Popular Posts

Monday, December 3, 2018

የባከነ ህይወት


ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። የሉቃስ ወንጌል 15፡17-19
የአባካኙ ልጅ ታሪክ ተብሎ በተለምዶ የሚታወቀው የመፅሃፍ ቅዱስ ታሪክ ስለ መልካም ልጅነትና ስለመጥፎ ልጅነት ብዙ ነገር ያስተምረናል፡፡ የአባካኙ ልጅ ታሪክ ስለተሳካ እና ስላልተሳካ የእግዚአብሄር ልጅነት ትምህርት ሊሰጠን ይችላል፡፡
በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን የልጅነት ህይወታችንን በከንቱ እንዳናባክን የአባካኙን ልጅ ችግሮች ከመፅሃፍ ቅዱስ ማጥናት ይጠቅመናል፡፡ የአባካኙል ልጅ አስተሳሰብ መረዳትና መንገዳችንን ማስተካከል ህይወታችን ፍሬያማ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡   
የአባካኙ ልጅ ሶስቱ መሰረታዊ ችግሮች
1.      አባካኙ ልጅ ችግር ከአባቱ በላይ ጥበበኛ የሆነ ስለመሰለው ነው፡፡
አባካኙ ልጅ የአባቱን ሃብት ተቀብሎ የሄደበት ምክኒያት አባቱ ለእርሱ እንደሚያስብለት እና እንደሚጠነቅቀልት እውቀቱ ስላልነበረው ነው፡፡ አባካኙ ልጅ ያለችው ትንሽ እውቀት አሳሳተችው፡፡ አባካኙ ልጅ ጥበበኛ የሆነ ሲመስለው ሞኝ ሆነ፡፡
እንዲሁም እኛ የእግዚአብሄር ልጆች ምንም ብናውቅ መቼም ቢሆን ከእግዚአብሄር በላይ እንደምናውቅ ሊመስለን አይገባም፡፡ እግዚአብሄር የመጨረሻውን ከመጀመሪያው ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር የከከለከለን ሁሉ አይጠቅመንም ብሎም ይጎዳናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ካዘዘን በአለም ላይ ማድረግ የምንችለው የተሻለው ነገር እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ በትንሽ እውቀታችን ተጠቅመን የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ለማስተካከል አንሞክር፡፡ እግዚአብሄር እንዳለው ሳይቀንሱና ሳይጨምሩ ምንም ሳይለውጡ እንዳለ መታዘዝ የልጅነትን ሙሉ በረከት ያስገኝለናል፡፡
2.     አባካኙ ልጅ የአባቱን ምሪት አልወደደም
አባካኙ ልጅ ወደሩቅ አገር የሄደበት ምክኒያት ለጊዜው እስራት የመሰለው የአባቱን ምሪት ለመሸሽ ነው፡፡ አባካኙ ልጅ ወደሩውቅ አገር የሄደው በላዩ ላይ ያለውን የአባቱን ሰልጣን ለመሸሽ ነው፡፡ አባካኙ ልጅ የአባቱን ምሪት ቢያደንቅ እና በአባቱ ምሪት እንደተጠቀመ ቢያውቅ ኖሮ ወይ ርቆ አይሄድም ወይም ርቆ ሄድም እንኳን ምን ማድረግ እንዳለበት ከአባቱ ምክርን ተቀብሎ ይፈፅመው ነበር፡፡
እንዲሁ በእግዚአብሄር ልጅነታችንን ካለፍሬ የሚያስቀረንና የሚያባክነው የእግዚአብሄርን ምሪት አለመፈለጋችን ነው፡፡ ብዚዎቻችን እግዚአብሄርን ለክብርህ መኖር እፈልጋለሁ እንላለን ነገር ግን ለክብሩ የምንኖርበትን የራሱን መንገድ ሲያሳየን መታዘዝ እንደ ንግግሩ አይቀልም፡፡ ምራኝ እንላለን ሲመራን ግን የማናደርግበትን ምክኒያቶች እንዘረዝራለን፡፡ የእግዚአብሄር ስልጣን ለእኛ ጥቅም እንደሆነ አናውቀውም፡፡ የእግዚአብሄር ስልጣን እንቅፋት ይመስለናል፡፡ የእኛ ስኬታችንንና ክብራችን  ዘወትር በቃሉ እግዚአብሄርን ለመታዝዝ መወሰን ነው፡፡
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 11፡4
3.     አባካኙ ልጅ ሳያይ ሊያምን አልቻለም  
አባካኙ ልጅ አባቱ የሚነግረውን ከማመን እና በአባቱ ልምድና ሰፊ እውቀት ከመጠቀም ይልቅ ነገሮችን በራሱ መሞከር ፈለገ፡፡ አባቱን ቢሰማ ኖሮ ከዚህ ሁሉ ውድቀት ይድን ነበር፡፡ አባቱን ቢያምን ኖሮ ህይወቱን አያባክነውም ነበር፡፡
እንዲሁም የእግዚአብሄር ልጆች ስንሆን የሚታየውን በአካባቢያችን ያለውን ሁኔታ ከማየት ይልቅ የማይታየውን የእግዚአብሄርን ሃሳብ መከተል ይሻለናል፡፡ ከሚታየው ከጊዜያዊው ነገር ይልቅ አሁን በተፈጥሮአዊ አይን የማይታየውን የእግዚአብሄርን አላማ መከተል ይጠቅማል፡፡ ምንም ሞኝነት ቢመስልም የእግዚአብሄርን መንገድ መምረጥ ውጤታማ ያደርገናል፡፡ ብዙ ሰዎች ባይመርጡንም የእግዚአብሄርን ነገር መፈለግ አንድ ያለው ህይወታችንን እንዳናባክን ያድርገናል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ማክበር #መደሰት #አባት #ቤተሰብ #ጥላ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #እውቀት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #ማስተዳደር #እረፍት

No comments:

Post a Comment