Popular Posts

Monday, October 8, 2018

ይቅር ማለት የማንፈልግባቸው 14 ምክኒያቶች


የማይበደልና ይቅር ለማለት የማይፈተን ሰው ያለ ከመሰላችሁ የሞተ ሰው ብቻ ነው፡፡ ይቅር ያለማለት ፈተና የሁሉም ሰው ፈተና ነው፡፡ ይቅር የማለት ሃላፊነት የህያው ሰው ሃላፊነት ነው፡፡ ይቅር ለማለት መፈተን ህያው መሆናችንንና በህይወት መኖራችን ማረጋገጫው ነው፡፡
ይቅር አለማለት ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ከማበላሸት ጀምሮ ብዙ ጉዳቶች አሉት፡፡ ይቅር ማለት ቀላል ፈተና አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ይቅር ለማለት የማንፈልገው የእግዚአብሄር ቃል እውቀት ሳይኖረን ሲቀር ነው፡፡
ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። ትንቢተ ሆሴዕ 4፡6
1.      ይቅር ማለት የማንፈልገው በዳይ ተጠቃሚ ስለሚመስለን ነው፡፡
በዳይ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ በዳይ የሚታዘንለት ሰው ነው፡፡ በዳይ እንዲበድል የሚያደርገው የሃጢያት ባህሪው ነው፡፡ የሰው የሃጢያት ባህሪ ያሳዝናል እንጂ አያስቀናም፡፡ ሃዋሪያው ጳውሎስ ብትበደሉ አይሻላችሁምን? ያለው የሚበድልን ሰው እግዚአብሄር ስለሚክሰው የበድለውን ሰው ግን ከሁለት ያጣ ስለሚሆን ነው፡፡ ሰው ሲበድል ተጠቀሚው ሰይጣን እንጂ በዳዩ አይደለም፡፡ ሰው ደግሞ በደሉን ይዞ ይቅር አልልም ካለ ሰይጣን ይበልጥ ይጠቀማል፡፡ ሰይጣን አንዱን ሰው በመበደል ሲጎዳው ሌላውን ይቅር ባለማለት ጨምሮ ይጎዳዋል፡፡
ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡7-8
ሰው የሚበድለው ቢያንስ አንድ ያለገባው እውነት ስላለ ነው፡፡
ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። የሉቃስ ወንጌል 23:34
2.     ይቅር ማለት የማንፈልገው የበደለንን ክፉ ስራ መቀበል ማመቻመች ስለሚመስለን ነው፡፡
ይቅር ማለት ከዚህ ከበደለኝ ሰው ጋር ባለኝ ግንኙነት የተበደልኩትን ነገር ከግምት ውስጥ አላስገባውም ማለት ነው፡፡ ስለተበደልኩ ለበደለኝ መልካም ማሰብ ፣ መልካም መናገርና መልካምን ማድረግን አላቆምም ማለት ነው፡፡ ይቅር ማለት ስለበደለኝ ሰው ክፉ አላስብም ፣ ክፉ አልናገርምና ክፉ አላደርግም ማለት ነው፡፡ ይቅር ማለት የሰውን ክፉ ስራ እውቅና መስጠትና ማበረታታት አይደለም፡፡ የበደለንን ሰውን ይቅር ባለማለታችን የበደለንን ሰው የሚለውጠው ነገር የለም፡፡ የበደለንን ሰው እንዲያውም የሚለውጠው ይቅቅር ማለታችን ፣ መፀለያችን እና መልካምን ማድረጋችን ብቻ ነው፡፡ የበደለንን ሰው ሊለውጥ የሚችለው እግዚአብሄር እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ የበደለንን ሰው መውደድ ይቅር ማለት መምከር ይበልጥ መልካም ማድረግ እንጂ የበደለንን ሰው የመለወጥ ሃላፊነት የእግዚአብሄር እንጂ የእኛ ሃላፊነት አይደለም፡፡
ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡20-21   
3.     ይቅር ማለት የማንፈልገው ይቅርታ ከበዳይ ይልቅ ተበዳይን እንደሚጠቅም ስለማናውቅ ነው፡፡
በደልን ይቅር ማለት የበዳይ ሃላፊነት አይደለም፡፡ ይቅር ባለማለታችን ተፈትነን የምንወድቀው እኛ እንጂ በዳይ አይደለም፡፡ የእኛ ይቅር ማለት ወይም አለማለት በዳይ ላይ የሚጨምርለት ወይም የሚቀንስበት ነገር የለም፡፡ ይቅር ማለት ይበልጥ የሚጠቅመው ተበዳይን ነው፡፡ ይቅር አለማለት ይበልጥ የሚጎዳው ተበዳይን ነው፡፡ ይቅርታ ተበዳይን ያበለፅገዋል፡፡ ይቅርታ ተበዳይን እግዚአብሄር በሰጠው አለማ እንዲኖር ነፃ ያደርገዋል፡፡ ይቅር አለማለት ተበዳይን እስራት ውስጥ ያቆየዋል፡፡ ይቅር አለማለት ነገርን ሁሉ ከበዳይ ጋር በማያያዝ እስራት ውስጥ ይከተዋል፡፡ ይቅር አለማለት ተበዳይን በመከታታለ ከመንገዱ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡ ሰው ይቅር ሳይል እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጠውን ራእይ ለመፈፀም ነፃ መሆን አይችልም፡፡ ይቅር የማይል ሰው እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጠውን አላማ እንዲፈፅም የሰጠውን ሃይል የበደለ ሰው ላይ ክፉ በመመለስ እንዲያባክን ያደርገዋል፡፡     
4.     ይቅር ማለት የማንገፈልገው ይቅርታ የእኛን ስህተት የሚያሳይና ተሸናፊ ስለሚያደርገን ስለሚመስለን ነው፡፡
ይቅር ማለት የማንፈልገው ይቅርታን የፉክክር ነገር ስለምናደርገው ነው፡፡ ይቅርታ ማድረግ የማንፈልገው የአለም የፉክክር ስሜት ስላልለቀቀን ነው፡፡ ይቅርታ የአሸናፊነት እንጂ የተሸናፊነት ስሜት አይደለም፡፡ ይቅርታ የበላይነት እንጂ የበታችነት ስሜት አይደለም፡፡ ይቅርታ ክብር እንጂ ውርደት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ እንደሚሻላ ያሰየን እኛ ይቅር በማለት ነው፡፡ አባት ልጆችን ይቅር በማለት ከእነርሱ እንደሚሻለ ያሳያል፡፡ ተበዳይ ይቅር በማለት ከበዳይ እንደሚሻል ያስመሰክራል፡፡
ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡20-21
5.     ይቅር ማለት የማንፈልገው እግዚአብሄር ምን ያህል ይቅር እንዳለን ስለማንረዳ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ይቅርታ በሚገባ የተረዳ ሰው ይቅር ለማለት ይወስናል፡፡ እግዚአብሄር ይቅር ባይለው ኖሮ ለዘላም ከእግዚአብሄር እንደሚለይ የሚየውቅ ሰው ሌላውን ይቅር ለማለት ምንም ምክኒያት አይኖረውም፡፡ ታላቅ ይቅርታን እንደተቀበለ የተረዳ ሰው ታናሽ ይቅርታን ለመስጠት አይቸግረውም፡፡ በማንኛውንም ጊዜ የእግዚአብሄር ይቅርታና ምህረት እንደሚያስፈልገው የሚያውቅ ትሁት ሰው ይቅር ለማለት ይወስናል፡፡ ካለ እግዚአብሄር ይቅርታ ምንም ነገር ማድርግ እንደማይችል የተረዳ ሰው ሌላውን ይቅር ለማለት ይዘጋጃል፡፡ 
ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። የማቴዎስ ወንጌል 18፡32-33
6.     ይቅር ማለት የማንፈልገው እኛ እንደምንበድል ስለማንረዳ ነው፡፡
የሚበድል ሰው የበደለን የመጣው ከእንግዳ ፕላኔት ስለሆነ አይደለም፡፡  ሰውን እንዲበድል ያደረግው የስጋ ባህሪ በአንተ ውስጥ አለ፡፡ ሌላው ሰው እንጂ እርሱ እንደማይበድል የሚያስብ ሰው ትእቢተኛ ሰው ነው፡፡ አሁን ለበደለ ሰው የሚሰጠው  ይቅርታ ነገ ከነገ ወዲያ ከሌላ ሰው እንደሚያስፈልገው የማያውቅ ሰው ተታሏል፡፡
7.     ይቅር ማለት የማንገፈልገው በእግዚአብሄርን ዳኝነት ከልባችን ስለማናምን ነው፡፡
ይቅር ማለት የምንፈልገው እኛው ራሳችን ከሰን ፣ እኛው ራሳችን ፈርደንና እኛው ራሳችን መፈፀም ስለማንፈለግ ነው፡፡ ይቅር ማለት የማንፈልገው ዳኝነቱን ከእግዚአብሄር ለመወሰድ ስለመንፈተን ነው፡፡ ይቅር ማለት የማንፈልግው ነገሩን ከእግዚአብሄር በላይ በሚገባ እንይዘዋልን ብለን በከንቱ ስለምናስብ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ዳኝነት ስናምን ፈጥነን ይቅር ለማለት አንቸገርም፡፡ ይቅር ማለት የማንፈልገው የእግዚአብሄርን መሪነት ለመውሰድ ስለምንፈተን ነው፡፡ እግዚአብሄር በበቂ ሁኔታ እየመራ አይደለም በዳይን ልክ እያስገባ አይደለም ብለን ስናስብ የእግዚአብሄርን መሪነት በራሳችን መወሰድ እንፈልጋለን፡፡
ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ ራሳችሁ አትበቀሉ፡፡ ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።   ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡19
8.     ይቅር ማለት የማንፈልግው ይቅር ያልነውን ከለቀቅነው ይሳካለታል ብለን ስለምንፈራ ነው፡፡
ሰው እንዳይሳካለት መያዝ የበለጠ ከባድ ስራ ብቻ ሳይሆነ የማይቻል ነው፡፡ ሰው እንዳይሳከለት ማድረግ አንችልም፡፡ ሰው እንዳይሳካለት ለማድረግ መሞከር ግን ጉልበታችንን አላግባብ ያባክናል፡፡ ሰው በትክክልም ቢሆን በተሳሰተ መንገድ ሊሳካለት ይችላል፡፡ የሰውን የትኛውንም ስኬቱን ልንይዝና ልናስቀር አንችልም፡፡ ሰው ሰራሽ ጊዜያዊ ስኬትም ይሁን ከእግዚአብሄር የሚመጣ እውነተኛ ስኬት በእኛ ቁጥጥር ስር አይደለም፡፡ የሰው ስኬት ላይ መቆም ግን የራሳችንን ስኬት ላይ እንዳንሰራ ያዳክመናል፡፡ ይቅር ባንልም ብንልም የሰው ስኬት በእኛ እጅ አይደለም፡፡ የሰው ስኬት በእግዚአብሄር እጅ ነው፡፡ እግዚአብሄር የተሳሳተ ሰውን እንኳን መክሮና ወደትክክል መልሶ እንዲሳካለት ያደርጋል፡፡
9.     ይቅር ማለት የማንፈልገው ይቅርታ ማድረግ እንደ ድሮው መሆን ስለሚመስለን ነው፡፡
ይቅር ማለት ወዲያው እንድሮው መሆን ማለት አይደለም፡፡ ይቅር ማለት ያለፈውን መተው እንጂ ስለ ወደፊቱ ማቀድ አይደለም፡፡ ስለወደፊቱ ለማቀድ የአሁኑ ይቅርታ ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን የአሁኑ ይቅርታ በወደፊቱ አቅድ አይወሰንም፡፡ ይቅር ማለት ወዲያው እንደበፊቱ መተማመን ማለት አይደለም፡፡ እንደገና መተማመን ጊዜ ይወስዳል፡፡ መተማመን በጊዜ ውስጥ የሚገነባ እንጂ ከይቅርታ ጋር አብሮ የሚመጣ አይደለም፡፡ የአሁኑ ይቅርታ በወደፊቱ መተማን ላይ አይደገፍም፡፡
10.    ይቅር ማለት የማንገፈልገው ይቅር አለማለት በህይወታችን ለሰይጣን በር መክፈት እንደሆነ ስለማናውቅ ነወ፡፡
ይቅር አለማለትና ጥላቻ የሰይጣን ለም መሬት ነው፡፡ ሰይጣን በጥላቻና ይቅር ባለ ማለት ካልሆነ በስተቀር እንደልቡ መስራት አይችልም፡፡ ይቅር አለማለት የሰይጣን ምግብ እንደሆነ ብንረዳ ከይቅር አለማለትና ከምሬት ጋር ለአንድ ደቂቃ መኖር አንፈልግም ነበር፡፡ ይቅር አለማለት በህይወት ለሰይጣን በር መክፈት ነው፡፡ ይቅር አለማለትና ምሬት ለሰይጣን ፋንታን መስጠት ነው፡፡
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27
11.     ይቅር ማለት የማንገፈልገው እኛ ሁልጊዜ ትክክል የሆንን ስለሚመልሰልን ነው፡፡
እኛ ትክክል ብንሆንም ወይም የበደለን ትክክል ቢሆንም ወይም ደግሞ ሁለታችንም ትክክል ብንሆንም ወይም ሁለታችንም ብንበድልም ይቅር ማለትን ሊተካ አይችልም፡፡ ይቅር ማለትን ሊተካ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ይቅር ላለማለት የሚበቃ ምንም ጥሩ ምክኒያት ሊኖረን አይችልም፡፡
12.    ይቅር ማለት የማንገፈልገው ይቅር አለማለታችን ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነታችን ላይ የሚያመጣውን ከፍተኛ ጉዳት ስለማንረዳ ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት እንደሚወሰን ብናውቅ ፈጥነን ይቅር ለማለት እንበረታታለን፡፡  
እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። የማቴዎስ ወንጌል 5፡23-24
ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። የማርቆስ ወንጌል 11፡25
13.    ይቅር ማለት የማንፈልገው በዳያችን ወደ እግዚአብሄር ዞር ባለ ጊዜ ይቅር እንሚባል ስለማናውቅ ነው፡፡ እኛ የያዝንው በደል በዳይ በቀኑና በሰአቱ ከእግዚአብሄር ጋር የጨረሰው ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡
እኛ ለምንም ያህል ጊዜ በምሬትት እንቆይ እንጂ በዳዩ ይቅርታ በጠየቀ ቅጽፅበት እግዚአብሄ ይቅር ብሎታል፡፡ ይቅር ባለማለት እግዚአብሄር ከእኛ ጋር አይቆምም፡፡ ይቅር ባለማለት ብቻችንን የምንቀረው እኛ ብቻ ነን፡፡  
14.    ይቅር ማለት የማንፈልገው ይቅርታ በፍቅር እንደሚያሳድገን ስለማናውቅ ነው፡፡
ሁላችንም የፍቅር ሰዎች መሆን እንፈልጋለን፡፡ ፍቅር የህግ ፍፃሜ ነው፡፡ ፍቅርን የምንለማመደው ደግሞ በይቅርታ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ህይወታችን የምናድገው በይቅርታ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለብዙ ነገር የሚያምንን በፍቅር ስናድርግ ብቻ ነው፡፡  
የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፡16-19
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ይቅርታ #ምህረት #ፍርድ #ጠላት #ዲያቢሎስ #ስፍራ #ኢየሱስ #ጥላቻ #ትእቢት #መራርነት #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment