Popular Posts

Follow by Email

Saturday, December 15, 2018

ሀገሪቱን የሚጎዱ ሁለቱ ፅንፍ አስተሳሰቦች


ሰብአዊ መብት ማንም ለማንም የሚሰጠው ችሮታ አይደለም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ሲፈጠር የተሰጠው ጥቅም ነው፡፡ ሰብአዊ መብት በማንም መልካም ፈቃደ የሚሰጥ መብት አይደለም፡፡ በነፃነት የማሰብ እና የመናገር መብት በብአዊ መብት በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት ነው፡፡ ሰው ማድረግ የሚችለው ትልቁ ነገር የሰውን ሰብአዊ መብት ማክበር ነው፡፡
ሰሞኑን እየሰማናቸው ያሉት የሰብአዊ መብት ገፈፋዎች እጅግ የሚያሰቅቁ አንገትን የሚያስደፉ ናቸው፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብአዊ መብቱ ሲገፈፍ እንደ ህዝብ ያዋርደናል፡፡ በማንኛውም ሰው ላይ የተደረገ ስቃይ እንደ ህዝብ ዝቅ ዝቅ ያደርገናል፡፡ በእኛ አይነት ፍጡር በሰው ላይ የተደረገ ስቃይ ሁላችንም ያሳንሰናል፡፡  
ግፍን ያደረግ ሰው መጀመሪያ የናቀው በመልኩና በአምሳሉ ሰውን የፈጠረውን እግዚአብሄርን ነው፡፡ ይህን ግፍና ስቃይ በሰው ላይ ያደረጉ ሰዎች ሰውን ከመናቃቸው በፊት የናቁት ሁሉን የሚያየውን እግዚአብሄርን ነው፡፡ ይህን ግፍና መከራ እርዳታ በሌለው ሰው ላይ ያደረጉ ሰዎች መጀመሪያ ያልፈሩትና የተዳፈሩት እግዚአብሄርን እንጂ ሰውን አይደለም፡፡  
ይህንን ግፍና መከራ ያደረጉ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ማዘን ንስሃ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የፍትህ አካላት ተከታትለው ባይደርሱባቸውም እንኳን ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት አለባቸው፡፡ ሰዎች ከሰው ፍርድ ማምለጥ ቢችሉም ከእግዚአብሄር ፍርድ ግን ማምለጥ አይችሉም፡፡ በእግዚአብሄር እጅ ከመውደቅ በሰው እጅ መውደቅ ይሻላል፡፡
እነዚህ ግፍን ያደሬጉ ሰዎች ንስሃ እስካልገቡና ከእግዚአብሄርና ከሰው ንቀታቸው እስካልተመለሱ ድረስ ከሰው ፍርድ ቢያመልጡ ከእግዚአብሄር ፍርድ ግን አያመልጡም፡፡ እነዚህ ሰዎች ሊደግፍ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከእግዚአብሄርና ከሰው የንቀት አስተሳሰባቸውና ስራቸው ስራቸው ጋር በመተባበር የእግዚአብሄርን ፍርድ ለራሱ ያከማቻል፡፡ ግፍን ለሰራው ሰውም ይሁን ሊደብቃቸው ለሚሞክረው ሰው ያለው ብቸኛ አማራጭ ሰዎቹን አሳልፉ በመስጠት ከእግዚአብሄር ቁጣ መዳን እና ማዳን ነው፡፡
እውነት አትለወጥም፡፡ ፍትህ አይለወጥም፡፡ እውነትን እንደምናከብርና ፍትህን እንደምንወድ የምናሳየው ፍትህ ያጓደለው ማንም ይሁን ማን አሳልፈን በመስጠት ነው፡፡ ነገር ግን ፍትህ የምንለው ሌላ ሌላው ሰው ላይ ሲሆን ከሆነና እኛ ላይ ሲደርስ ግን ፍትህ የማይሰራ ከሆነ ውሸተኞች ነን፡፡ በወገንተኝነት ስሜት አላግባብ የምናደርገው ነገር የሚጎዳው ራስን ነው፡፡ ዛሬ በጭካኔ በሌላ ላይ ክፉ የሰራው ሰው ነገ በእኛ ላይ አይሰራውም ብለን ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ በወገንተኝነት ስሜት ፍትህን ማጨለም ከእግዚአብሄ ጋር መጣላት ነው፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡3
እነዚህ ግንፍን ያደረጉ ሰዎች ማንም ይሁን ማንም ካልተመለሱ ግፍ የሚሰራ ጥሩ መንገድ ስለሚመስላቸው ነገ እና ከነገ ወዲያ በሌላው ሰው ላይ እንደማያደርጉት ማንም እርግጠኛ ሊሆን አይችልም፡፡ በእግዚአብሄር እጅ መውደቅ እጅግ አስፈሪ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር እንዳያዋርደው የሚፈልግ ሰው ቀድሞ ራሱን ማዋረድ አለበት፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ ስልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመው ግፍን ፈፅመዋል ብለው የሚጠረጠሩት በአብዛኛው ከአንድ ብሄር የተውጣጡ በመሆናቸው ያንን ብሄር ሁሉ እንደ ግፈኛ ማየት ሌላው ፅንፍ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሚዛናዊነትን መጠበቅ እንጂ ሁለት ስህተት ትክክልን አይሰራም፡፡ ስህተት የሚስተካከል በትክክል እንጂ በስህተት አይደለም፡፡ ብዙ እግዚአብሄርን የሚፈሩ ከግፍ የራቁ ህሊናቸውን ጠብቀው የሚኖሩ የተባረኩ ሰዎች ከሁሉም ብሄር አሉ፡፡ ጥቂቶች ባደረጉት ግፍ ብሄር ሁሉ እንዳደረገው አድርጎ ማቅረብ በብሄሩ ላይ የማይገባ ስጋትን ስለሚጭር ከግፈኞቹ ጋር አላግባብ እንዲተባበር ይፈትነዋል፡፡  
ጥቂት ሰዎች ያደረጉት ግፍ ምክኒያት በሚሊዮኖች የሚቆጠርን ሰው አውጥቶ መጣል ብልህነት አይደለም፡፡ በጥቂት ክፉ ሰዎች ድርጊት በሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብ እንደ ክፉ ህዝብ መፈረጅ በአንድ ብሄር ላይ ስጋትን ከመጨመር ውጭ ለማንም አይጠቅምም፡፡
እንዲሁም ሰዎች በወንጀል ተጠረጠሩ ማለት ወንጀለኞች ናቸው ማለት እንዳይደለ መታወቅ አለበት፡፡ የህግ የበላይነት በሰፈነበት ስርአት ሰው በነፃ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቶ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ንፁህ ሰው ነው፡፡ ሰው ተጠረጠረ ማለት ተፈረደበት ማለት አይደለም፡፡
ሰው ለምን ተጠረጠረ ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ሰው እንዲፈረድበት ንፁሁም ሰው ይሁን ጥፋተኛም ሰው ሊጠረጠር ይገባዋል፡፡  
እነዚህም ግፍን ያደረጉ እና ንስሃ ያልገቡ ሰዎች መሸሸግ የሚፈልጉት በዚህ ሁለት ፅንፍ አስተሳሳብ ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ግፍን የፈፀሙ ሰዎች ለፍርድ ሲፈለጉ አንድ ብሄር ላይ የተነጣጠረ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ለማስመሰል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እነዚህ ግፍ የፈፀመሙ ሰዎች ድል ሰው ግፍ ባደረገው ግለሰብ ላይ ማተኮርን ትቶ አለአግባብ በህዝብ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፍትህ #ፅንፍ #ስጋት #ፀሎት #ፍርድቤት #ህግአውጪ #ህግአስፈፃሚ #ምክርቤት #ፖሊስ #ዲሞክራሲ #ህግተርጉዋሚ #ተቃውሞ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment