Popular Posts

Tuesday, December 18, 2018

የአገልግሎት ስድስቱ ቅድመ ሁኔታዎች

እግዚአብሄርን እንደ ማገልገል የከበረ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄርን ማገልገል ደግሞ በጣት ለሚቆጠሩ ጥቂት ሰዎች የተሰጠ እድል ሳይሆን ለሁሉም ሰው የተሰጠ እድል ነው፡፡ እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄርን እርሱ በሚፈልገው እንጂ እኛ በፈለግነው ሁኔታ አናገለግለውም፡፡ እግዚአብሄርን በማገልገል ፍሬያማ ለመሆን ከእኛ የሚጠይቀው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄርን ማገልገል በእግዚአብሄር ቃል ስርአት እንደሚገባ መሄድን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ነው ብዙ ሰዎች እግዚአብሄርን ያገለግላሉ ነገር ግን ሁሉም እግዚአብሄርን በማገልግል ፍሬያማ አይሆኑም፡፡ እግዚአብሄርን በማገልግል ውጤያማ የሚያደርጉትን ነገሮች ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡  
1.      ቅንነት
እግዚአብሄርን ለማገልገል ቅንነት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ቅንንት ሳይኖራቸው እግዚአብሄርን ለማገልገል የሚሞክሩ ሰዎች እግዚአብሄርንም ራሳቸውን ለማገልገል ሲመክሩ ይወድቃሉ፡፡ እግዚአብሄርን ለማገለገል ለእግዚአብሄር ቃል የዋህ መሆን ይጠይቃ፡፡ እግዚአብሄርን ለማገልገል ለእግዚአብሄር ሃሳብ ሞኝ መሆን ይጠይቃል፡
እግዚአበሄርን ካላመንነው እግዚአብሀርን ማገልግል የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ እንደው በከንቱ እንወጣለን እንወርዳለን እንጂ እግዚአብሄን ማገልግል የምንችለው እግዚአብሄርን ባመንንነት መጠን ብቻ ነው ፡፡
እግዚአብሄር አገልግሉኝ የሚለው ለእኛው ጥቅም እንደሆነ በቅንነት መረዳት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርን መልካምነት በመጠራጠርና ለእግዚአብሄር ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ባለመስጠት የምናገለግለው አገልግሎት ፍሬያማ አይሆንም፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። የማቴዎስ ወንጌል 25፡24-25
2.     ትህትና
እግዚአብሄርን ማገልገል በእግዚአብሄር ፊት ትሁት መሆን ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሄር መንገድና የእኛ መንገድ ሊለያየ ይችላል፡፡ እግዚአብሄርን የምናገለግለው በራሳችን መንገድ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን የምናገለግለው በእርሱ መንገድ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ለመኖር እና እርሱ በሚመርጠው መንግድ እርሱን ለማገልግል ትህትና ይጠይቃል፡፡
እርሱም ብቻ አይደለም ሰውን ለማገልገል ትህትና ይጠይቃል፡፡ የምናገለግለውን ሰው እኛ አንመርጥም፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ሰው ነው የምናገለግለው፡፡ የምናገለግላቸው ሰዎች ከእኛ የተለዩ ሰዎች ናቸው፡፡ የምናገለግላቸው ሰዎች እንደእኛ መረዳት የሌላቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሰውን በማገልገል እግዚአብሄርን ለማገልገል ዝቅ ማለትና ትህትና ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርን ለማገልገል ሌላውን ሰው ከእኛ እንደሚሻል መቁጠርን ይጠይቃል፡፡ ሁሉም ሰው በትህትና አድጎ ጨርሶ ማገልገል አይጀምርም፡፡ እያገለገልንም በትህትና እናድጋለን፡፡ ነገር ግን ትሁት በሆንንበት መጠን ብቻ ነው ጌታን ማገልገል የምንችለው፡፡ 
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡3፣5
3.     ተገኝነት   
ተገኝነት ወይም ራስን መስጠት ለአገልግሎት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ሰው ምንም ያህል ስጦታ ቢኖረው ራሱን ካልሰጥ ምንም ስጦታ እንደሌለው ይቆጠራል፡፡ ሰው ስጦታውን አውጥቶ ለእግዚአብሄር ህዝብ ጥቅም ማዋል የሚችለው ራሱን ለሚያገለግልው ህዝብ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ሰው ራሱን ላለመስጠትም ሰስቶ እግዚአብሄርን ለማገልገልም ፈልጎ ሁለት ወዶ አይሆንም፡፡ ሰው ራሱን ሲሰጥ ብቻ ነው እግዚአብሄር በውስጡ ያስቀመጠውን ፀጋ አውጥቶ ህዝቡን የሚጠቅመው እንዲሁም ስጦታውን የሚያሳድገው፡፡ ሰው በውስጡ ያለውን ፀጋ የሚያሳድገውና በአገልግሎቱ የሚያድገው ራሱን ከሰጠ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ፀጋ ኖሮት ራሱን ካልሰጠው ሰው ይልቅ ያነሰ ፀጋ ኖሮት ራሱን የሰጠው ሰው እግዚአብሄር በሃይል ይጨቀምበታል በአግልግሎቱ  ያሳድገውማል፡፡ ራሱን የያልሰጠን ሰው እግዚአብሄር ሊጠቀምበትና በአገልግሎትም ሊያሳድገው አይችልም፡፡
የጌታንም ድምፅ፦ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም፦ እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። ትንቢተ ኢሳይያስ 6፡8
በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ማነው? መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 29፡5
4.     ታማኝነት
ሰው አገልጋይ እንዲሆን ታማኝነት ይጠበቅበታል፡፡ አግዚአብሄር በሰጠው በትንሽ ነገር የማይታመን ሰው እግዚአብሄርን አገልግላለሁ ቢል ውሸቱን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰው አገልግሎቱ የሚፈተነው በትንኙ ነው፡፡ የሰው አገልግሎቱ የሚለካው በጥቃቅን ነገር ላይ ባለው ታማኝነት ነው፡፡ አንዴ የጀመረውን ነገር እንስከሚጨርሰው ድርስ የሚያመን ሰው ለሚያገልግለው ሰው በረከት ይሆናል እርሱንም በአገልግሎቱ እያደገና ለታላላቅ ሃላፊነት እየተሾመ ይሄዳል፡፡
ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። የሉቃስ ወንጌል 16፡10
5.     እረፍት
አገልግሎት የሚጀምረው ከእረፍት ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ያላረፈ ሰው እግዚአብሄርን አገልግላለሁ ማለት ከንቱ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያላሳረፈው ሰውን ሊያሳርፍ አይችልም፡፡ በእግዚአብሄር አገልግሎት ያልረካ ሰውን ሊያረካ አይችልም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ለእርሱ መልካም እንደሆነ በማወቅ ማረፍ አለበት፡፡ ሰው ከማገልገሉ በፊት እግዚአብሄር ለእርሱ ግድ እንደሚለውና የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንደሚያሟላለት ማወቅ አለበት፡፡ ሰው እግዚአብሄር እረኛው እንደሆነና የሚያሳጣው እንደሌለ በእግዚአብሄር እረኝነት ማረፍ አለበት፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ስራ ሲሰራ እግዚአብሄር የእርሱን ስራ እንደሚሰራለት ያላመነ እና ስለኑሮው የሚጨነቅ ሰው እግዚአብሄርን ማገልገል አይችልም፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚያገለግለው ከጭንቀት ባረፈበት መጠን ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡31፣33
6.     ፍቅር
እግዚአብሄር ለማገልገል እግዚአብሄርን መውደድ ግዴታ ነው፡፡ አገልግሎት ከፍቅር ይመነጫል፡፡ የማንወደውን ሰው ልናገለግለው አንችልም፡፡ የምንወደውን ሰው እንኖርለታለን እናገለግለዋለን፡፡ እግዚአብሄርን ማገልገል ሰውን መውደድ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርንም ማገልገል የማይወዱንንና የማይቀበሉንን ሰዎች ጭምር በእኩልነት መውደድ ይጠይቃል፡፡
ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ። የዮሐንስ ወንጌል 21፡17
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ክርስቶስ #ጌታ #ፍቅር #ታማኝነት #ቅንነት #ተገኝነት #ትህትና #እምነት #እረፍት #ቅድሚያ #እምነት #እውቀት #መደገፍ #ሰንበት #በመንፈሴ #በሃይል #በብርታት #ፀጥታ #መመለስ #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment