Popular Posts

Monday, October 1, 2018

በበጉ ደም አነጹ


እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ቢፈጥረውም ሰው በእግዚአብሄር ላይ አመፀ፡፡ ሰው አታድርግ የተባለውን ያንኑ ነገር በማድረግ በሃጢያቱ ከእግዚአብሄር ጋር ተለያየ፡፡
እግዚአብሄር ቅዱስ ነው፡፡ ሰው ደግሞ ሃጢያተኛ በመሆኑ ከእግዚአብሄር ጋረ ተለያየ፡፡ ሃጢያተኛው ሰው ወደ ቅዱሱ እግዚአብሄር መቅረብ አይችልም፡
እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም፤ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። ትንቢተ ኢሳይያስ 59፡1-2
ሰው ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብ የሃጢያት እዳው ሁሉ መከፈል ነበረበት፡፡ ሰው ደግሞ ሃጢያተኛ በመሆኑ የራሱን የሃጢያት እዳ ራሱ ሊከፍል አይችልም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው የሰውን የሃጢያት እዳ ለመክፈል ነው፡፡ ኢየሱስ ደሙን ያፈሰሰው ሰውን ከእግዚአብሄር ጋር የለየውን የሃጢያትን እዳ ለመክፈል ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ሃጢያት የሰራች ነፍስ እርስዋ ትሞታለች እንደሚል እኛ ስለሃጢያታችን መሞት ነበረብን፡፡ ስለሃጢያታችን ለዘላለም ከእግዚአብሄር መለያየት ነበረብን፡፡ ኢየሱስ ስለእኛ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ ሞቶዋል፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ስርየት ደሙን አፍስሶዋል፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ደሙን ያፈሰሰው ስለሃጢያቴ ይቅርታ ነው ብሎ የሚቀበል ሰውን ሁሉ እግዚአብሄር ይቀበለዋል፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያቱ ባፈሰሰው ደም ሃጢያቱን የታጠበ ሰው ወደ ቅዱሱ ወደ እግዚአብሄረ መቅረብ ይችላል፡፡ ከክርስቶስ ኢየሱስ ደም ውጭ የሰውን ሃጢያት ሊያነፃ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡7
ልብሱን ምንም ሃጢያት በሌለበት በበጉ ደም ያጠበ ሰው የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ያገኛል፡፡
ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። የዮሐንስ ራእይ 2214
በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ሃጢያታቸው የሚታጠብና ከሃጢያታቸው የነፁ ሰዎች ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር ይኖራሉ፡፡
ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ፦ እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም፦ እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። የዮሐንስ ራእይ 7፡13-15
አሁን ኢየሱስን ለመቀበል ከወሰንክ ይህንን ፀሎት ከልብህ ወደ እግዚአብሔር ፀልይ
እግዚአብሄር ሆይ የመዳንን እውቀት ስለላክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ሃጢያተኛ እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡ በሃጢያቴ ካንተ እንደተለሁ አውቃለሁ፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያቴ በመስቀል ላይ በመሞት የሃጢያቴን ዋጋ ሁሉ እንደከፈለ አውቄያለሁ፡፡ ኢየሱስ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው፡፡ ልጅህ አድርገህ ወደ ቤተሰብህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ደም #ስርየት #ይቅርታ #ልጅነት #ደህንነት #መልካምስራ #መልካምምግባር #ሞት #አላማመሳት #ሐጢያት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ፍጥረት #ልጅነት #ስራ #እምነት #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment