Popular Posts

Sunday, April 14, 2019

በእግዚአብሄር ቢጠሩም እንኳን የማይመረጡ አስር አይነት ሰዎች



የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና። የማቴዎስ ወንጌል 22፡14
እግዚአብሄር ቅን ፈራጅ ነው፡፡ እግዚአብሄር እውነተኛ ዳኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሁሉም ሰው እኩል እድልን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡ እግዚአብሄር ይመርጣል እንጂ ሁሉንም አይወስድም፡፡  እግዚአብሄር የሚመርጥበት የራሱ መመዘኛ አለው እንጂ እግዚአብሄር ይመርጣል፡፡ እግዚአብሄር ቅን ፈራጅ ነው እንጂ እግዚአብሄር አይፈርድም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በቅንነት ይፈርዳል፡፡  
የሰው በረከትና ስኬታማነት በሰው በራሱ መልስ ይደገፋል፡፡ እግዚአብሄር እድሎችን ሁሉ ከፈተ ማለት ሰው ሁሉ በእድሎቹ ይጠቀማል ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር እድሎችን ሁሉ ከፈተ ማለት ሰውን ሁሉ ወደ እድሎቹ ውስጥ እንዲገባ እግዚአብሄር ያስገድዳል ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ከነፃ ፈቃድ ጋር የፈጠረ እግዚአብሄር የሰውን ነፃ ፈቃድ ያከብራል፡፡ እግዚአብሄር ጨዋ አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰው ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ቢፈልግም መዳንና አለመዳን በሰው ምርጫ ላይ ይደገፋል፡፡
ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡3-4
እግዚአብሄር ሰውን ምንም ቢወደውና ለእርሱ ያለው አላማ የፍቅር አላማ ቢሆንም ሰው ይህንን የፍቅር አላማ ለመቀበልም ላለመቀበልም ነፃ ፈቃድ አለው፡፡ 
እግዚአብሄር የጠራቸው ሰዎች ሁሉ የማይመረጡበት ምክኒያት እና እግዚአብሄር ቢጠራቸውም የማይመረጡትን አይነት ሰዎች ከእግዚአብሄር ቃል እንመለከት፡፡
·         ሃላፊነቱን ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሄር የሚያስተላልፉ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
ለህይወታችው ምንም ሃላፊነት የማይወስዱ ሰዎች የተጠሩም ቢሆን እንኳን አይመረጡም፡፡ ሁል ጊዜ ሃላፊነቱን በእግዚአብሄር ላይ የሚያደርጉ ሰዎች የራሳቸውን ሃላፊነትና የህይወት ድርሻ የማይወጡ ሰዎች አይመረጡም፡፡ በህይወታቸው ስለሆነው ነገር ሁሉ የአርባ ቀን እድሌ ነው በማለት ሃላፊነት መውሰድ የማይፈልጉ ሰዎች አይመረጡም፡፡ ስለወደፊት ህይወታቸው ምንም ነገር የማያደርጉ ሰዎች መስራተ የሚችሉትን ነገር ከመስራት ይልቅ እጃቸውን አጣጥፈው አንድ ነገር እንዲደረግላቸው ብቻ የሚጠብቁ ሰዎች አይመረጡም፡፡
ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። የማቴዎስ ወንጌል 11፡12
·         እግዚአብሄር እንደቸገረው የሚመስላቸው ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
ከእግዚአብሄር ጋር የምንጣበቀው ለራሳችን ብለን እንጂ እግዚአብሄር ስለቸገረው ልንረዳው አይደለም፡፡ ሃጢያት የማንሰራው ህይወታችንን ላለማጉደፍና የሌሎችን ህይወት ላለማበላሸት እንጂ ለእግዚአብሄር አምላክነት አንድ ነገርን ለመጨመር አይደለም፡፡
ኃጢአት ብትሠራ ምን ትጐዳዋለህ? መተላለፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ? ጻድቅስ ብትሆን ምን ትሰጠዋለህ? ወይስ ከእጅህ ምንን ይቀበላል? እንደ አንተ ያለውን ሰው ክፋትህ ይጐዳዋል፤ ለሰውም ልጅ ጽድቅህ ይጠቅመዋል። መጽሐፈ ኢዮብ 35፡6-8
·         ነፃ ፈቃድ እንዳላቸው የማያውቁ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
ሰው እንደ ሬዲዮና ቴሌቪዠን ሲከፍቱት የሚከፈት ሲዘጉት የሚዘጋ የራሱ ፈቃድ የሌለው ግኡዝ አይደለም፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረውን ሰው ፈቃድ ያከብራል፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረውን ሰው መልካሙን መንገድ ያሳየዋል እንጂ በመልካሙ መንገድ እንዲሄድ አያስገድደውም፡፡
በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ ኦሪት ዘዳግም 30፡19
·         እግዚአብሄር ኩሩ አምላክ እንደሆነ የማይረዱ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
እግዚአብሄር የሚፈልገው በፍቅር የሚገዙለትን እንጂ በግድ የሚያመልኩትን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በግድ የሙጥኝ የሚል አምላክ  አይደለም፡፡
አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 15፡2
·         ከእግዚአብሄር ጋር አብረው ሰራተኛ እንደሆኑ የማያውቁ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረን አብረነው እንድንሰራ ነው፡፡ እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረን በሙሉ ፈቃደኝነት ደስ ብሎን አብረነው እንድንወጣና እንድንገባ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር አብረው ሰራተኛ እንደሆኑ የማያውቁ በራሳቸው ጉልበት ሁሉን ነገር ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ቢጠሩም አይመረጡም፡፡
የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡9
·         ነፍሳቸውን የማይክዱ ሰነፍ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
እግዚአብሄር ትጉህ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ስንፍና የለበትም፡፡ እግዚአብሄር አብሮ የሚሰራው ከትጉሃና ጋር ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ነገር ዋጋ መክፈል ውድ እንደሆነ እና ብክነት የሚያስቡ ሰዎች አይመረጡም፡፡ ነፍሳቸውን ከእግዚአብሄር በላይ ሊያስደስቱ እንደሚገባቸው የሚያስቡ ሰዎች በእግዚአብሄር የማይመረጡ ሰዎች ናቸው፡፡
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 16፡24-25
·         እግዚአብሄርን በሚገባ የማያምኑ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄርን መንግስት ስራ መስራት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ድርሻ የሰውን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ነው፡፡ እግዚአብሄርን የማያምኑ ሰዎች ስለምን እንበለላን ስለምን እንጠጣለን ብለው እግዚአብሄር በሚያደርግላቸው ነገር እና በእግዚአብሄር ድርሻ ላይ በመጨነቅ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምኑ ሰዎች እግዚአብሄር አገልግሉኝ ሲላቸው ሊጠቅማቸው ሳየሆን አለአግባብ ሊጠቀምባቸው የሚመስላቸው ሰዎች ሁል ጊዜ ከእግዚአብሄር ጋር ስለሚተላለፉ ለእግዚአብሄር ስራ ቢጠሩ እንኳን የማይመረጡ ሰዎች ናቸው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። የማቴዎስ ወንጌል 25፡24-25
·         የሰበብ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም  
መስራት የሚገባቸውን ነገር ለምን መስራት እንደማይችሉ ስንኩል ምክኒያት የሚያቀርቡ ሰዎች ቢጠሩን እንኳን አይመረጡም፡፡ እግዚአብሄርን ላለማገልገል ሁላችንም ምክኒያቶች ይኖሩናል፡፡ እንዲያውም ጌታን ላለመከተል ምክኒያት የለም ብንል እንዋሻለን፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ምክኒያት ጌታን ላለመውድና ለጌታ ዋጋ ላለመክፈል በቂ ምክኒያት አይሆንም፡፡ ነገር ግን ምክኒያቶችን ጥሰው በዘመናቸው የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ይመረጣሉ፡፡
ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው፦ መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። ሌላውም፦ አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። ሌላውም፦ ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው። የሉቃስ ወንጌል 14፡18-20
·         በአለም ውድድር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
ሰው በአለም ውድድር ውስጥ ገብቶ የእግዚአብሄርን ስራም ሊሰራ አይችልም፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች ሌላ ምንም የሚሰሩት በህይወታቸው የተቀመጠ አላማ ስለሌለ እርስ በእርስ በከንቱ ይወዳደራሉ ይፎካከራሉ፡፡ ክርስቶስን ሊከተል የሚወድ ሰው ግን ከአለም ፉክክር ራሱን ማግለል አለበት፡፡ በአለም ፉክክር ውስጥ መወዳር የሚፈልጉ ሰዎች ለጌታ ከመኖር ውድቅ ስለሚሆኑ የማይመረጡ ሰዎች ናቸው፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
·         በሁለት ሃሳብ የሚወላውሉ ራስ ወዳድ ሰዎች በእግዚአብሄር አይመረጡም
እግዚአብሄርንም መውደድ ራስ ወዳድም መሆን አይቻልም፡፡ እግዚአብሄርን የሚወድ ሰው ከራሱ ጥቅምና ፍላጎት በፊት የእግዚአብሄርን ነገር ማስቀደም አለበት፡፡
ሌላውንም፦ ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስም፦ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው። ደግሞ ሌላው፦ ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስ ግን፦ ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው። የሉቃስ ወንጌል 9፡59-62
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የተጠሩ #ብዙዎች #የተመረጡ #ጥቂቶች #ልጅነት #ደህንነት #መልካምስራ #መልካምምግባር #ሞት #አላማመሳት #ሐጢያት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ፍጥረት #ልጅነት #ስራ #እምነት #አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment