Popular Posts

Wednesday, April 24, 2019

ወደድክም ጠላህም አመለካከትህ ይታያል



ስለሰው ያለህ አመለካከት በተለያየ ምክንያት ሊለወጥና የተበላሸ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሰው ያለህ አመለካከት እንዳይበላሽና ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ስለ ሰው ያለህ አመለካከት በተለያየ ምክንያት ቢበላሽም በፍጥነት ማስተካከል ግዴታ የአመለካከት መበላሸት የሚያስከትለውን ጉዳት ይቀንሳል፡፡
ሰው በሌለበት ጊዜ ስለ አንድ ሰው ስለምታስበው ነገር እጅግ መጠንቀቅ አመለካከትህ እንዳይበላሸ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ስለ አመለካከትህ መጠንቀቅ ያለብህ ስለእርሱ ያለህ አመለካከትህ የተበላሸብህ ሰው አጠገብህ ስላለ ወይም ስለሌለ አይደለም፡፡ ስለ አመለካከትህ መጠንቀቅ ያለብህ ሰው አመለካከትህን ስለሚያየው ወይም ስለማያየውም አይደለም፡፡ ሰው ቢኖርም ባይኖርም አመለካከትህ መልካም ካልሆነና ከተበላሸ የሚያበላሻቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡  
ሰው በሌለበት ጊዜም ቢሆን ስለሌላው ሰው ስለምታስብው ነገር መጠንቀቅ ያለብህ ይፍጠንም ይዘግይም ስለሰው ያለህ አመለካከት ስለሚገለጥ ነው፡፡ ሰው በማይሰማህ ጊዜ ለራስህ ወይም ለሌላው ሰው የምትናገረው ነገር በአንድም በሌላ መልኩ ይሰማል፡፡ ሰው በማይኖርበት ጊዜ የምታሳየው አመለካከት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይንፀባረቃል፡፡
የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። የሉቃስ ወንጌል 8፡17
ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካከት ማስተካከል ያለብህ በግልህ ነው፡፡ ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካከት ማስተካከል ያለብህ ሰውየው በሌለ ጊዜ ነው፡፡ ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካከት ማስተካል ያለብህ ብቻህን ባለህበት ጊዜ ነው፡፡ ስለሌላው ያለህን አመለካት ማቅናት ያለብህ ሰውየው አጠገብህ በሌለበት ጊዜ ስለዚያ ሰው በምታስብበት ወቅት ነው፡፡ ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካት ማቃናት ያለብህ ከራስህ ጋር ስታወራ ነው፡፡
ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል። መጽሐፈ ምሳሌ 20፡5
ሰው ለእርሱ ያለህን አመለካከት ያውቃል፡፡ በተለይ መንፈሳዊ ሰው ሁሉ ይመረምራል፡፡
የተበላሸ አመለካከትህ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የምትችለው ብቸኛ ነገር አመለካከትህን ቀድሞ ማስተካከል እንጂ አመለካከትን መደበቅ አይደለም፡፡ ጠረኑን ያመጣውን ነገር በማጥፋት የአፍን መጥፎ ጠረን ማስተካከል እንጂ ጠረኑ እንዳይታወቅ መመኘት ብቻ መፍትሄ ጠረኑ እንዳይወጣ አያግደውም፡፡  
ሰዎችን እግዚአብሄር እንደሚያያቸው ማየት አመለካትህን ያስተካከልዋል፡፡ ሰዎችን እግዚአብሄር እንደሚያከብራቸው ማክብር አመለካከትህን ቀና ያደርገዋል፡፡ ከሰዎች በላይ ራስን ከፍ አድርጎ በትእቢት ላለመመልከት በአስተሳሰብ ህይወትህ መጠንቀቅ አመለካከትህን ጤናማ ያደርገዋል፡፡  
ሄዋን ለእግዚአብሄር ያላት አመለካከት የተበላሸው ብቻዋን በነፃነት መልካም እንዳልሆነ ስለእግዚአብሄር ማሰብ ስትጀምር ነው፡፡ ሄዋን የቅንነት አመለካከትዋ እንዳይበላሽና ከእግዚአብሄር ጋር ያላትን ግንኙነት እንዳያበበላሽ ማድረግ የምትችለው የቅንነት አስተሳሰብዋን መበላሸት በእንጭጩ ብትቀጭ ነበር፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3
ለሰው ያለህ ቅንነት እንዳይበላሽ አመለካከትህን የሚያበላሽን ነገር ማስተናገድ ይኖርብሃል፡፡ ስለሰው ያለህን ቅንነትን የሚያበላሽን ፍቅር የሌለበትን ነገር በነፃነት እያስብክና ግንኙነቴን አያበላሽም ብለህ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ስለሰው ያለህን አመለካከት የሚያበላሽን አክብሮት የሌለበትን ነገር በነፃነት እያሰብክ አመለካከቴ አይታወቀም ብለህ መመኘት ከንቱ ነው፡፡ ስለሰው ያለህን ቅንነትን የሚያበላሽ እንደእግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ሃሳብን በአስተሳሰብ ህይወትህ እያስተናገድክ ይህ አመለካከቴ ሌላውን አይጎዳም ብለህ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ስለሰው ያለህን አመለካከት ተበላሽቶ ሌላው ሰው በንግግር ወይም በድርጊትህ አይረዳውም ማለት ሞኝነት ነው፡፡
ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡12-13
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አመለካከት #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment