Popular Posts

Thursday, April 4, 2019

ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል


መታዘዛችሁ ለሁሉ ተወርቶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ። የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። ወደ ሮሜ ሰዎች 16፡19-20
ሰይጣን የህይወት ጠላት ነው፡፡ የሰይጣን አላማ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ነው፡፡ ሰመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት ውጭ ሰይጣን ሌላ አላማ የለውም፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 10፡10
ሰይጣን ህይወታችንን ሊውጥ ዙሪያችንን ይዞራል፡፡ ሰይጣን ከአላማችን ሊያሰናክለን ይፈልጋል ይተጋል፡፡
በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡8-9
ስለዚህ እኛ ደግሞ ለበጎ ነገር ጥበበኞች መሆን አለብን፡፡ እንዳመጣልን የምንኖር ሰዎች መሆን የለብንም፡፡ ህይወታችንን እንዴት እንደምንመራ ማወቅ አለብን፡፡ በጎን ነገር ለማድረግ ፈጣን መሆን አለብን፡፡
ክፉን ነገር ላለማድረግ የምንጠነቀቅ ሰዎች መሆን አለብን፡፡ ክፉን በክፉ ፋንታ ላለመመለስ መጠንቀቅ አለብን፡፡ ያለንን ሃይልና  ተሰሚነት ተጠቅመን ክፋትን ላለማድረግ መወሰን አለብን፡፡ ክፉ ሰዎች እነርሱን ተከትለን ክፋትን እንድንሰራ የሚመጣውን ፈተና ክፋትን ባለማድረግ በአሸናፊነት ማለፍ አለብን፡፡ ክፋትን ተከትለን ክፉን በክፉ ላለመመለስ ክፋት በእኛ እንዲያበቃ የክፋትን ሃሳብ በውስጣችን መግደል አለብን፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14፡20
ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች ስንሆን የእኛን ሰላም የሚፈልገው እግዚአብሄር የሰይጣን አላማ በህይወታችን ላይ እንዳይሳካ ያደርጋል፡፡ ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች ስንሆን የሰይጣንን አሰራር ከንቱ ያደርገዋል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሰይጣን #ዲያብሎስን #ሽንገላ #ሃሳብ #አእምሮ #ጥበበኞች #ክፉ #የዋሆች #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment