Popular Posts

Follow by Email

Thursday, April 11, 2019

የማይለወጥ ሰውየሰው ትክክለኛ ህይወት ከመለወጥ ይጀምራል፡፡ ሰው እውነተኛ በረከት ውስጥ የሚገባውምው በመለወጥ ብቻ ነው፡፡ ያልተለወጠ ሰው መኖር ያልጀመረ ሰው ነው፡፡
በተፈጥሮ ስንመለከት ሰው ከተወለደ ጀምሮ ይለወጣል፡፡ ለውጥ የሰው ተፈጥሮ አንድ ክፍል ነው፡፡ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ በህይወት የማይለወጥው ነገር ለውጥ ብቻ ነው፡፡ ለማደግ ለውጥ ግዴታ ነው፡፡  
በመንፈሳዊውም ብንመለከት የሰው እውነተኛ ህይወት ከለውጥ ይጀምራል፡፡
ሰው ለመለወጥ ሲወስን ህይወትን ያገኛል፡፡ ሰው መንገዱን ለመለወጥ ሲወስን ህይወቱ ይታደሳል፡፡ የህይወት መታደስ ብቸኛው መንገድ ለውጥ ነው፡፡
እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። የሐዋርያት ሥራ 3፡19-20
ለውጥ መርገም አይደለም፡፡ አስፈላጊ ለውጥ የህይወት በረከት ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ለውጥን እንዲሁ ይፈሩታል፡፡ ለውጥ ለሰነፎች አይደለም፡፡ ለውጥ ለትጉ ሰዎች ነው፡፡ ለውጥን የሚወዱ ሰዎች ለመትጋት የጨከኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለውጥን የሚወዱ ሰዎች ለመለወጥ ቅናት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለውጥን የሚወዱ እና የሚቀበሉ ሰዎች ለማደግ ልቡ ያላቸው ፣ ሃሞታቸው ያልፈሰሰና ልባቸው ያላረጀ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ለውጥ ስራን ይጠይቃል፡፡ ለውጥ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ለውጥ መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ ለውጥ ራስን መመርመር ይጠይቃል፡፡ ለውጥ ቅድሚያ አሰጣጥን መፈተሽና ማስተካከልን ይጠይቃል፡፡ በዘመኑ መለወጥ ተወስደን ወደኋላ እንዳንቀር መጽሃፍ ቅዱስ ይመክራል፡፡  
ዘመኑ ሲለወጥ የተለወጠውን ዘመን የምንገዛበትና ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅም የምናውልበትን የእግዚአብሄር ጥበብ መፈለግ አለብን፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡15-16
ሁኔታዎች ሲለወጡ ስለሁኔታው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለመፈለግ መትጋት በሁኔታዎች ውስጥ አሸናፊ እንድንሆን ያደርገናል፡፡
ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡15-17
ለውጥ የሚለውጠው ቅድሚያ አሰጣጣችንን ነው፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ቅድሚያ አሰጣጣችን ለነበርንበት ህይወት ተስማሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ አሰጣጣችን አዲስ ለምንገባበት የህይወት ደረጃ ተስማሚ ላይሆንና ማስተካከል የሚያስፈልገው ሊሆን ይችላል፡፡ ቅድሚያ አሰጣጣችን መስተካከልና በአዲሱ የህይወት ደረጃ መቃኘት ሊኖርበት ይችላል፡፡
ለውጥ ቀላለ ነገር አይደለም፡፡ ከለመድነው እና ከተመቻቻንበት ነገር ወጥተን አካሄዳችንን መለወጥ የህይወት ፈተና ነው፡፡ የሁኔታዎች መለወጥ መልስ የሌለው ጥያቄ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን መልስ የሌለው ጥያቄ የለም፡፡ ለማንኛውም ጥያቄ መልስ የምናገኘው በእግዚአብሄር ነው፡፡ ጥያቄ አስፈሪነቱ መልስን እስከምናገኝ ድረስ ብቻ ነው፡፡
ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡13
ለመለወጥ የሚማር ልብ ያስፈልገናል፡፡ ለመለወጥ የማላውቀው ነገር አለ ብለን ማመን ይጠይቃል፡፡ ሁሉንም አውቃለሁ ከዚህ ወዲያ የሚያስተምረኝ ሰው የለም ብለን በትእቢት ካሳብን ለውጥን በደፈናው እንቃወመዋለን፡፡ ለመለወጥ የሚማር የዋህ ልብ ይጠይቃል፡፡ ለመለወጥ አዲስ ነገርን ለመማር የተዘጋጀ ልብን ይጠይቃል፡፡
ህይወት ሁልጊዜ አንድ አይነት እንደሆነ የሚፈልጉ ሰዎች ለውጥ ያስፈራቸዋል፡፡ ህይወት አንድ አይነት እንዲሆን የሚመኙ ሰዎች ለውጥን በፀጋ መቀበል ያቅታቸዋል፡፡ ነገረ ግን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከለውጥ ጋር አብረው መኖር እንደሚችሉ የሚያምኑ ሰዎች ከለውጥ ውስጥ የተሻለ ነገርን ማውጣት ይችላሉ፡፡ የለውጥ በጎ ጎን የሚመለከቱ ሰዎች ለውጥን ለመቀበል ይዘጋጃሉ፡፡ ያለመለወጥንና ያለማደግን አስከፊነት የሚረዱ ሰዎች ለለውጥ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ይወስናሉ፡፡
ለመለወጥ ልበ ሰፊ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ለመለወጥ ከምናውቀው የተለየ ሃሳብን ማስተናገድ ይጠይቃል፡፡ ለመለወጥ አዲስን መንገድን ለመሞከር ዝግጁነትን ይጠይቃል፡፡ ለመለወጥ አዲስ ነገርን በፀጋ መቀበልን ይጠይቃል፡፡
ለመለወጥ ውሳኔን ይጠይቃል፡፡ ለመወሰን የሚፈራ ሰው አይለወጥም፡፡ ለመወሰን አደጋን መጋፈጥ ወይም ሪስክ መውሰድን ይጠይቃል፡፡ ላለመሳሳት ከመጠን በላይ የሚፈራ ሰው ለመወሰን ይፈራል፡፡ የማይወስን ሰው ደግሞ አይለወጥም ብሎም አያድግም፡፡ ብሳሳትም የህይወቴ መጨረሻ አይደለም ብሎ የሚያምን ሰው ውሳኔ ለመወሰን አይፈራም፡፡  
የህይወት ስኬት የቀጣይ ለውጦች ድምር ውጤት ነው፡፡
በህይወታቸን አስፈላጊ ለውጦችን ባደረግን ቁጥር እንለወጣለን፡፡ በተለወጥን ቁጥር እናደርጋለን ፡፡ ባደግን ቁጥር በምድር ላይ የእግዚአብሄርን አላማ ፈፅመን ማለፍ እንችላለን፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ጌታ #ኢየሱስ #ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መለወጥ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment