Popular Posts

Sunday, December 9, 2018

እውነትን የመናገር አስር ጥቅሞች


ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ኤፌሶን ሰዎች 4፡25
1.      እውነት ነፃ ያወጣል
እውነትን የሚናገር ሰው ለሰው ባርነት ሳይሆን ለሰው ነፃነት ይሰራል፡፡ ውሸትን የሚናገር ሰው ግን ሰውን ነፃ የሚያወጣውን እውነት በመከልከል ሰውን በባርነት ለማቆየት የስጋውን ሃሳብ ይከተላል፡፡
እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። የዮሐንስ ወንጌል 8፡32
2.     እውነት አንድ ነው
እውነት ትላንትም ዛሬም ነገም አንድ ነው፡፡ እውነት ምንም ማሳመሪያ አይፈልግም፡፡ እውነት ምንም መሸፋፈኛ እይጠይቅም፡፡ ወሸት ግን ራሱን ችሎ አይቆምም፡፡ ውሸት ሌላ ውሸቶችን ይፈልጋል፡፡ ሌሎቹም ውሸቶች ለጊዜውም ለመቆም ሌላን ውሸት ይፈልጋሉ፡፡
ውሸት በራሱ ደካማ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ውሸት ይታወቃል፡፡ ውሸት ሰውን ያጋልጠዋል፡፡ ውሸት ሰውን ያዋርደዋል፡፡
ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ኤፌሶን ሰዎች 425
የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። የሉቃስ ወንጌል 8፡17
3.     እውነት ቀላል ነው
እውነትን መናገር ህይወትን ያቀላል፡፡ ውሸትን መናገር ግን ህይወትን ያወሳስባል፡፡ ውሸትን መናገር ከባድ የቀን ስራ ነው፡፡ ውሸትን መናገር ውሸቶቹ ሁሉ ተፈጥሮአዊ ስላልሆኑና ሰው ሰራሽ ስለሆኑ እነርሱን ሁሉ ማጥናት ይጠይቃል፡፡ ውሸትን መናገር ከውስጥ ስለማይመጣ ተናጋሪውን ያሰቃየዋል፡፡ ሰው ለውሸት ስላለተሰራ ውሸትን መናገር ሰው ተፈጥሮ ያለሆነውን ነገር ለማድረግ መሞከር ነው፡፡
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። የዮሐንስ ወንጌል 8፡44
4.     ውሸት ሰውን ለማሳሳት ከሰይጣን ጋር መተባበር ነው፡፡
ውሸትን መናገር ሰው በእውነት ላይ ተመስርቶ ትክክለኛ ውሳኔ እንዳይወስን ማሳሳት ነው፡፡
5.     እውነት ከእግዚአብሄር ነው
እውነትን መናገር ሰውን ነፃ ለማውጣት ከእግዚአብሄር መንፈስ ጋር መተባበር ነው፡፡ ውሽት ሰውን ያለ አግባብ ለመቆጣጠር የሚደረግ የስጋ ስራ ነው፡፡ ውሸት ከራስ ወዳድነት የሚመጣ የሃጢያት ባህሪ ነው፡፡
እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። የዮሐንስ ወንጌል 8፡45
6.     እውነት ሃያል ነው
እውነት ጋር የሚቆም ሃያል ነው፡፡ እውነትን የሚናገረው ሰው ራሱን እንጂ እውነትን አይረዳውም፡፡ እውነት የሚይዛት ቢኖርም ባይኖርም እያሸነፈች ትቀጥላለች፡፡
ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡8
7.     እውነት ድፍረትን ይሰጣል
ውሸት ተናጋሪውን ፈሪ በማድረግ እስራት ውስጥ ይከተዋል፡፡ እውነት ግን ተናጋሪውን በመተማመን እንዲኖር ያደርገዋል፡፡
ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል። መጽሐፈ ምሳሌ 28፡1
8.     እውነት ያሳድገናል
እውነትን በተበናገርን ቁጥር ስጋችንን እምቢ ስለምንለው በመንፈስ እያድግን እንሄዳለን፡፡ ውሸት ግን ህይወታችንን ያቀጭጨዋል፡፡
ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ኤፌሶን 4፡15
9.     እውነት የራሳችን የሆነውን ያሳየናል
በከንቱ እንጓጓለን እንጂ ደፍረን እውነቱን የማንናገርለት ነገር የእኛ አይደለም፡፡ በውሸት ለማግኘት የምንጥረው ነገር እግዚአብሄር ያልሰጠንን እራሳችን በትእቢት እጃችንን ዘርግተን ልንወስድ የምንሞክረው የውሸት በረከት ነው፡፡   
10.    እውነትን መነጋገር በረከታችንን ይጠብቀዋል
እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ አትፍሩ። የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤ ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ዘካርያስ 8፡15-17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ውሸት #ሀሰት #ሰይጣን #ዲያቢሎስ #ጠላት #ማታለል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment