Popular Posts

Saturday, December 8, 2018

ሰውን የመፍራት ወጥመድ


ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል። መጽሐፈ ምሳሌ 29:25
ሰውን መፍራት ባርነት ነው፡፡ ሰውን እንደ መፍራት ለእግዚአብሄር እንዳንኖር የሚያደርገን ባርነት የለም፡፡
ሰው ከሰው ፍርሃት ነፃ መሆን ካልቻለ ለእግዚአብሄር ለመኖር ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡
ሰው ከሰው መልካምን ነገር ሲቀበል አብሮ ሰውን መፍራት እንዳይቀበል መጠንቀቀ አለበት፡፡ ሰው መልካመ ሲያደግለት እግዚአብሄርን ማየትና እግዚአብሄርን ማመስገን አለበት፡፡ ሰው ሰውን የመልካምነት ምንጭ ካደረግው ሰውን ይፈራል፡፡ ሰው እግዚአብሄ ካልተጠቀመበት በስተቀር ምንም መልካም ሊያደረግ አይችልም፡፡
ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። የማርቆስ ወንጌል 10፡18
ምንም መልካም ያደረገልን ሰው ቢሆን እግዚአብሄር እንደተጠቀመበት ሰው ሊወደድና ሊከበር እንጂ ሊፈራ ግን አይገባውም፡፡
እግዚአብሄር ሰውን ፈርተን የምናደርገው ማንኛውንም ነገር አይቀበለውም፡፡ ሰውን መፍራታችን እግዚአብሄርን እንዳንፈራ ያደርገናል፡፡
በህይወት ስኬታማ ለመሆን ከሰው በላይ እግዚአብሄርን መፍራት መምረጥ አለብን፡፡ ሰውን ከፈራን እግዚአብሄርን መፍራት እንደተውን ማወቅ አለብን፡፡ እግዚአብሄርን የሚፈራ ሰው ደግሞ ሰውን ሊፈራ አይችልም፡፡
ኢየሱስ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም እንዳለ ሁሉ ሰውንም እግዚአብሄርን በአንድ ጊዜ በአንድ ላይ መፍራት አንችልም፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ የማቴዎስ ወንጌል 6፡24
ሰውንም እግዚአብሄርን ለመፍራት የሚሞክር ሰው በከንቱ ይደክማል እንጂ አይሳካለትም፡፡ ሰውንም እግዚአብሄርን መፍራት የሚባል ነገር የለም፡፡ ወይ ሰው እንፈራና እግዚአብሄርን አንፈራም ወይም ደግሞ እግዚአብሄርን በመፍራት ሰውን አንፈራም፡፡
እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ። እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል? ትንቢተ ኢሳይያስ 2፡21-22
ሰው ሊፈራ የሚገባው አይደለም፡፡  ሰውን መፍራት ሰውን ያለአቅሙ የእግዚአብሄር ቦታ ላይ ለመስቀል እንደመሞከር ነው፡፡ መልካም ያደረገልን ሰውም ቢሆን ሊፈራ እና ከእግዚአብሄር በላይ ሊሰማ አይገባውም፡፡
ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ፦ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። የሐዋርያት ሥራ 5፡29
ሰው ሊፈራ የማይገባው ውስን ፍጥረት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በህይወታችን ላይ ካለው ተፅእኖ በላይ እግዚአብሄር በህይወታችን ላይ ያለው ተፅእኖ እጅግ በጣም ይበልጣል፡፡
ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። የማቴዎስ ወንጌል 10፡28
ሰውን ፈርተን ከምናተርፈው ትርፍ ይልቅ እግዚአብሄርን ፈርተን የምናተርፈው ይሻላል፡፡ ሰዎች ከፈራችኋቸው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማስተው የራሳቸውን ፈቃድ ለማድረግ ይጠቀሙባችኋል፡፡
ስለዚህ በድፍረት፦ ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን። ወደ ዕብራውያን 13፡6
ኢየሱስ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈፀም  እናቱንና አባቱን እንኳን አልፈራም፡፡  
ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። የሉቃስ ወንጌል 2፡48-49
የሰው ፍርሃት ብዙዎችን በሙላት እንዳይጨርሱ ከእግዚአብሄር ፈቃድ መንገድ አሰናክሏቸዋል፡፡ የሰው ፍርሃት ብዙዎችን የእግዚአብሄርን አላማ በህይወታቸው ተከትለው ፍሬያማ እንዳይሆኑ አድርጎዋቸዋል፡፡  ሰውን መፍራት የብዙዎችን ህይወት ከንቱ አድርጎ አስቀርቷል፡፡
ዛሬ ራሳችንን እንመርምር፡፡ ሰውን ፈርተን ያላደረግነው የእግዚአብሄር ሃሳብ ካለ በፍጥነት ንስሃ እንግናባና እንመለስ፡፡ ሰዎች ደስ ባይላቸውም የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማድረግ እግዚአብሄርን ለማክበር እንጨክን፡፡
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ወደ ገላትያ ሰዎች 1፡10
ምንም አስቸጋሪ ቢሆን ከሰው ይልቅ እግዚአብሄርን መፍራት ይበልጣል፡፡
ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ የሐዋርያት ሥራ 4፡18-19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጌታ #ኢየሱስ #ፍቅር #ፍርሃት #ሃይል #ራስንመግዛት #አላማ #መዳን #ነፃነት #ቅድስና #ሰላም #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #የዋህነት #ንፁህ

No comments:

Post a Comment