Popular Posts

Friday, December 21, 2018

ለእነዚህ 11 ነገሮች ጊዜ የለንም


1.      ለጭንቀት
የእግዚአብሄር ፅድቅና መንግስቱን ለመፈለግ በቀን 24 ሰአት 7 በሳምንት ሰባት ቀን አለን፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ከመፈለግ የሚተርፍ እና ለጭንቀት የሚሆን አንድ ደቂቃም የለንም፡፡ 
እርሱ ስለእናንት ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን በእርሱ ላይ ጣሉት የተባለለት ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነ አባት እያለን በጭንቀት የምናባክንው ምንም ጉልበት የለም፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። የማቴዎስ ወንጌል 6፡31-32
ጭንቀት ፍሬ እንዳናፈራ የሚያደርግ የመንፈሳዊ ፍሬ ጠላት ስለሆነ በጭንቀት ለማባከን የምንፈልገው ምንም ፍሬ የለንም፡፡
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። የማቴዎስ ወንጌል 13፡22
2.     ለውድድር
እግዚአብሄር የሰጠን በቂ የህይወት ሃላፊነት አለን፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ ሰርተን እንድናከብረው የሰጠን የህይወት አላማ አለን፡፡ እግዚአብሄር የጠራን ለተለየ አላማ ነው፡፡ ከእኛ የተለየ የህይወት አላማ ካለው ሰው ጋር አንፎካከርም፡፡ እኛ የምንወዳደረው እግዚአብሄር ከሰጠን ስራ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠኝን ስራ ምን ያህሉን ሰርቼያለሁ ብለን በመጠየቅ     የተሰጠንን ሃላፊነት ከራሳችን የስራ አፈፃፀም ጋር እናስተያያለን፡፡  
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
3.     ለስንፍና
ነገ ይመጣሉ ብለን ስለምናስባቸው ስለ ትልልቅ ነገሮች አንመካም፡፡ ያለን አሁን ነው፡፡ አሁንን በሚገባ እንጠቀምበታለን፡፡ አሁን እንተጋለን፡፡ ለነገ ብለን የምንቆጥበው ጉልበት የለንም፡፡ የጉልበት የቁጠባ ባንክ የለም፡፡ ዛሬ ካልተጋንበት ጉልበታችን ይባክናል እንጂ አይጠራቀምም፡፡ ታማኝነታችንን ለማሳየት ታላላቅ ነገሮችን አንጠብቅም፡፡ አሁን ባለን ነገር ታማኝነታችንን እናሳያለን፡፡ በመቃብር የስራና የትጋት እድል የለም፡፡ 
አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። መጽሐፈ መክብብ 9፡10
4.     ለቅንጦት
እግዚአብሄር የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያሟላ ቃል ገብቷል፡፡ ነገር ግን ቅንጦታችንን እንደሚያሟላ ቃል የገባበት አንድም ቦታ አይገኝም፡፡ ለቅንጦት የምንጠቀመው ገንዘብ ሁሉ ከመሰረታዊ ፍላታቸን ላይ የተቀነሰ ነው፡፡ ለቅንጦት የምንጠቀመው የመሰረታዊ ፍላጎታችን በጀት ነው፡፡ በቅንጦት ላይ ያዋልነው ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎት ይቀንሳል፡፡ ለመሰረታዊ ፍላጎት ማዋል ያለብንን ነው በቅንጦት ላይ የምናቃጥለው፡፡ ስለዚህ ከመሰረታዊ ፍላጎት ውጭ በቅንጦት ላይ የምናጠፋው አንድም ገንዘብ የለንም፡፡
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡3
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡8-9
5.     ለጥላቻ
ስንሰራ የተነደፍነው ለፍቅር ነው፡፡ ስንወድ ያምርብናል፡፡ ስንወድ እንሳካለን፡፡ ስንወድ እንከናወናለን፡፡ ለጥላቻ ግን አልተሰራንም፡፡ ለምሬትና ይቅር ላለማለት ግን አልተፈጠንም፡፡ እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ጥላቻ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡
ጥላቻ ያለበት ሰው ሰይጣንን እንጂ እግዚአብሄርን ማገልገል አይችልም፡፡ ጥላቻ ለሰይጣን እንደፈለገ ዘርቶ ብዙ ፍሬ የሚያጭድበት ለም መሬቱ ነው፡፡ ስለዚህ ለፍቅር እንጂ ለጥላቻ የምናውለው ምንም ጊዜ የለንም፡፡
መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡31-32
6.     ሰውን ለማስደሰት
የተጠራነው እግዚአብሄርን ለማስደሰት ነው፡፡ ሰው የምናስደስተው እግዚአብሄርን በማሰደሰት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ባለመታዘዝ ሰውን አናስደስትም፡፡ እግዚአብሄር የጠራንን ነገር ማድረግ ትተን ሰውን ለማስደሰት ጊዜውም ጉልበቱም የለንም፡፡
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ወደ ገላትያ ሰዎች 1፡10
ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው፦ እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው። የሐዋርያት ሥራ 4፡19-20
7.     ለምኞት
የእግዚአብሄርን አላማ ለመፈፀም ወደምድር መጥተናል፡፡ የራሳችንን ፍላጎት ለመፈፀም የሚያስችል ጊዜውም ጉልበቱም የለንም፡፡ ለአላማችን የሚበቃ የእግዚአብሄር ፀጋ በእኛ ላይ አለ፡፡ ከዚያ የተረፈ እንደፈለግን ለመኖር እና የራሳችንነ ፍላጎት ለመፈፀም የሚበቃ ትርፍ አቅርቦት የለንም፡፡ ለወንንጌል የከበረ አላማ ተጠርተናል፡፡ ይህንን የከበረ አላማ ትተል ወንጌሉን የልጅነት ምኞታችንን ለማሳካት ህሊናችን አይፈቅድልንም፡፡
እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 16፡18
እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡20-21
እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። 2 ወደ ጢሞቴዎስ 2፡4
8.     ለግምት እና ለሙከራ
እግዚአብሄር በትጋት ይመራናል፡፡ እግዚአብሄር የሚመራንን ምሪት እንከተላለን እንጂ እግዚአብሄር ይህን ይፈልግ ይሆን እያልን በግምት ለመመራት የሚበቃ አቅምም ጉልበትም የለንም፡፡ ህይወታችንን በሙከራ ለማሳለፍ የሚተርፍ ጊዜውም አቅሙም የለንም፡፡ እግዚአብሄር ካላለን ስፍራችንን አንለቅም፡፡ እግዚአብሄር ሳይለን በራሳችን አነሳሽነት ለእግዚአብሄር ለማድረግ የምናባክነው ትርፍ ጉልበትና ጊዜ የለንም፡፡ 
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡14
9.     ለሰው አስተያየት
እግዚአብሄር ብዙ ጊዜ በሰዎች ሲመክረንና ሲመልሰን አይተናል፡፡ በህይወታችን በሰዎች የሚጠቀመውን የእግዚአብሄርን ምሪት እንከተላለን፡፡ ነገር ግን የሰውን አስተያየት ሁሉ በማድረግ በሰዎች አስተያየት ህይወታችንን አንገነባም፡፡ በእግዚአብሄር ምሪት እንጂ በሰዎች አስተያየት ህይወታችንን ለመገንባት የሚበቃ ጊዜ የለንም፡፡ የሰዎች ፍላጎት ስለሆነ ብቻ እግዚአብሄርን ያለንን ለማድረግ የሚያስችል አንድም ትርፍ ቀን በህይወታችን የለንም፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3
10.    ለፍርሃት
የፍርሃት አላማ እኛን እግዚአብሄር ከሰጠን የህይወት ሃላፊነት ማስቆም ነው፡፡ ፍርሃትን ለማስተናገድ ጊዜ የለንም፡፡ ፍርሃት ስሜት አይመጣመ ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን ከመታዘዛችን በፊት ይፍርሃት ስሜቱ መቆም የለበትም፡፡ የፍርሃት ስሜቱ እያለም ቢሆን የእግዚአብሄር ፈቃድ እናደርገዋልን፡፡
አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። የሉቃስ ወንጌል 12፡32
11.     ለማጉረምረም
እግዚአብሄርን በሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ነገር ግን በማጉረምረም እግዚአብሄርን ለማማት ጊዜ የለንም፡፡ ባይገባንም እንኳን ሁለ በሚያውቅና ለእኛ በሚጠነቀቅ በእግዚአብሄር ላይ እንደገፋለን እንጂ በማጉረምረም አባታችንን እግዚአብሄርን ለማስቆጣት ፍላጎቱም ጊዜውም የለንም፡፡
በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡14-15
ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡17-18
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #አገልግሎት #ግምት #ምኞት #አላማ #ምሪት #ማጉረምረም #አስተያየት #ጥላቻ #ቅንጦት #ስንፍና #ጭንቀት #መዋረድ #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #ፍርሃት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment