Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, December 5, 2018

መንፈሳዊ ተራማጅ


በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት አምነን የዳን ሁላችን በማደግና በመለወጥ እግዚአብሄርን ማስከበር ረሃባችንና ጥማታችን ነው፡፡ ማናችንም ባለንበት መቅረት አንፈልግም፡፡ ማናችንም ከእግዚአብሄር ጋር እኩል መራመድ እንፈልጋለን፡፡ ሁላችንም ጌታን በትጋት መከተል እንፈልጋለን፡፡ ሁላችንም ሁላችንም በመንፈሳዊ ህይወታችን ማደግና መሻገር እንፈልጋለን፡፡
ሁላችንም እንደ ሄኖክ አካሄዳችንን ከእግዚአብሄር ጋር እኩል ማድርግ እንፈልጋለን፡፡ ማናችንም እግዚአብሄር ካቀደልን እርምጃ አንድም እርምጃ ወደኋላ መቅረት አንፈልግም፡፡
ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና። ኦሪት ዘፍጥረት 5፡24
ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ ወደ ዕብራውያን 11፡5
·         መንፈሳዊ አካሄድ እንደ ተፈጥሮአዊው አካሄድ በስጋ አይን የሚታይ ባለመሆኑ ከእግዚአብሄር ጋር በትክክል መራመዳችንን እርግጠኛ መሆን እንፈልጋለን፡፡ በአሁኑ ሰአት መድረስ ያለብንኝ ቦታ ላይ ነኝ ወይ የሚለውን ጥያቄ ልስ ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ በአካሄዴ በትክክለኛው እርምጃ ላይ ነኝ? የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜ ያሳስበናል፡፡
ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር እየተራመዱ ቢሆንም ከእግዚአብሄር ጋር እየተራመዱ መሆናቸውን የሚያውቁበትን መንገድ ከቃሉ ካለማወቃቸው የተነሳ ራሳቸውን በከንቱ ይኮንናሉ፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ማደግና መለወጣቸውን ለማወቅ በቁሳቁስ ራቸውን ስለሚለኩ ካለ አግባብ ይጨነቃሉ፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር መራመድና አለመራመድ ሊለካ የማይችል ረቂቅ ነገር አይደለም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር መራመዳችንን እና አለመራመዳችንን በእግዚአብሄር ቃል ህይወታችን መፈተሽና ማወቅ እንችላለን፡፡ በህይወታችን እያደግን እየተለወጥን እየተሻገርን መሆናችንን የምናውቅባቸውን ነገሮች ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
1.      ለፅድቅ ረሃብና ጥማት ካለን
በእግዚአብሄር ዘንድ ትክክል ሆኖ ለመገኘት ረሃቡና ጥማቱ ካለን እያደግን እየተለወጥም መሆኑ ምልክት ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የእግዚአብሄርን ፅድቅ መራብና መጠማት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የተራበና የተጠማ ሲያገኝ ያረካናል፡፡
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። የማቴዎስ ወንጌል 5፡6
2.     በእያንዳንዱ ቀን የእግዚአብሄርን ቃል እየፈልግንና እያሰላስልን ከሆነ
ለእግዚአብሄር ቃል በህይወቱ የመጀመሪያውን ስፍራ የሚሰጥ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር እየተራመደ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያስብና የሚያሰላስል ሰው ቃሉን ለማድረግ ጉልበት ያገኛል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያሰላስል ሰው እያደገና እየተሻገረ መሆኑ ማረጋገጫው ነው፡፡
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡8-9
3.     እግዚአብሄር በመንፈሱ የመራንን እያደረግን ከሆነ
ብዙ ሰዎች ያደጉና የተለወጡ የሚመስላቸው ታላላቅ ነገር ሲያደርጉ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በዝምታ የሚመራቸውን ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ እያደጉ እየተለወጡ ብሎም እግዚአብሄር ወደ አየላቸው የክብር ደረጃ እየገቡ ነው፡፡
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡14
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #መጠበቅ #መተማመን #እምነት #መራመድ #መውጣት #መግባት #አልተገኘም #እግዚአብሔር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አካሄድ #እርምጃ #አማልክት #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሔርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment