Popular Posts

Thursday, December 6, 2018

ምስኪኑ ዝነኛ


ሰዎች የሚሮጡለትና ራሳቸውንና እድሜያቸውን የሚሰጡለት ነገር ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት የከበረ ነገር አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች የከበረውን ከተዋረደው መለየት ባለመቻላቸው ውድ የሆነውን ህይወታቸውን በከንቱ ያባክኑታል፡፡  
አንድ ሰው ሰዎች በምድር ላይ የሚሮጡለት ነገር ሁሉ ኖሮት በምድር ላይ መከተል የሚገባውን ነገር የማይከተል ሰው ምስኪን ሰው ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ ብዙ ገንዘብና ዝና ኖሮት ነገር ግን በገንዘብና በዝና የማይገዛውን ዋናውንና ውዱን የእግዚአብሄርን ህይወት ካጣው ከእርሱ በላይ ምስኪን ሰው የለም፡፡
ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡27
ሰው በምድር ላይ 120 ዓመት በሚኖርበት ቆይታው በምድር ላይ ርስትና ሃብት ኖሮት ዘላለማዊውን ርስት ግን ካጣ ከንቱ የከንቱም ከንቱ ነው፡፡
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1፡18-19
ሰው በምድራዊ ነገር ሁሉ ባለጠጋ ሆኖ በእግዚአብሄር ነገር ደሃ ከሆነ ያሳዝናል፡፡
ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡5-6
ሰው ሁሉ ሰው ሊያጅበው የሚፈልግ ታቀዋቂና ተወዳጅ ሰው ሆኖ የእግዚአብሄር አብሮነት ከእርሱ ጋር ከሌለ የድሃ ድሃ ነው፡፡
ሰው አለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?
ሰው በምድር ላይ ብዙ ሃብትና ንብረት ቢኖረው ነገር ግን የፈጠረው እግዚአብሄር በእርሱ ደስ የማይሰኝበት ከሆነ ምን ዋጋ አለው?
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 3፡36
ሰው በአለም ላይ የሚያስከብሩ ነገሮች ሁሉ ኖሮት በእግዚአብሄር ዘንድ ያለው የልጅነት ክብር ከሌለው ምን ይጠቅመዋል፡፡
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? የማቴዎስ ወንጌል 16፡26
ሰው በምድር ላይ ተዝናንቶ ኖሮ ነገር ግን የዘላለም ህይወት ባይኖረውና ቢፈረድበት ምን ይረባዋል?
ሰው ሁሉ ነገር ኖሮት የተፈጠረለትን አላማ እግዚአብሄርን ካላመለከ የሞት ሞት ነው፡፡
ሰው ሰዎች ሁሉ አድንቀውትና አጨብጭበውለት የአለም ተሸላሚ ሆኖ እግዚአብሄር ግን ጎሽ ካላለው ምን ዋጋ አለው፡፡
ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። የማቴዎስ ወንጌል 25፡23
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment