Popular Posts

Monday, December 24, 2018

የምስጋና ምስክርነት


በሃጢያት ጨለማ በጠፋሁ ጊዜ ፈልጎ ያገኘኝን የክርስቶስን እውቀት ብርሃን በልቤ ያበራን እግዚአብሄርን ማመስገን አለብኝ፡፡ ሳላውቀው ሳልረዳው ስለሃጢያቴ የሞተልኝን እግዚአብሄርን የማመስገን ግዴታ አለብኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በጤና እና በህይወት የጠበቀኝ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡ በመልካም የፍቅር ቤት ውስጥ እንዳድግ ከወላጆቼ ታማኝነት ፣ ትጋትንና መስዋእትነትን ከህይወት ምሳሌነታቸው እንድማር ያደረገኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ ከወጣትነቴ ጀምሮ የመራኝን እግዚአብሄርን ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡
ይህን አልችለውም ብዬ በራሴ ተስፋ በቆረጥኩ ጊዜ ትችለዋለህ ብሎ ያመነብኝ በውስጤ ባስቀመጠው የሚያስችል ፀጋ የተማመነብኝ ከምችለው በላይ እንድፈተን ያልፈቀደ እግዚአብሄር ይመስገን፡፡   
በብዙ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ ሳልፍ ከጎኔ የሆነውን ያበረታኝን ሳዝን ያፅናናኝን ስደክም ያበረታኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
አብሬያቸው ይህን ድንቅ ጌታ እንዳመልክ የምወዳቸውንና የሚወዱኝን ወንድሞችና እህቶች የሰጠኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ያለኝን ድርሻ ያሳየኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ለምንድነው የጠራኝ ብዬ እንዳላወላውል ልቤን በፈቃዱ ያፀናውን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደጠራኝ ጥርት አድርጎ ያሳየኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
ሰዎች የከበረውን ከተዋረደው መለየት አቅቷቸው በህይወት ሲንከታተቱ የከበረውን ከተዋረደው እንድለይ ያደረገኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
በእያንዳንዱ ነገሬ እየመራኝ ያለውን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ መልካሙ እረኛዬ እግዚአብሄር እኔን በትጋት እንደሚመራኝ ከማወቄ የተነሳ የሌለኝ ነገር ሁሉ የሌለኝ ስለማያስፈልገኝ እንደሆነ እስከምረዳ ድረስ በትጋት የሚመራኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ ልቤ ሙሉ ነው የጎደለኝ ነገር እንዳለ አይሰማኝም፡፡
እንደገና መኖር ቢኖርብኝ አሁን የምኖረውን ኑሮ ደግሜ መኖር እስከምፈልግ ድረስ በህይወቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔ ከሰው ሁሉ በላይ ደስተኛ ነኝ ባልልም ነገር ግን ከእኔ በላይ ደስተኛ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡
በክርስቶስ ያገኘሁትን ሰላም አልፎ ሊገባ የሚችል ምንም ሁኔታ በህይወቴ የለም፡፡
እግዚአብሄር በሰዎች ፊት ሞገስ ሰጥቶኛል፡፡ ሰዎች ይወዱኛል ያከብሩኛል ስለዚህ ደግሞ በሰዎች ፊት ተቀባይነትን የሰጠኝን እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ፡፡
ስኬት የእግዚአብሄርን አላማ መፈፀም ነው፡፡ በህይወቴ የእግዚአብሄር አላማ በህይወቴ በመፈፀም የተሳካልኝ እንደሆንኩ አውቃለሁ፡፡
ከእኔ በላይ ተከናወነለት ብዬ የምቀናበት ሰው የለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ እንደተከናወነለት ሰው ልቤ ሙሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምሰራው ስራ ሁሉ ድል በድል የምሄድ ሰው አድርጎኛል፡፡  
እኔ ራሴን መንከባከብ ከምችለው በላይ እርሱ ሲንከባከበኝ አይቻለሁ፡፡ ጌታዬን ከተከተልኩ ጀምሮ እግዚአብሄር የሚያስገፈልገኝን ሁሉ ሲያሟላ ስላየሁት እግዚአብሄር ምን ያደርግልኛል የሚለው ጭንቀት ከህይወቴ ስለሞተ እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡ አሁን ሁል ጊዜ የሚያሳስበኝ ምን ላድርግለት ፣ እንዴት ልኑርለት ፣ ምኔን ልስጠው ፣ እንዴት ላገልግለው የሚለው ሃሳብ ብቻ ነው፡፡
ጌታን እንዳወቅኩ ህልሜ እግዚአብሄር በሃይል እንዲጠቀምብኝ ነበር፡፡ አሁን ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ በአገልግሎቴ ሰዎች ሲባረኩ ሲጠቀሙ ሳይ እግዚአብሄርን ከማመስገን ውጭ ሌላ ምንም ቃላት የለኝም፡፡ እግዚአብሄር በቃልህ ተጠቅሞ  ካለሁበት ነገር አወጣኝ የሚል ምስክርነት በመስማት ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ምስክርነት #መዳን #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #ኢየሱስ #ጌታ

No comments:

Post a Comment