Popular Posts

Saturday, December 31, 2016

አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን

እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
በሃጢያት ምክኒያት የሰው ቅድሚያ አሰጣጥ ተዛብቷል፡፡ ይህ ቅደም ተከተል ካልገባው የሰው ህይወት ከንቱ ሩጫ ነው፡፡ ሰው ይህን ቅደም ተከተል ካላስተካከለ በህይወቱ የሚስተካከል ምንም ነገር አይኖርም፡፡  
ኢየሱስም አለ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት አትጨነቁ፡፡ መብላትና መልበስ የህይወት አላማችሁ አይሁን፡፡ መጠጣትና መልበስን እንደ ራእይ አትያዙት፡፡ መብላትና መጠጣትን መከተል አይመጥናችሁም፡፡ መብላትና መልበስን መፈለግ የእግዚአብሄር ቤተሰብ አባልነት ክብራችሁ አይመጥነውም፡፡ ከመብላትና መጠጣት ያለፈ ክብር ያላችሁ ሰዎች ናችሁ፡፡ ከመጠጣትና ከመልበስ እጅግ የላቅ ጥሪ አላችሁ፡፡ የሚበላና የሚጠጣ ከመፈለግ የተሻለ ክብር አላችሁ፡፡
መብላትና መጠጣትን መፈለግ ክብር አይደለም፡፡ የሚበላውና የሚለበሰውን መፈለግ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ መብላትና መልበስን ማንም ሰው ፣ ማንም መንገደኛ ፣ ማንም ተራ ሰው ይፈልገዋል፡፡
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ማቴዎስ 6፡32
እግዚአብሄር አያስፈልጋችሁም እያለ አይደለም፡፡ ይህ ለኑሮ እንደሚያስፈልግ አባታችሁ ያውቃል፡፡ እግዚአብሄርን አታስረዱትም፡፡ ስለ ባተሌነታችሁ ለእግዚአብሄር የሚበላና የሚጠጣ ለመፈለግ ነው ብላችሁ ለእግዚአብሄር ምክኒያትን አትሰጡትም፡፡
ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና።
እግዚአብሄር እያለ ያለው የሚበላ የሚጠጣ የሚለበስ መፈለግ ድርሻችሁ አይደለም፡፡ አስቀድማችሁ ድርሻችሁን አድርጉ፡፡ አስቀድማችሁ የሚመጥናችሁን አድርጉ፡፡ አስቀድማችሁ የተጠራችሁትን አድርጉ፡፡ አስቀድማችሁ የቤተሰቡን ክብር ጠብቁ፡፡ አስቀድማችሁ መንግስቱን ተንከባከቡ፡፡ አስቀድማችሁ መንግስቱን ፈልጉ፡፡
ይህ ሁሉ ይጨመርላችኋል፡፡ ይህ ሁሉ ተጨማሪ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ምርቃት ነው፡፡ ይህን ሁሉ እስከማትፈልጉ ድረስ እግዚአብሄር የድርሻውን ያደርጋል፡፡ እግዚአብሄር ያቀርባል፡፡ ይጨመርላችኋል፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱ

ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ሮሜ 11፡36
ሁሉ ከእርሱ
መልካምነት ሁሉ ከእርሱ ነው፡፡ እኛም ከእርሱ ነን፡፡ የሚያቀርበው እርሱ ነው፡፡ መልካንም ነገር ለማድረግ የሚያስፈልገውን መነሳሳት እንኳን የሚሰጠን እርሱ ነው፡፡ ድፍረትን የሚሰጠን ራሱ ነው፡፡ የሚያበረታን እርሱ ነው፡፡ ሁሉ ከእረሱ ነው፡፡
ሁሉ በእርሱ ነው
ከእግዚአብሄር ጋር አብረን የምንሰራ ነን፡፡ እርሱ ሲሰራ እንተባበረዋለን፡፡ እርሱ እየሰራ ነው፡፡ በእድል የሆነ ነገር የለም፡፡ ሁሉንም የነደፈው እርሱ ነው፡፡ የሚጀምረውና የሚመራንና እርሱ ነው፡፡ እርሱ የሚሰራበትን ፈልገን እንተባበረዋለን፡፡ በእኛ ሃይል ለእግዚአብሄር አንኖርም እግዚአብሄርንም በራሳችን ሃይል አናገለግልም፡፡ ሁሉ በእርሱ ነው፡
የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡9
ሁሉ ለእርሱ ነው
ሁሉንም እንዴት ለራሱ ክብርና ለእኛ ጥቅም እንደሚለውጠው ያውቃል፡፡ ሁሉ ለእርሱ ክብር ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማንም መጠቀሚያ ሊያደርገው አይችልም፡፡ እንዴት የሁሉንም ነገር መጨረሻ ለራሱ አላማ እንደሚለውጠው ያውቃል፡፡ ክብሩንም ሁሉ መውሰድ ያለበት እግዚአብሄር ነው፡፡
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ሮሜ 8፡28
ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ሮሜ 1136
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#በእርሱ #ለእርሱ #ከእርሱ #ክብር #አላማ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ብቸኛው መመዘኛ

ለእግዚአብሄር ክብር እንደመፈጠራችን መጠን በህይወታችን ለእግዚአብሄር ብቻ መኖር እንፈልጋለን፡፡ የልባችን ጩኸት በእግዚአብሄር በልብና በሃሳቡ እንዳለ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አድርጎ ማለፍ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ምኞት የለንም፡፡  ዳዊት በዘመኑ የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግሎ አንቀላፋ ተብሎ እንደተመሰከረለት እንዲመሰከርልን እንፈልጋለን፡፡ በምድር ላይ የሚያረካን ለእግዚአብሄር ክብር መኖር ብቻ ነው፡፡
ታዲያ በስኬት ማገልገላችንና አለማገልገላችን የሚለካው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አገልግለን በህይወት እንድናርፍ ያደርገናል፡፡ ከእኔ ምንድነው የሚጠበቀው? ከእኔስ ምንድነው የማይጠበቀው? የሚለውን ጥያቄ መልስ ማወቅ ሃላፊነታችንን በትኩረት እንድንወጣ ያስችለናል፡፡
አንድ ቀን ጉዞዋችንን ዞር ብለን ስናየው ለእግዚአብሄር በሚገባ የተኖረ ህይወት እንድናይ እንፈልጋለን፡፡ በመጨረሻ እግዚአብሄር "መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ" እንዲለን እንጠብቃለን፡፡
ግን እግዚአብሄር ህይወታችንን የሚመዝነው በምንድነው? መመዘኛው መስፈርት ምንድነው ?
እግዚአብሄር አፈፃፀማችንን የሚለካው ስለታማኝነታችን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን ስለሰጠን በእጃችን ላይ ስላለው ስጦታ እንጂ ስላልሰጠን ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀን በህይወታችን ስላስቀመጠው ስለሰጠን መክሊት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠይቀው እንዴት እግዚአብሄር ላይ በመደገፍ በታማኝነት የሰጠንን ነገር ማስተዳደራችንን ብቻ ነው፡፡
ጊዜ
የሰጠንን ጊዜ እንዴት በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ይጠይቀናል፡፡ እግዚአብሄር በቀን ስለሰጠን 24 ሰአት እንጂ ስላልሰጠን 25 ሰአት አይጠይቀንም፡፡ የሰጠንን 24 ሰአት ግን እንዴት ለእግዚአብሄር ክብር እንደተጠቀምንበትና እግዚአብሄር በህይወታችን ላስቀመጠው ራእይና ሃላፊነትና እንዳዋልነው ታማኝነታችን ይለካል፡፡ እግዚአብሄር ያለው አንድና ብቸኛ መመዘኛ ታማኝነት ነው፡፡   
እውቀት
እግዚአብሄር የሰጠንን እውቀት ካለመሰሰት ለእግዚአብሄር መንግስት ተጠቅመንበታል? እግዚአብሄር እንዴት እውቀታችንን በታማኝነት እንደተጠቀምንበት ይለካል፡፡ ለተገለጠልን የፈቃዱ እውቀት ምን ያህል እየኖርን እንደሆነ ይፈትናል፡፡ ስላልተረዳነውና ስለማናውቀው የእግዚአበሄር ፈቃድ እንጠየቅም፡፡
የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡47-48
ገንዘብ
እግዚአብሄር ለመዝራትና ለመብላት የሰጠንን ገንዘብ እንዴት እያስተዳደርን እንዳለን እንጂ ስለሌለን ስለ ቢሊዮን ብር  አይጠይቀንም፡፡ የሰጠንን እንዴት እንዳዋልነው ግን ይጠይቀናል፡፡
እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡7፣10
ጉልበት
እግዚአብሄር የሰጠንን ማንኛውም ሃይል እንዴት እንደተጠቀምንበት ታማኝነታችንን ማየት ይፈልጋል፡፡ ያለንን ሃይልና ተሰሚነት የተጠቀምንበት ለመገንባት ይሁን ለማፍረስ ታማኝነታችንን ይለካል፡፡ ያለንን ሃይልና ጉልበት ለራሳችን ራስወዳድነት ወይም ለፍቅርና ለሌሎች ጥቅም እንዳዋልነው ማወቅ ይፈልጋል፡፡  
የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። 1ኛ ጴጥሮስ 4፡11
የስኬታችን አንዱና ብቸኛው መመዘኛው እግዚአብሄር የሰጠን ማንኛውም መክሊት በመልካም የማስተዳደር ታማኝነታችን ነው፡፡
ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡21
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ታማኝነት #መክሊት #ጊዜ #ጉልበት #እውቀት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, December 30, 2016

እግዚአብሄርን የማመስገን መልካምነት

እግዚአብሄርን ለማመስገን ብዙ ምክኒያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሄርን ለማመስገን የሁሉም ሰው የጋራ ምክኒያት የሆነው አንድ ምክኒያት ነው፡፡ ሰው ሌላ ምክኒያት ቢያጣ እንኳን በዚህ ምክኒያት እግዚአብሄርን ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡ ሰው ምክኒያት ቢያጣ እንኳን ይህ ምክኒያት እግዚአብሄርን ለማመስገን በቂ ነው፡፡
መፅሃፍም ቅዱስም ይህን ምክኒያት እግዚአብሄርን ለማመስገን ምክኒያት አድርጎ ደጋግሞ ፅፎታል፡፡
እግዚአብሄር መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁለንተናው መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄር አይለወጥም ሁልጊዜም መልካም ነው፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ያዕቆብ 1፡16-17
የመልካምነት ትርጉሙ ቢያከራክር እንኳን ለመልስ እግዚአብሄርን ማየት በቂ ነው፡፡ እግዚአብሄር የመልካምነት ማጣቀሻ (Refrence) ነው፡፡ ሰው በሚያነበው መፅሃፍ ላይ ያለን ቃል ትርጉም ባይረዳ ማጣቀሻን ይፈልግና የቃሉን ትርጉም ያያል፡፡ እንደዚሁ የመልካምነት ትርጉሙ ቢያጠራጥር እግዚአብሄር ጋር መልሱ አይታጣም፡፡
እግዚአብሄር መልካም ብቻ ሳይሆን የመልካምነትም ደረጃ መዳቢ ነው፡፡ እሱ መልካም ያለው መልካም ነው እርሱ መልካም አይደለም ያለው መልካም አይደለም፡፡ ስለ መልካምነት የመጨረሻው ወሳኝ አካል እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያርመው የለም፡፡ እግዚአብሄርም ማንንም አያማክርም፡፡
እግዚአብሄርን መልካም ስለሆነና ምንም የማይወጣለት ፍፁም መልካም ስለሆነ እግዚአብሄርን ማመስገን መልካም ነው፡፡ ሰው በምንም ነገር ቢሳሳት እግዚአብሄርን ስለማመስገኑ በጭራሽ አይሳሳትም፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ምንም የሚወጣለት ነገር የለም፡፡  
እግዚአብሄር መልካም ስለሆነ ምስጋና ይገባዋል፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ይገባል፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ውበት አለው፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ያማረ ነው፡፡
እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው። መዝሙር 147፡1
ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፤ መዝሙር 135፡1፣3
እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤ በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ። መዝሙር 92፡1-3
ሃሌ ሉያ። ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ መዝሙር 107፡1
ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና። መዝሙር 118፡ 1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #አመስግኑ #መልካም #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #አብርሃም #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

Thursday, December 29, 2016

የወዳጅነት ጥበብ

በሰው ህይወት ውስጥ በጣም ከፍተኛ ስፍራ ካላቸው ነገሮች አንዱ ወዳጅነት ነው፡፡  
ወዳጅነት የሌላውን ስሜት መረዳት ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት የሌላን ድንበር ማክበር ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት አንዱ ሌላውን ማገልገልን ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት አንዱ የአንዱን ሸክምን መሸከምን ይጠይቃል፡፡
ሰው የራሱ የግሌ የሚለው ክልል አለው፡፡ ሰው ለራሱ ብቻ የሚያስቀረው ሚስጥር ሊኖረው ይችላል፡፡ ሰው ለራሱ ብቻ የሚፈቅደው ግላዊነት ይኖረዋል፡፡ ያንን የግል ክልል ማክበር ወዳጅነትን ያጠናክራል፡፡
ወዳጅነት አንዱ ለሌላው መድረስን ያካትታል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ እንደሚወድ ያስተምረናል፡፡  
ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል ምሳሌ 17፡17
ወዳጅነት ሃላፊነት ነው ፡፡ ወዳጅነት ማካፈል ነው፡፡ ወዳጅነት ለሌላው መገኘት ነው፡፡ ወዳጅነት መስጠት ነው፡፡ ሰው ለሁሉም ሊሰጥ አይችልም፡፡ ለሁሉም ሊሰጥ የሚፈልግ ሰው ለማንም ሳይሰጥ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ መርጠን በመልካም በወዳጅነት ላይ ኢንቨስት እንድናደርግ የሚያስተምረን፡፡
ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ። ምሳሌ 1824
ወዳጅነት በአንድ ዘመን ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ወዳጅነት ለትውልድ ይተላለፋል፡፡ አንዳንዴ ከዘመድ ይልቅ ወዳጅ ቀድሞ ይደርሳል ይጠቅማልም፡፡
ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል። ምሳሌ 2710
ወዳጅነት በመተማመን ላይ ብቻ ይመሰረታል፡፡ ስለዚህ ነው ወዳጅነት በአንድ ለሊት የማይገነባው፡፡ አንዱ ለሌላው ያለውን መሰጠት በማየት ነው አንዱ ለሌላው ራሱን የሚሰጠው፡፡ ወዳጁ ያለውን ታማኝነት በማየት ነው በታማኝነት ራሱን ለወዳጅነቱ ቀስ በቀስ የሚሰጠው፡፡ ወዳጅነትን ሊያፈርስ የሚመጣውን ነገር በጥንቃቄ መከታተል ይጠይቃል፡፡
ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል። ምሳሌ 1628
ወዳጅ በመልካም መንገድ በወዳጁ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ ትጉህ ወዳጅ ወዳጁን ትጉህ ያደርገዋል፡፡ አስተዋይ ወዳጅ ወዳጁን ማስተዋል እንዲጨምር ይረዳዋል፡፡ እንደ ወዳጅ በወዳጁ ላይ ተፅእኖ ለማድርግ ሰፊ እድል ያለው የለም፡፡
ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። ምሳሌ 13፡20
ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። ምሳሌ 27፡17
ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፤ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች። ምሳሌ 12፡26
ወዳጅ ያሳርፋል፡፡ ወዳጅ ያስደስታል፡፡
ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል። ምሳሌ 27፡9
በተቃራኒው ደግሞ ከክፉ ባልንጀርነት መሸሽ ህይወትን ይጠብቃል፡፡ በባልንጀርነት አመል እንዳይበላሽ መጠንቀቀ ያስፈልጋል፡፡
ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋር አትሂድ፥ መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። ምሳሌ 22፡24-25
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡33
ወዳጅነት ምህረት ይቅር ማለት መሸከም ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው የማንወድለት ይህን ቢያስተካክል የምንለው ነገር አለው፡፡ ሁሉም ነገሩ የሚያስደስተን ሰው በምድር ላይ የለም፡፡ ስለዚህ ሌላውን መሸከም የሰውን መልካምነት እንድንጠቀም ያስችለናል፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ግን መለየት ነው የሚፈልገው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ወረተኛ ነው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው በወዳጅነት አይፀናም፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ከወዳጅነት በላይ ሌሎች ጥቅሞችን በማስቀደም ታላቁን ስጦታ ወዳጅነትን ይጥላል፡፡
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፡1
ወዳጅነትን የሚያከብር ሰው በምህረት ይመላለሳል፡፡ ለወዳጅነት ዋጋ የሚሰጥ ሰው ወዳጅነትን የሚያጠፋውን ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃል ዋጋም ይከፍላል፡፡
ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል። ምሳሌ 17፡9
ወዳጅነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወዳጅ ወዳጁን እጅግ በጣም ከማመኑ የተነሳ ከጠላት መሳም ይልቅ የወዳጅ ማቁሰል እንኳን ተቀባይነት አለው፡፡
የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው። ምሳሌ 27፡5-6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ወዳጅ #ጓደኛ #መታመን #ጥበብ #ፍቅር #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, December 28, 2016

የዝምታ አምልኮ

ከእግዚአብሄር ጋር ላለን ግንኙነት መጠናከር ጠቃሚ ከሆኑ የተለያዩ የጥሞና መንገዶች አንዱ ዝምታ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ስምረት የሚለካበት አንዱ መንገድ ዝምታ ነው፡፡
ስጋ ሁል ጊዜ መናገር ይፈልጋል፡፡ ስጋ የሚረካው በመናገር ነው፡፡ ስጋ በህይወት የመጡትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚሞክረው በመናገር ብዛት ነው፡፡ ስለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ አልናገርም ብለን ስንወስን ስጋ ከውስጣችን ሲጮህና ሲቃወም የምንሰማው፡፡ ስጋ ራሱን የሚያረካው በመናገር ነው፡፡
ስጋ ዝም ማለትና ማረፍ አይፈልግም፡፡ ስጋ ነገሮችን በንግግር መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ጊዜ መስጠት አይፈልግም፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ስፍራን በመስጠት በዝምታ መጠበቅ አይፈልግም፡፡ ስጋ ዝምታን እንደ ሽንፈትና እንደ አቅመቢስነት ነው የሚያየው፡፡ አንደበቱን መግታት የማይችል ብዙ የሚለፈልፍ ሰው ካያችሁ በስጋው የተሸነፈ ሰው ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
ፀጥታ የመታመን ምልክት ነው፡፡ ፀጥ የሚለው እግዚአብሄር የልብን ጩኸት ይሰማል የሚል ሰው ነው፡፡ ፀጥ የሚል ሰው የህይወት ቁልፉ እግዚአብሄር ጋር እንጂ ሰው ጋር እንደሌለ የሚያምን ሰው ነው፡፡ ፀጥ የሚል ሰው የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ እንደማይሰራ (ያዕቆብ 1፡20) የተረዳ ሰው ነው፡፡ ያልታመነ ሰው ይናወጣል፡፡ ያላመነ ሰው በፀጥታ መቀመጥ አይችልም፡፡
የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ ኢሳይያስ 30፡15
ሳንናወጥ በዝምታ እግዚአብሄርን መጠበቅ በእግዚአብሄር ላይ መደገፋችንን ያሳያል፡፡ በፀጥታ እግዚአብሄርን መጠበቃችን ለእግዚአብሄር ስፍራን መስጠታችንን ያሳያል፡፡ በፀጥታ መቀመጣችን "ካለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና" (ዮሐንስ 15፡5) ያለውን ቃል በማመን በእርሱ ላይ እርፍ ማለታችንን ያሳያል፡፡ ፀጥታችን እግዚአብሄር ምድርን እንደሚገዛ ማመናችንን ያሳያል፡፡
ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ። መዝሙር 46፡10
በዝምታ የሚኖር ሰው ሃይሉን ባላስፈላጊ መናወጥ አያባክንም፡፡ በእርግጥም በዝምታ እግዚአብሄርን የሚጠብቅ ሰው ሃይሉን እንደንስር ያድሳል፡፡
እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡31
የምናድርበት መንገድ ነው፡፡ ዝምታ ለእግዚአብሄር የምናመልክበት መንገድ ነው፡፡ ዝምታ ለእግዚአብሄር የምንገዛበት መንገድ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ልንከተለው ስለሚገባው ስለኢየሱስ ዝምታ መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ማቴዎስ 12፡18-19

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ዝምታ #ማረፍ #መታመን #መደገፍ #ፀጥታ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Tuesday, December 27, 2016

Life is like a Cup of Coffee (Author Unknown)

A group of alumni, highly established in their careers, got together to visit their old university professor. Conversation soon turned into complaints about stress in work and life.
Offering his guests coffee, the professor went to the kitchen and returned with a large pot of coffee and an assortment of cups – porcelain, plastic, glass, crystal, some plain looking, some expensive, some exquisite – telling them to help themselves to the coffee.
When all the students had a cup of coffee in hand, the professor said: “If you noticed, all the nice looking expensive cups have been taken up, leaving behind the plain and cheap ones. While it is normal for you to want only the best for yourselves, that is the source of your problems and stress.
Be assured that the cup itself adds no quality to the coffee. In most cases it is just more expensive and in some cases even hides what we drink. What all of you really wanted was coffee, not the cup, but you consciously went for the best cups… And then you began eyeing each other’s cups.
Now consider this: Life is the coffee; the jobs, money and position in society are the cups. They are just tools to hold and contain Life, and the type of cup we have does not define, nor change the quality of life we live.
Sometimes, by concentrating only on the cup, we fail to enjoy the coffee. Savor the coffee, not the cups!
The happiest people don’t have the best of everything. They just make the best of everything. Live simply. Love generously. Care deeply. Speak kindly.
For More Articles https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#God #Jesus #life #rejoice #trustgod #grace #salvation #church #testimony #rejoice #preaching #Bible #theword #Abiydinsa #scriptures #abiywakumadinsa

ህይወት እንደ ሲና ቡና

(Life is Like a cup of coffee) ከሚለው የተተረጎመ  
ከኮሌጅ የተመረቁና በስራቸውም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ባለሙያዎች የድሮ የዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰራቸውን ለመጎብኘት በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ ውይይቱ በፍጥነት በስራና በህይወት ውጥረት ላይ ወደ ማጉረምረም ተለወጠ፡፡
ፕሮፌሰሩ ለእንግዶቹ ቡና ለማቅረብ ወደ ኩሽና ሄዶ አንድ ትልቅ ጀበና ቡናና አንዳንዱ ልሙጥ ፣ አንዳንዱ ውድአንዳንዱ የሚያምር ከሸክላ የተሰራ ሲኒ ፣ ከፕላስቲክ የተሰራ ሲኒ ፣ ከብርጭቆ የተሰራ ሲኒ ይዞላቸው መጣና ራሳቸውን አንዲያስተናግዱ ነገራቸው፡፡
ሁሉም ተማሪዎች አንድ አንድ ቡና ሲኒ እንደያዙ ፕሮፌሰሩ እንዲህ አለ: "አስተውላችሁ ከሆነ ርካሾቹና ልሙጦቹ ሲኒዎች ተትተው  የሚያምሩትና ውዶቹ ሁሉም ሲኒዎች ተወስደዋል፡፡ ለራሳችሁ ምርጥ ነገር መፈለጋችሁ የሚጠበቅ ቢሆንም የህይወታችሁ ውጥረትና ችግር ምንጭ ይኸው ነው፡፡
ሲኒው ለቡናው ጥራት ምንም አስተዋፅኦ አያደርግም፡፡ አንዳንዴ እንዳውም ብዙ ብር ያስወጣል፡፡ አንዳንዴም የምንጠጣውን ቡና ይደብቀዋል፡፡ ሁላችሁም በእርግጥ የሚያስፈልጋችሁ ቡናው እንጂ ሲኒው አይደለም፡፡ ነገር ግን አስባችሁ ምርጡን ሲኒ አነሳችሁ፡፡  ከዚያም በኋላ አንዳችሁ የሌላችሁን ሲኒ ማየት ጀመራችሁ፡፡
ተመልከቱ ሕይወት ቡናው ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለን ስራ ፣ ገንዘብ እና የህይወት ደረጃ አቋም ሲኒዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሲኒዎች ሕይወትን የሚይዙ መያዣዎች እቃዎች እንጂ ህይወት አይደሉም፡፡ የምንጠጣበት ሲኒ ቡናውን ሊገልፀው አይችልም ወይም የምንኖረውን ህይወት ጥራት አይለውጠውም፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሲኒው ላይ ብቻ በማተኮር በቡናው መደሰት ያቅተናል፡፡ ቡናውን አጣጥም እንጂ ሲኒውን አይደለም! 
እጅግ ደስተኛ ሰዎች ሁሉ ምርጥ ነገር ሁሉ የላቸውም፡፡ ነገር ግን ካላቸው ነገር ምርጥ ነገርን ማውጣት ይችላሉ፡፡
በቀላሉ ኑር ፣ በልግስ ውደድ ፣ ለሌላው በሚገባ አስብ በደግነት ተናገር፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ራስንማማጠን #ደስተኝነት #ያለኝይበቃኛል #ህይወት #ዘላለም #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, December 24, 2016

ወንድ ልጅ

ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9፡6
ኢየሱስ የእግዚአብሄር ድንቅ ስጦታ ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ምድር ሲወለድ ከተገለፀበት ስሞች መካከል አንዱ ይህ ነበር፡፡
ኢየሱስ በምድር ላይ የነበረውን ጨለማ የመግፈፍ ታላቅ ሸክምን በጫንቃው ላይ ተሸክሞ ነበር ወደምድር የመጣው፡፡ ሰው ሁሉ የእግዚአብሄርን አላማ በማይረዳበትና በጠላት የማታለል እስራት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ኢየሱስ ብቻ ነበር ለእውነት ሊመሰክልር ወደ ምርድ የመጣው፡፡
ጲላጦስም፦ እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። ዮሃንስ 18፡37
በብቸኝነት በምድር ላይ የተገኘውና ሰዎችን ወደ እውነት ለመምራት ሸክምና ሃላፊነትን የወሰደው፡፡ ስለዚህ ነው ኢየሱስ የአለምን ህዝብ ወደ እውነትና ወደ ብርሃን የመምራት ሃላፊነት በጫንቃው ላይ የነበረው፡፡
ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው። ዮሃንስ 8፡12
ኢየሱስ ከተገለፀባቸው ስሞች ማዕረጎችና መካከል ድንቅ መካር የሚለውም ይገኝበታል፡፡ ኢየሱስ እውነትም መካሪ ነው ያውም ድንቅ መካሪ፡፡ በህይወት በተጨንቅንበት ጊዜ መውጫው በጨነቀን ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባን ግራ በገባን ጊዜ ምን ማድርግ እንዳለብል መውጫውን የሚያሳየን ኢየሱስ ነው፡፡ መንገዱ በጠፋብን ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ መንገድ ነው፡፡ ግራና ቀኙን የማያውቀው ሰው ኢየሱስ ሲገናኘው ምን ማድረግ እንዳለበት ማወቅ ይጀምራል፡፡  
ኢየሱስ ከዘላለም በፊት የነበረ የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ ምንም በምድር የእኛን የሃጢያት እዳ ለመክፈል ሰው ሆኖ ቢመጣም ኢየሱስ ግን ከዘላለም የነበረ ኃያል አምላክ ነው፡፡ በሰው ምክኒያት ሃጢያት ወደ ምድር እንደገባ ሁሉ በሰው ምክኒያት የሃጢያት ሃይል መሻር ሰለነበረበት ኢየሱስ እንደ ሰው በስጋና በደም ተካፈለ እንጂ ኢየሱስ ምድርን የፈጠረ ለአላማው የጨከነ ሃያል አምላክ ነው፡፡ ለማዳን ብርቱ በምንም የማይበገር አለምን ያሸነፈ ሃያል አምላክ ነው፡፡
እውነተኛ አባትነትን ያሳየን ኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስ እውነተኛ አሳቢ ፣ የሚጠነቀቅልን ፣ መሪያችን ፣ ታጋሽ አባት ነው፡፡ የአባት ትርጉሙ ከጠፋብን ከኢየሱስ ጋር በተገናኘን ጊዜ የአባትን ትርጉም በቅጡ እንረዳለን፡፡ የአባትነት ድርሻና ሃላፊነት ክርክር ቢነሳ ሊፈታው የሚችል አባትነቱን ያስመሰከረ ኢየሱስ ነው፡፡
ኢየሱስ የሰላም አለቃ ነው፡፡ እውነተኛ ሰላምን የፈለገ ሰው ወደ ሌላ መመልከት የለበትም፡፡ የሰላምን ትርጉም ያጣ ሰው እውነተኛ የሰላምን ትርጉም የሚረዳው በኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስ የሚሰጠው ሰላም አለም እንደሚሰጠው ሰላም አይነት አይደለም፡፡ ኢየሱስ የሚሰጠው ሰላም አእምሮን የሚያልፍ ሰላም ነው፡፡ ኢየሱስ የሚሰጠው ሰላም ከአለም ጩኸትና ትርምስ በላይ የሚሰማ ልብን የሚያሳርፍ ሰላም ነው፡፡
አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ፊልጵስዩስ 4፡7
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃንስ 14፡27
ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9፡6
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ሰላም #ድንቅመካር #ሃያልአምላክ #የሰላምአለቃ #ዘላለምአባት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አለቅነት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, December 23, 2016

መንፈሳዊ ጤንነታችን የምንለካባቸው 12 መንገዶች

የክርስትና ህይወታችንን ስኬት የምንመዝነው የተመገብነውን ምግብ ጤንነት በማየት ነው፡፡ የምንሰማው ነገር ጤናማ ካልሆነ ህይወታችን የተሳካ ቢመስለን እንኳን እየቀጨጭን እንደሆንን ማወቅ አለብን፡፡ የምንበላውን ምግብ ጤንነት እርግጠኛ ከሆንን ደግሞ እያደግን እየለመልምን እንደሆነ እርግጠኛ እንሆናለን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡13
የምንመገበውን ምግብ ጤንነት ለመገምገም የሚረዱ አስራ ሁለት መመዘኛዎች

·         የምሰማው ጤናማ ትምህርት በፍቅር እንድኖር ያበራታታል
የምንሰማው ትምህርት በፍቅር እንድኖር የማያበረታታ ከሆነና ፍቅርን በሌሎች መሰል ነገሮች የተካ ከሆነ ጤነኛ ምግብ እንዳልተመገብን ምልክቱ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ በፍቅር ካልኖርንና ካላገለገልን በሁኔታዎች ተቋቁመን ማለፍና እግዚአብሄር የጠራንን የመንግስቱን ስራ ለረጅም ጊዜ ማገልገል ያቅተናል፡፡ የማንኛውም ትምህርት አላማ በፍቅር እንድኖር ማድረግ ነው፡፡    
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡5
·         የምንመገበው ጤናማ ትምህርት በእግዚአብሄር እንዳምን ይረዳል  

የምመገበው ምግብ በእምነት እግዚአብሄርን እንዳይ የሚታየውን የምድራዊውንና ጊዜያዊውን ነገር እንዳላይ ካበረታታኝ ጤነኛ ምግብ እንደተመገብኩ ማረጋገጫው ነው፡፡ 

የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18

·         ጤናማ ትምህርት በትዕቢት እንድናስብ አያደርግም

አንዳንዴ የምንሰማው ትምህርት ራሳችንን በትክክል እንዳናይ ይጋርደናል፡፡ ትምህርቱ ከሆንነው በላይ በትቢት እንድናስብ ያደርጋል፡፡ ጤናማ ትምህርት ግን ከፍ ባልን ቁጥር ይበልጥ ትሁት እንድንሆን ያደርጋል፡፡ የምንሰማው ትምህርት ሌሎችን በአክብሮት እንድንይዝ ካላበረታታና ሌሎችን እንድንንቅ ካደፋፈረን የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡

እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ሮሜ 12፡3

·         ጤናማ ትምህርት ሰማያዊ ነገር ላይ እንዳተኩር ያደርጋል

የምንመገበው መንፈሳዊ ምግብ ሃሳባችን ምድራዊ እንዲሆ ካደረገ በልባችን ያለው ብርሃን እንዳያጠፋው መጠንቀቅ አለብን፡፡ የምንበላው ምግብ የሰማይን ሃሳብ ይበልጥ የሚያጎላው ካልሆነና በላይ ያለውን እንድንፈልግ ካልረዳን  ምግባችንን በፍጥነት መቀየር አለብን፡፡ 

እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ቆላስይስ 3፡1-2

·         ጤናማ አስተምሮት ለስኬትና ለብልፅግና እንድቸኩል አያደርግም
የምንማረው ትምህርት የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን እንድፈልግ ካላበረታታ ይልቁንም ለሁለት ጌቶች ለገንዘብና ለጌታ እንድንገዛ ካበረታታ እንዲሁም ስለኑሮ እንድንጨነቅ ካደረገ የተመገብነው ትምህርት ጤናማነት ያጠራጥራል፡፡ በታማኝነት የሚባርከውን የእግዚአብሄርን እርምጃ እንዳንታገስ ካደረገና በፍጥነት መበልፀግ እንደምንችል ካስተማረ የስህተት ትምህርት ነው፡፡ ጤናማ ትምህርት ያለኝ ይበቃኛል እንድንል ያሳርፋል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20


·         ጤናማ ትምህርት መስማት በይቅርታና በምህረት እንድመላለስ ያደርጋል

የምመገበው ምግብ ሰዎችን እንድጠላ የሚያበረታታ ከሆነና በልቤ ቂምና ምሬትን እንዳልይዝ ካልገሰፀኝ ጤነኛ ትምህርት እየተመገብኩ አይደለም ማለት ነው፡፡ ጥላቻ የመንፈሳዊ ህይወትን ጤና የሚያስተጓጉል መርዝ በመሆኑ  የበደለንን ሁሉ ይቅር ማለት እንደምንችል የማያስተምር አስተምሮት ጤናችን እንዲጓደል ያደርጋል፡፡

መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። ኤፌሶን 4፡31-32

·         ጤናማ ምግብ ለአገልግሎት ያነሳሳል 

የተወለድነው ወደ እግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ ነው ፡፡ የክርስቶስ አካል ደግሞ ህያውና ሰራተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የበላነውን ምግብ ጤነኝነት የምንመዝነው ከፊት ይልቅ ለአገልገሎት በመነሳታችን ነው፡፡ ለአገልግሎት ያለን ፍላጎት እየወረደ ከሆነ ጤነኛ ምግብ እየበላን አይደለንም፡፡ የምንመገበው ምግብ የአገልግሎትን ክብር ካላሳየንና አለምን ንቀን ጌታን አንድናገለግል ካላበረታታን የምንመገበው ምግብ ጤነኝነቱ ያጠራጥራል፡፡

ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10

·         የምመገበው ምግብ የሰውን ድካም የሚያጎላ መሆን የለበትም

የምንመገበው ምግብ የራሳችንን ከንቱነት የሚያጎላና የእግዚአብሄርን እርዳታ የማያሳይ ከለሆነ ለመንፈሳዊ ህይወት እድገታችን ከፍተኛ እንቅፋት ነው፡፡ በሚያስችለው በእግዚአብሄር ፀጋ ላይ ሳይሆን በእኛ ድካም ላይ የሚያተኩር ትምህርት አጉል ሃይማኖተኝነት እንጂ እውነተኛ ክርስትና አይደለም፡፡

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5

·         የምንመበው መልካም ትምህርት እንደ እንግዳና መጻተኛ እንድኖር ያደርጋል  

የምመገበው ምግብ በአለም ውድድር ውስጥ ተዘፍቄ የክርስትና አላማዬን እንዳልስት አድርጎኛል ወይ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ የምሰማው ትምህርት እንደ እንግዳና ምፃተኛ ራሴን ከአለም ጉድፍ እንድጠብቅና እግዚአብሄርን በማገልገል አላማና ጌታን በማክበር እንድኖር አድርጎኛል፡፡

ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡11

·         የምንመገበው ትምህርት አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ መሆን የለበትም

የምመገበው ትምህርት የእግዚአብሄርን ሃሳብ በመረዳት በመንፈስ ቅዱስ እንድመራ ነፃነቱን የሚሰጠኝ ነው ወይስ እንደ መጀመሪያ ትምህርት በአትቅመስና አትንካ እስራት ውስጥ የሚጨምረኝ ነው ? የምመገበው ትምህርት በሃይማኖታዊ ስርአቶች ላይ ያተኮረ ብቻ ከሆነና በመንፈስ ቅዱስ በመመራት እግዚአብሄርን እንድናስደስት የማይለቅ ከሆነ የእድገት ጠር የሆነ ትምህርት ነው፡፡

እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ . . .ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና።  ቆላስይስ 2፡20-22

·         የምሰማው ትምህርት ዘላለማዊ ህይወትን የሚያስይዝ መሆን ነው ያለበት
በምናደርገው በማንኛውም ውሳኔ ዘላለም እንደሚኖሩ ሰዎች በክርስቶስ የፍርድ ወንበር እንደምንቀርብ ሰዎች እነዶሆን የማያበረታታ ትምህርት ጤናማ ትምህርት አይደለም፡፡  

መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12

·         የምሰማው ንፁህ ትምህርት ወደ ክርስቶስ የሚያሳይ ነው

የትምህርትን ጤነኝነት አንደኛው መመዘኛ ትምህርቱ ወደ ክርስቶስ ማሳየቱ ወይም አለማሳየቱ ነው፡፡ ለሰው ክብርን የሚያመጣ ክርስቶስን የሚሸፍን ትምህርት ጤናማ ትምህርት አይደለም፡፡ ክብርን ለክርስቶስ የማያመጣ ማንኛውም ትምህርት ለጤናም ሆነ ለእድገት የማይጠቅም ትምህርት ነው፡፡
 
እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ዮሃንስ 16፡14

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ክብር #ጤናማ #አላማ #ሰማይ #ዘላለም #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ