Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, January 31, 2017

ከአሸናፊዎች እንበልጣለን

በአለም ላይ ብዙ ሃያላንና አሸናፊዎች አሉ፡፡ አለም ሰዎችን በሚያንበረክኩ ብዙ አዋራጆች የተሞላች ነች፡፡ በአለማችን ደካሞች በሃያላን ሲሸነፉ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ሰዎች በአሸናፊዎች በየእለቱ ይሸነፋሉ፡፡
ሌሎችን ተሸነፉ ማለት እኛ እንሸነፋለን ማለት አይደለም፡፡ ለእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ሽንፈት የእኛ እጣ ፋንታ አይደለም፡፡ አሸናፊነት እጣ ፈንታችን ነው፡፡ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ከእኛ ጋር ሆኖ ፣ ለእኛ ሆኖ እና በእኛ ውስጥ ሆኖ ከማሸነፍ ውጭ ምንም ሊታሰብ አይችልም፡፡   
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡37-39
እርግጥ ነው እግዚአብሄር ለአሸናፊነት ጠርቶናል ስንል በአለም ላይ ያለውን ሁኔታ እየካድን አይደለም፡፡ እኛ ክርስቶስን የምንከተል የበላይ ነን የምንለው በራሳችን ጉልበት ሳይሆን በእግዚአብሄር ስለተወደድን ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በራሳችን ጥረትና መንገድ ሳይሆን በወደደን በእርሱ በክርስቶስ ነው፡፡ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ስንል እስከመጨረሻው በሚያፀናን በክርስቶስ ፍቅር ተመክተን ነው፡፡
በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ ፊልጵስዩስ 1፡6
እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። ዮሐንስ 10፡28
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው አለምን ያሸነፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለምንከተል ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞቱ በሻረው በኢየሱስ ነፃ ስለወጣን ነው፡፡
እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ ዕብራውያን 2፡14-15
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው የሰይጣን ሃይላት ሁሉ በሻረው በክርስቶስ ስለተሞላን ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው ክርስቶስ የአሸናፊውን ስልጣን ስለገፈፈው ነው፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ የሚንበረከኩለት ክርስቶስ ጌታችን ስለሆነ ነው፡፡  
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ ፊልጵስዩስ 2፡9-10
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው የሰይጣን ሃይላት ሁሉ በሻረው በክርስቶስ ስለተሞላን ነው፡፡
ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡10
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው አሸናፊውን አለም ባሸነፈው በክርስቶስ ስለምንታመን ነው፡፡
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃያል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አሸናፊ #አለቅነት #ስልጣናት #ስልጣን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment