብዙ ሰዎች እግዚአብሄር ከእነርሱ በላይ ለእነርሱ የሚያስብ አባት መሆኑን በማወቅ ለመስማት አይቀርቡም፡፡  
ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። መጽሐፈ መክብብ 5:1
በእግዚአብሄር ፊት ለመስማት አለመቅረብን የመሰለ ሞኝነት የለም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ለመስማት አለመቅረብን የመሰለ ብክነት የለም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ለመስማት አለመቅረብ ክፋት ነው፡፡  
ብዙ ሰዎች እነርሱ ለራሳቸው ካላሰቡ እግዚአብሄር ለእነርሱ እንደማያስብ ስለሚመስላቸው ለመስማት አይቀርቡም፡፡ ብዙ ሰዎች እግዚአብሄርን የሚያዩት ለእነርሱ ሃሳብ እንደሌለውና እነርሱ ሃሳብ ካልሰጡት በስተቀር እንደማያስብ ራእይ እንደጎደለው ሰው ስለሆነ ብዙ ጊዜ ለመስማት ሲቀርቡ አይታዩም፡፡ ብዙ ሰዎች እግዚአብሄርን የሚያዩት በሃሳብ እንደሚረዱትና እንደሚያስታውሱት ሰው ፍጡር ስለሆነ ለመስማት አይቀርቡም፡፡  
እግዚአብሄር ለእኛ ያስባል፡፡ ለእኛ በማሰብ እግዚአብሄርን ማንም አይቀድመውም፡፡ እኛ እንኳን እግዚአብሄር ለእኛ እንደሚያስብው ለራሳችን አናስብም፡፡ ከእግዚአብሄር ሃሳቢነት አንፃር እኛ እንኳን ለእራሳችን አናስብም፡፡ ከእግዚአብሄር ፍፁም በጎ አሳቢነት አንፃር እኛ እንኳን ክፉ አሳቢዎች ነን፡፡
እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? የማቴዎስ ወንጌል 7፡11
እግዚአብሄር የእኛን የህይወት እቅድ አስቀድሞ አውጥቶ ጨርሷል፡፡ በምድር ላይ የተፈጠርነው እንድንሰራው የታቀደ የህይወት አላማ ስላለን ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11
ወደእርሱ የምንፀልየው ለእግዚአብሄር ሃሳብ ልንሰጠው አይደለም፡፡ የምንፀልየው የእርሱን ሃሳብ ለመካፈል ነው፡፡ የምንፀልየው ልናማክረው አይደለም፡፡ የምንፀልየው ሊመክረን ነው፡፡ የምንፀልየው ልንነግረው አይደለም፡፡ የምንፀልየው ልንሰማው ነው፡፡
የፀሎት ዋናው ከፍል ባሪያህ ይነግርሃልና ስማ ሳይሆን ባሪያህ ይሰማሃልና ተናገር ነው፡፡
የምንፀልየው እኛ የምንፈልገውን ለመስማት ነው የምንፀልየው ወይስ እርሱ የሚናገረውን ለመስማት ነው?
እርሱ የሚናገረውን ለማድረግ እናምነዋለን ወይስ እኛ የምንናገረውን እንዲያድግ ነው የምናምነው?
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 16፡25
ስለህይወታችን አምነነው እርሱ የሚናገረውን ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይስ እኛ የምንናገረውን እንዲያደግ ብቻ ነው የምንፈልገው?
እግዚአብሄር እኔን ላከኝ የምትፈልገውን አደርጋለሁ የሚል ለመስማት እና ለማድረግ የተዘጋጀን ሰው ይፈልጋል፡፡ ለመስማት እና ለማድረግ የተዘጋጀ ሰው እግዚአብሄርን ሲጣራ ይሰማል፡፡
የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። ትንቢተ ኢሳይያስ 6፡8
እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም፦ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፦ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3፡10
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ምሪት #ጆሮ #ትህትና #ቃል #ድምፅ #አእምሮ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #መታዝዝ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment