Popular Posts

Thursday, December 20, 2018

በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ፣ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም


የተጻፈውም ጽሕፈት፦ ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል። የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። ትንቢተ ዳንኤል 5፡25-28
ይህ ፅሁፍ የተፃበት ሰው ንጉስ የነበረና ንግስናውን ካለአግባብ በመጠቀም ህዝቡን ሲያጎሳቁል ስለነበረ ነው፡፡ ነው ይህ ጽሁፍ የተፃፈው እግዚአብሄርን ስላልፈራና ስለተዳፈረ ንጉስ ነው፡፡
እግዚአብሄርን አለመፍራትና ማን አለብኝነት ሰይጣንን መከተል ነው፡፡ በየትኛውም ቦታ በቤተሰብ በቤተክርስትያን በአገር ትእቢት ሰውን ያዋርዳል፡፡ ትእቢት ውድቀትን ይቀድማል፡፡ ሰው የሚሰነብተው በትህትና እንጂ ትእቢት ከመጣ ውድቀት ይመጣል፡፡
ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል። መጽሐፈ ምሳሌ 16፡18
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በቤተክርስትያን ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ በፍጥረቶቹ ላይ ስለሚሆነው ነገር ሁሉ ግድ ይለዋል፡፡
ምድር የግለሰቦች አይደለችም፡፡ ምድር የእግዚአብሄር ነች፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሄር ለሰዎች ስልጣንን በአደራ ይሰጣል፡፡ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለም፡፡ 
ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡1
እግዚአብሄር ሰዎችን ስለሚወድ ሰዎችን እንዲያገለግሉና በመልካም እንዲያስተዳድሯቸው እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ስልጣንን ይሰጣል፡፡
አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል። እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2፡3-8
መሪን የሚሾመው እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄር ህቡን ወደ ብልፅግና እንዲመሩና መሪዎችን ይሾማል፡፡
ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሄር ነች፡፡ ስልጣን የእግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄር ስልጣንን ለሰዎች በአደራ ይሰጣል፡፡ ስልጣን በሰው ቤት ላይ እንደተሾመ ሰው በአደራ የሚሰጥ ሃላፊነት ነው፡ 
ስልጣን ተጠቃሚነት አይደለም፡፡ ስልጣን ሃላፊነት ነው፡፡ ስልጣንን ከእግዚአብሄር በአደራ እንደተሰጠ ጊዜያዊ ሃላፊነት የማያይ ሰው ስልጣኑን አላግባብ ይጠቀማል፡፡ ስልጣኑን የሰጠው አምላክ እንደሚጠይቀው የማያውቅ ሰው በስልጣኑ ይባልጋል፡፡ ስልጣኑን የሰጠው አምላክ ስራውን እንደሚከታተለውና እንደሚመዝነው የማውቅ ሰው እንዲያገለግለው የተሰጠውን ህዝብ ያጎሳቁላል፡፡ ስልጣኑን በአደራ ለሰጠው አምላክ ሃላፊነት እንዳለበትና እንደሚጠየቅ የማያውቅ ሰው እንደ ባለአደራ ሳይሆን እንደግል ቤቱ ያስተዳደራል፡፡
እግዚአብሄር መሪን ይመዝናል፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛን መሪን ይሽራል፡፡ እግዚአብሄር ስልጣንን ለወደደው ይሰጣል፡፡
ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው። ትንቢተ ዳንኤል 4፡17
እግዚአብሄር በሌላው ላይ የሰጣቸውን ድል በሃያልነታቸው እንዳገኙት የሚያስቡ ሰዎች ንስሃ ሊገቡ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ህዝብን የማስተዳደር ስልጣን በራሳቸው ሃያልነትና ቅልጥፍና እንዳገኙት የሚያስቡ ሰዎች ሊያዝኑና ሊፀፀቱ ይገባል፡፡ የጦርነት ድል የሚገኘው በሃያልነት ሳይሆን በእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ ነው፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መጽሐፈ መክብብ 9፡11
እግዚአብሄር የሰጣቸውን ህዝብን የማስተዳደር ስልጣን በራሳቸው ሃያልነትና ቅልጥፍና እንዳገኙት ቆጥረው እግዚአብሄርን ባለመፍራት የኖሩ ሰዎች ሊያዝኑበትና ሊያፍሩበት ይገባል፡፡ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ህዝብን የመምራት እድል በሚገባ ያልተጠቀሙ ሰዎች ሊያዝኑና ንስሃ ሊገቡ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር በእጃቸው የሰጣቸውን ህዝብ ያጎሳቆሉ ሁሉ ንስሃ ሊገቡ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር በእጃቸው የሰጣቸውን ህዝብ የዘረፉ ሁሉ በሌብነታቸው ሊያፍሩ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር በአደራ የሰጣቸውን ህዝብ ሃብትና ንብረት በስግብግብነት ሁሉ ወደ ግል ይዞታነት ያሸጋገሩ ሁሉ ሊያፍሩ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ሃላፊነት ሳይወጡ የራሳቸውን የግል ጥቅም ሲያሳድዱ የኖሩ ሁሉ ሊፀፀቱ ይገባል፡፡ እግዚአብሄር እንዲመሩትት እና ወደብልፅግና እንዲያደርሱት የሰጣቸውን ህዝብ አስፈራርተው የነጠቁትና የበዘበዙት ሁሉ ሊያፍሩበት ይገባል፡፡ እግዚአብሄር በአደራ የሰጣቸውን ህዝብ በማን አለብኝነት የገረፉ ፣ ያሰቃዩና የገደሉ ሁሉ በትእቢት መቀጠል ሳይሆን ከእግዚአብሄር ምህረትን መጠየቅ አለባቸው፡፡  
አሁን እግዚአብሄር በሰጣቸው ጊዜ ሊመለሱና እግዚአብሄር በሰጣቸው ስልጣን ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ሊወስኑ ይገባል፡፡
አሁንም በትእቢት የሚመላለሱ ሰዎች ከመፀፀት ይልቅ ወቀሳውንና ጥፋተኝነቱን ወደሌላ ሰው የሚያስተላለፉ ሰዎች እግዚአብሄር ይፈርድባቸዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ስራ የማይቀበሉ አገሪቱ ላይ የመጣውን ለውጥ የሰው የእጅ ስራ የሚያደርጉ ሰዎች እግዚአብሄርን ደስ አያሰኙትም፡፡ በአገሪቱ ላይ የመጣው ለውጥ የእግዚአብሄር እጅ እንደሌለበት የሚያስቡ ሰዎች እንደገና ሊያስቡበት ይገባል፡፡
እግዚአብሄር እድልን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር መዝኖ ቀለህ ተገኘህ ብሎ የጣለውን ሰው ሊያነሳው የሚችል ማንም ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄር መዝኖ የጣለውን ሰው የተባበሩት መንግስታት አያነሳውም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ተመዝኖ የተጣለን ሰው ሃያሉ የአሜሪካ መንግስት አያስጥለውም፡፡
ባለስልጣኖች ስልጣን የእግዚአብሄር መሆኑን የመረዳት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ስልጣን የእግዚአብሄር እንደሆነ እግዚአብሄርን በመፍራት ህዝብን ለማገልገል ለህዝብ ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነ የማይረዱ ባለስልጣት እግዚአብሄር ይፈርድባቸዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ስርአት የሚቃወመው እግዚአብሄርን ይቃወማል፡፡ እግዚአብሄር በፈጠረው ምድር ላይ እግዚአብሄርን ተቃውሞ የሚሳካለት ሰው የለም፡፡  
ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2፡10
እግዚአብሄር የማንንም ውድቀት አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር ሃያል ነው ማንንም አይንቅም፡፡ ራሱን የሚያዋርደውን ማንኛውንም ሰው እግዚአብሄር ይቅር ይላል ያነሳዋል፡፡ ራሱን የሚያዋርደውን ሰው ልብ እግዚአብሄር አይንቅም፡፡ ራሱን የሚያዋርደውን ሰው እግዚአብሄር ህዝቡን የሚያገለግልበትን ሌላ እድል ይሰጠዋል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ባለስልጣን #ፀሎት #ወታደር #ኢየሱስ #ጌታ #መበለት #ድሃአደግ #ድሃ #ጭቆና #ፍትህ #ፍርድ #ቀራጭ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment