Popular Posts

Monday, December 10, 2018

በክፉ ሰዎች አትቅና


ልጄ ሆይ፥ በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትውደድ፤ ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ሽንገላን ትናገራለችና። መጽሐፈ ምሳሌ 24:1-2
ክፋት ምንም የሚያስቀና ንፅህና የለውም፡፡ ክፋት ምንም የሚስብ ዘላቂ ነገር የለውም፡፡ ክፋት ምንም የሚያስቀና መልካምነት የለውም፡፡ ክፋት ያመልጠኛል ተብሎ የሚናፈቅ ነገር የለውም፡፡ ክፋት ምንም የሚያቀና ጥበብ የለበትም፡፡ ክፋት ምንም የሚያስወድድ ምንም ነገር የለውም፡፡
ስለ ኃጢአተኞች አትቈጣ፥ በክፉዎችም አትቅና። ለኃጢአተኛ የፍጻሜ ተስፋ የለውምና፥ የኀጥኣንም መብራት ይጠፋልና። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፥ ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ። መከራቸው ድንገት ይነሣልና፤ ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል? መጽሐፈ ምሳሌ 24:19-22
በክልፉዎች ላይ የምንናደደው የተጠቀሙ ስለሚመስለው ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ክፉ ሰዎች እየተጠቀሙ ሳይሆን መከራ ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ ሃጢያተኞች በክፋታቸው ይጎዳሉ እንጂ አይጠቀሙም፡፡
ክፉዎች በክፉነታቸው ብቻ ሊታዘንላቸው ይገባል እንጂ እንደበለጡ እንደተጠቀሙ ቆጥረን ልንቆጣባቸው አይገባም፡፡ ሃጢያተኞች እንደተጠቀሙ አድርገን ልንናደድባቸው አያስፈልግም፡፡
ሰው ቢረዳው ክፉ አይሆንም፡፡ ሰው ቢረዳው የክፋትን ቁራጭ በህይወቱ አያስተናግድም ነበር፡፡ ሰው ካልተሸወደ በስተቀር በትክክለኛ አእምሮ ክፋትን አይሰራም፡፡ ሰው በትክክለኛ እእምሮ ክፋትን በመስራት ከእግዚአብሄር ጋር አይጣላም፡፡ ሃጢያተኞች እንደ ተጠቃሚዎች ሳይሆን እንደ ተሸወዱ ሰዎች ያሳዝናሉ፡፡ ክፉዎች እንደአሸናፊ ሊቀናባቸው አይገባም፡፡ በክፉዎች የሚቀና ሰው የክፋትን አደገኝነት ያልተረዳ ሰው ነው፡፡  
በሃጢያተኛ የመቅናት አንዱ መገለጫ መንገድ የክፉን መንገድ ተከትሎ ክፋትን ማድረግ ነው፡፡ በሃጢያተኛ የመቅናት አንዱ መገለጫ መንገድ እኔ እብሳለሁ ብሎ በክፋት መፎካከር ነው፡፡ በክፋት የሚወዳደር ሰው የክፋትን አስቀያሚነት በሚገባ ያልተረዳ ሰው ነው፡፡ በክፉ ላይ የሚቀና ሰው የክፋትን ትክክለኛ መልክ የማያውቀው ሰው ነው፡፡ ክፋትን የሚያውቀውና የሚፀየፈው ሰው በክፉ ሰው ላይ ቀንቶ ክፋትን በክፋት ፋንታ አይመልስም፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡9
ክፉ ሰው ያዋጣኛል ብሎ በክፋት መንገድ ሲሄድ ስታይ መንገዱን ተፀየፈው እንጂ በክፋቱ ተሳካለት ብለህ አትቅናበት፡፡ በመልካም የተሳካለትን ሰው አይተህ ብትቀናበትና ብትከተለው ታተርፋለህ፡፡ በክፉ ሰው ቀንተህና ተጠቃሚ የሆነ መስሎህ ብትከተለው ትስታለህ፡፡
በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። መጽሐፈ ምሳሌ 24:31-32
በግፈኛ ሰው አትቅና፡፡ ግፈኛን ሰው ስታይ ግፉን ተፀይፈህ እንደ እርሱ ላለመሆን በልብህ ወስን፡፡ ግፈኛ ስው በግፉ ሲሳካለት ስታይ ከግፉ ጋር ላለመካፈል እግሬ አውጭን ብለህ ሽሽ፡፡
ግፈኛ ሰው ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ እንጂ የምትከተለው ምሳሌ አይሁንህ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #መልካም #ክፉ #ክፋት #አትቅና #አሸንፍ #ብቃት #የእግዚአብሄርችሎታ #የእግዚአብሄርሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ፅድቅ #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ #ምስክርነት

No comments:

Post a Comment