የትዕቢትን
ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16
ዝቅተኛ
ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16 (አዲሱ
መደበኛ ትርጉም)
የሰው እውቀት የሚለካው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያሉትን
ሰዎች እንዴት እንደሚይዝ በማወቁ ነው፡፡ የሰው ሃያልነት የሚለካው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሚይዝበት የጥንቃቄ አያያዝ
መጠን ነው፡፡ የሰው ባለጠግነት የሚለካው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ባለው የአክብሮት ግንኙነት ነው፡፡
እውነተኛ እውቀት ያለው ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ
ካሉ ሰዎች ጋር አብሮ ለመሆን አይፈራም፡፡ እውነተኛ ሃያል ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ጋር አብሮ በመሆኑ ይቀንስብኛል ብሎ
የሚፈራው ምንም ነገር የለም፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ ለመሆን ይደፍራል፡፡
የእውነት እውቀት የሌለው ሰው ግን ዝቅተኛ ኑሮ
ውስጥ ካሉ ጋር መታየት አይፈልግም፡፡ ሃያል እንደሆነ በራሱ የማይተማመን ሰው ግን ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ጋር አብሮ መሆኑ ሃያልነቱ
የሚቀንስበት ይመስለዋል፡፡ ባለጠጋ እንደሆነ እርግጠኛ ያልሆነ ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ጋር አብሮ መሆኑን የሰዎቹ ዝቅተኛ ኑሮ
ይጋባብኛል ብሎ ስለሚፈራ አይደፍርም፡፡
እውነተኛ እውቀት የሌለው ሰው ሁሉ ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ መሆኑ
ከፍተዕነት ስሜት እንዲሰማው ደርገዋል፡፡ ደካማ የሆነ ሰው የሃላልነት ስሜቱን የሚገኘው ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች አካባቢ በመሆን
ነው፡፡ የአእምሮ ደሃ ሰው በራሱ ባለጠግነት ስለማይተማመን ባለጠጋ እንዶሆነ ራሰን የሚያታልለው ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች ዙሪያ
በመሆን ነው፡፡
እውነተኛ ባለጠጋ ድህነትን አይፈራም፡፡ ድህነትን እንዳይመጣበት የሚፈራና የሚሰግድለት
ሰው ድሃ እንዳይሆን ምንም ክፉ ነገርን ከመስራት አይመለስም፡፡
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት
ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡10
እውነተኛ እውቀት ያለው ሰው የሰውን ስኬት በሰውነቱ እንጂ በኑሮ ከፍታና ዝቅታ
አይለካም፡፡ እውነተኛ ሃያል የሰው ሃያልነት በሰውነት እንጂ ባለው ቁሳቁስ እንደሆነ አያምንም፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ሰው ባለጠግነት
ሰውነት እንጂ የኑሮ ከፍተኝነት እና ዝቅተኝነት እንዳልሆነ ይረዳል፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም
ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? የያዕቆብ መልእክት 2፡5
እውነተኛ እውቀት ያለው ሰው ከፍ ባለ ቁጥር ራሱን ያዋርዳል፡፡ እውነተኛ ሃያል
ሰው እርሱ ብቻ እድለኛና ተወንጫፊ ኮከብ ስለሆነ ሳይሆን ማንም ሃያል ሊሆን እንደሚችል በሰው ያምናል፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ሰው
ሁሉም ሰው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ባለጠጋ እንደሆነ ስለሚያውቅ ራሱን ያዋርዳል፡፡ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ሰዎች የሚጠላና ዝቀተኛ
ኑሮዋቸው ይተላለፍብኛል ብሎ ከእነርሱ ጋር መታየትም ሆነ አብሮ መሆን የማይፈል ሰው የአእምሮ ደሃ ነው፡፡
የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ
ያልፋልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡9-10
እውነተኛ አዋቂ የእግዚአብሄር እርዳታ እንጂ እውቀቱ ምንም እንደማያመጣ የተረዳ
ሰው ነው፡፡ እውነተኛ ሃያል ሰው እግዚአብሄር እንጂ ሃይሉ የትም እንደማያደርስ አውቆ የናቀው ሰው ነው፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ድህነትም
ባለጠግነትም ምንም እንደማያመጡ በመረዳት እና ድህነትንም ባለጠግነትንም የማይፈራ ሰው ነው፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና
መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13
ገንዘብን የማይወድ ከምንም ባለጠግነትም ይሁን ድህነት አልፎ ሰውን የተሚወድ ሰው
የተባረከ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #ትህትና #ባህሪ #ምሪት #ዘላለም #መተው #ልብ #ፉክክር #ቁሳቁስ #መታመን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment