Popular Posts

Wednesday, April 17, 2019

አትወደኝም? ችግር የለም!



ሰው ፍቅር በሆነው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ተፈጥሮአል፡፡ ሰው በፍቅር ተፈጥሮአል፡፡ ሰው ለፍቅር ተፈጥሮአል፡፡ ሰው ለፍቅር እንጂ ለሌላ ነገር አልተፈጠረም፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ያመነ ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው የሚወድበት ሙሉ ብቃት በውስጡ አለው፡፡ ሰው ሰውን የሚወድበት ፍቅር ከእግዚአብሄር ተሰጥቶታል፡፡
በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ወደ ሮሜ ሰዎች 5፡5
የሰው ፍቅር ምንጩ ሰው አይደለም፡፡ ሰው ሰውን ለመውደድ የሰው ፍቅር አያስፈልገውም፡፡ ሰው ሰውን ለመውደድ የሚያስፈልገው የእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ምህረትና ፍቅር የተቀበለ ሰው ሌላውን መውደድ ይችላል፡፡
ከእግዚአብሄር የተቀበልነው ፍቅር አላማው ደግሞ ለሌሎች ፍቅር እንድንሰጥ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን ፍቅር ለሌሎች እንድናከፋፍል በእግዚአብሄር ፍቅር ተወደናል፡፡
አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። የዮሐንስ ወንጌል 15፡9
በእግዚአብሄር ፍቅር የረካ ሰው ሌላውን በፍቅሩ ሌላውን ሰው ማርካት ይችላል፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር የተነሳ ሰው ሌላውን በፍቅሩ ማንሳት ይችላል፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር የተባረከ ሰው ሌላውን በፍቅሩ መባረክ ይችላል፡፡
ሰው ቢወድህ ጥሩ ነው፡፡ ሰው ባይወድህ ይጎዳበታል፡፡ ሰው ቢወድህ ይጠቀማል፡፡ ሰው ባይወድህም የምትኖረው በእግዚአብሄር ፍቅር ስለሆነ እንደ እግዚአብሄር ፍቅር በህይወትህ ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ለሚኖር ሰው የሰው ፍቅር መጣም ቀረም ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡  
የሰው ፍቅር በሚወደው ሰው ፍቅር መልስ ላይ መደገፍ የለበትም፡፡ የማይወድህ ሰው አለ? ችግር የለም ልትወደው ትችላለህ፡፡
ወዳጅ ወይም ባልንጀራ ማለት የሚወድ የሚጠቅም የሚባርክ ሰው ማለት ነው፡፡ ወዳጅነት የሚመሰረተው በእኛ መውደድ ላይ እንጂ ስንወደው መልሶ በሚወደን ሰው ላይ የፍቅር መልስ ላይ አይደለም፡፡
እኔ ለሰዎች መልካም አደርጋለሁ ሰዎች ግን ለመልካምነቴ ምላሽ አይሰጡም ብሎ ላሰበው የህግ አዋቂ ኢየሱስ የመለሰው መልስ ወዳጅነት የሚመሰረተው በአፍቃሪው ላይ እንጂ በተፈቃሪው መልስ ላይ እንዳልሆነ ያስተምረናል፡፡ የሉቃስ ወንጌል 10፡29-37
ኢየሱስ በምሳሌ ያስተማረው ወዳጅነት የሚመሰረተው እኛ ለሌሎች በምናደርገው መልካምነት ላይ እንጂ መልካምነታችንን አይተው በመልካምነት በሚመልሱት በሰዎች መልስ ላይ እንዳይደለ ነው፡፡
እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም፦ ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም፦ ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው። የሉቃስ ወንጌል 10፡36-37
በክርስቶስ ኢየሱስ የተወደድንበት ፍቅር ታላቅ ፍቅር ስለሆነ እኛ በፍቅር እንድንኖር ሌላ ተጨማሪ የሰው ፍቅር አያስፈልገንም፡፡ የእኛን ፍቅር የሚያበረታታ የተፈቃሪ ሰው የፍቅር መልስ የለም፡፡ የእኛን ፍቅር የሚያጨልም የተፈቃሪው ሰው አሉታዊ መልስ የለም፡፡
የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፡17-18
እኛ በፍቅር እንድንኖር በልባችን የፈሰሰው የእግዚአብሄር ፍቅር በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ራሱን የቻለ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር የማንንም ሰው የፍቅር እርዳታ አይፈልግም፡፡
ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን ምህረትና ፍቅር በህይወት ዘመናችን ሁሉ ሰጥተን አንጨርሰውም፡፡
ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። የማቴዎስ ወንጌል 18፡32-33
አትወደኝም? ምንም ችግር የለም፡፡ እኔ እወድሃለሁ፡፡ እኔ አንተን ለመውደድ የአንተ እኔን መውደድ ቅድመ ሁኔታ ወይም ግዴታ አይደለም፡፡ ለእኔ መልካም አታስብም? መልካም አትናገርም? መልካም አትናገርም? ምንም ችግር የለም፡፡ እኔ ግን ለአንተ እንዲሁ በነፃ  መልካም አስባለሁ መልካም እናገራለሁ መልካም አደርጋለሁ፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ፍቅር #ምክንያት #ያለምክንያት #እንዲሁ #ውሳኔ #የዘላለም #ታማኝ #ምንጭ #መውደድ #ስሜት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትዕግስት #መንፈስቅዱስ #ማስተዋል #ልብ #መሪ 

No comments:

Post a Comment