Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, April 16, 2019

የብዙ ሰዎች ፍቅር የሚቀዘቅዝባቸው ሶስቱ ዋና ዋና ምክኒያቶችከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። የማቴዎስ ወንጌል 24፡12-13
ፍቅር ታላቅ ሃብት ነው፡፡ የፍቅር ህይወት ታላቅ ስብእና ነው፡፡ ፍቅር ክብር ነው፡፡ ፍቅር ውበት ነው፡፡
ኢየሱስን እንደ አዳኛችን የተቀበልን ሁሉ ከእግዚአብሄር በመወለዳችን የእግዚአብሄር ፍቅር በእኛ ውስጥ አለ፡፡ የመውደድ እምቅ ጉልብት ቢኖረንም ይህ በውስጣችን የተጠራቀወመውን ጊልበት አውጥቶ ለብዙዎች በረከት ለማድርግ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡   
በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ወደ ሮሜ ሰዎች 5፡5
ፍቅር መታወቂያችንና ክብራችን ነው፡፡ ፍቅር ሃብታችንና መገለጫችን ነው፡፡ ለፍቅር ተወልደናል፡፡ ሰው ፍቅር ከሌለው የተፈጠረበተን አላማ የሳተ ከንቱ ሰው ነው፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡1
ፍቅር ምንም ያህል የከበረ ቢሆንም ፈተና አለበት፡፡ የፍቅርን ፈተና ያላለፉ ሰዎች ፍቅራቸው ትቀዘቅዛለች፡፡
ፍቅር ቅፅበታዊ አይደለም፡፡ ፍቅር ከትትልና እንክብካቤ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ፍቅር ዝም ብሎ ከተተወ ፍቅርን ሊያቀዘቅዙ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ስላሉ ፍቅር ይቀዘቅዛል፡፡
ፍቅር ግን እንዳይቀዘቅዝ እንዲያውም እየጋለና እየጨመረ እንዲሄድ ለማድረግ እነዚህን ፍቅርን የሚያቀዘቅዙትንና የወይንም ቦታችንን የሚያጠፉትን ጥቃቅን ቀበሮዎች ከህይወታችን መሰለልና ማጥፋት አለብን፡፡  
ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፡15
1.      ስንፍናና አለመትጋት
ፍቅርን ሊያጠፉ የሚመጡ ብዙ ውሆች ስላሉ ፍቅር እንዳይጠፋ ትጋት ይጠይቃል፡፡ ፍቅር ከተተወ ይጠፋል፡፡ ፍቅር እንክብካቤ ካልተደረገለት ይበላሻል፡፡ እንደእሳት ፍቅር ካልቆሰቆሱትና ካላቀጣጠሉት ይከስማል፡፡ ፍቅር እንደችግኝ ማዳበሪያ ካላደረጉለት ውሃ ካላጠጡትና ካልኮተኮቱት ይደርቃል፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ወደ ዕብራውያን 10፡24-25
ፍቅር ሌላውን በመረዳት ራስን ከሚወዱት ሰው ጋር ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር የምንወደውን ሰው ማጥናትና መረዳት ይጠይቃል፡፡ የምንወደውን ሰው ለመረዳት መነጋገር መወያየት ይጠይቃል፡፡
በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ወደ ዕብራውያን 10፡25
ፍቅር ራስን በምንወደው ሰው ቦታ አስቀምጦ ነገሮችን ካለአድልዎ ማየት ይጠይቃል፡፡ የምንወደውን ሰው ለመረዳት ጊዜ መስጠት ይጠይቃል፡፡ የምንወደውን ሰው ለመረዳት ጥረት ይጠይቃል፡፡
2.     መሰናከልና የክፋት መልስ መመለስ
ፍቅር የሚቀዘቅዝበት ምክኒያት ለፍቅራችን መልስን መጠበቅ ነው፡፡ ለፍቅር ድርጊታችን  ከምንወደው ሰው መልስ የምንጠብቅ ከሆንን አንዳንዴ መልካም መልስ ስለማናገኝ ይፍጠንም ይዘግይም ፍቅር መቀዝቀዙ አይቀሬ ነው፡፡ ፍቅር እንካ በእንካ ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍቅር የመስጠት የመባረክ የማንሳትና የመጥቀም ጉዳይ ነው፡፡ ፍቅር እንዲያው ለመስጠት ብሎ የመስጠት ጉዳይ እንጂ መልስን ጠብቆ የመስጠት ጉዳይ አይደለም፡፡
የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? የማቴዎስ ወንጌል 5፡46-47
ፍቅር እግዚአብሄር ለሌላው ሰው እኛ ውስጥ ያስቀመጠውን መልካምነት በታማኝነት የማስጠት ጉዳይ ነው፡፡ ፍቅር ደጋግ መጋቢነት ነው፡፡ ፍቅር ንግድ አይደለም፡፡ ፍቅር ስጦታ መስጠት ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን የተመረቀ እድለኛ ማድረግ ነው፡፡
3.     ራስ ወዳድነትና የእግዚአብሄርን ፍቅር በሚገባ አለመረዳት  
ፍቅር ከራስ ያለፈን ነገር ይጠይቃል፡፡ ፍቅር ሌላው ላይ ማተኮርን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር ሌላውን መድረስ ይጠይቃል፡፡ ፍቅር በራስ ነገር አለመያዝና አለመወሰድን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር በራስ ጉዳይ ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረትን አለማድረግ ይጠይቃል፡፡
ለስጋችን ፊት ከሰጠነው ለራሳችን ህይወት ብቻ ተጨንቀን ማንንም ሳንደርስ እንድንሞት ሊያደርገን ይችላል፡፡ ስጋችንን እህህ ብለን ከሰማነው በራሳችን ጉዳይ ተጠምደን ለማንም ሰው በረከት ሳንሆን እንድናልፍ ያደርገናል፡፡ ለስጋችን ፊት ከሰጠነው በእኛ ውስጥ ለሌሎች የተጠራቀመውን ጉልበት አውጥተን ሳንጠቀም እንድናልፍ ያደርገናል፡፡ የስጋን ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ከሰማነው ለራሳችን ብቻ እያዘንን እና እየተጨነቅን እግዚአብሄር ለሌሎች በእኛ ውስጥ ካስቀመጠው ስጦታ ጋር እናልፋለን፡፡ የስጋን ለአንተስ ማን አለህ የሚለውን የሽንፈት ንግግር ከሰማነው ለራሳችንም ለሌሎችም ሳንጠቅም እንድናለፍ ያደርገናል፡፡
ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 4፡10
እግዚአብሄር እኔን ወዶኛል እኔ ሌሎችን እወዳልሁ ካልን ግን የእግዚአብሄር አላማ ፈፅመን ማለፍ እንችላል፡፡ እግዚአብሄር አስቅድሞ ወዶኛል ስወደው መልሶ የሚወደኝ ሰው አያስፈልገኝም ካልን በፍቅር ሌሎችን ማንሳት ማነፅና መባረክ እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር በወደድን ፍቅር ከረካን ሌሎችን በፍቅራችን ማርካት እንችላለን፡፡  
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መውደድ #መወደድ #ማስተዋል #እግዚአብሔርንመፍራት #ጥበብ #ክፉ #መልካም #ፍርድ #እውቅና #ፍፁም #ችግር #መፍትሄ #አላማ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment