Popular Posts

Thursday, May 25, 2023

ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም

 


ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5:16

ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:2

ከሰው ጋር ማንኛውንም ግንኙነት ለማድረግ ሰውን ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ ሰው ማነው? የሚለውን ጥያቄ በሚገባ የመመለስ ሸክም አለብን፡፡ ሰውን በሚገባ ካላወቅነው እንደሚገባ አብረን ልንኖር አንችልም፡፡

ሰውን ለማወቅ ባለን ጥረት ሰውን በተለያየ መመዘኛ ለማወቅ እንጥራለን፡፡ ስለሰው ስናስብ በተፈጥሮ እነዚህ የሰው መመዘኛዎች ወደ አእምሮዋችን ይመጣሉ፡፡

ማነው  ? ምን ይሰራል  ? የት ይኖራል ? ገቢው ምንድነው  ? በማህበረሰብ ውስጥ ያለው ተቀባይነት ምን ያህል ነው ? ተምሮዋል ወይስ አልተማረም ? ሃያል ነው ደካማ ? ባለጠጋ ነው ደሃ ? የኑሮ ደረጃም ዝቅተኛ ከፍተኛ መካከለኛ ነው ? የአገሬ ሰው ነው አይደለም ? ላምነው እችላለው ? ልደገፍበት እችላለሁ ?

እነዚህን እና የመሳሉትን ጥያቄዎች የመመለስ ሸክም በእኛ ላይ ወድቆብናል፡፡

ችግሩ ደግሞ እነዚህን ጥያቄዎች በትክክል መመለሳችን ሰውም በሚገባ እንድንመዝነው በቂ አይደሉም፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች ሰውን መዝነን  ከጨረስን በኋላ ልንሳሳት መቻላችን የሰውን አመዛዘን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ እነዚህ መመዘኛውዎች በእግዚአብሄር መልክ እና አምሳል የተፈጠረውን ሰው ለመመዘን ብቁዎች አይደሉም፡፡

ሰዎች ሰውን በተለምዶ የሚመዝኑባቸው መመዘኛዎች ሰውን በብቃት ለመመዘን ብቁ እንዳልሆኑ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡

እነዚህ መመዘኛቸው የራሳቸው ጉድለት ስላለባቸው ሰው ራሱንም ሆነ ሌላውን ሰው በእነዚህ መመዘኛዎች በመመዘን ሊሳሳት ይችላል፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24

ጠቢብነት ሃያልነት እና ብልጥግና የሰውን የወደፊት ስኬት እንደማይወስኑ  መፅሃፍ ቅዱስ ግልፅ አድርጎታል፡፡ ሰው ጠቢብ መሆኑ እና አለመሆኑ የሚያስመካም የሚያዋርድም ነገር አይደለም፡፡ ሰው ሃያል መሆኑ እና ደካማ መሆኑ ከቁጥር የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ሰው ባለጠጋ መሆኑ እና አለመሆኑ የህይወት ስኬት ቁልፍ መያዙን  ወይም አለመያዙን አያሳይም፡፡

ምክኒያቱም እነዚህ የምድር መመዘኛዎች የሰውን ስኬት እና ውድቀት ሊመሰክሩ የሚችሉ ብቁ ምስክሮች ስላይደሉ ነው፡፡

የሰውን ትክክለኛ ዋጋ ሊያሳየን የሚችለው እግዚአብሄ ብቻ ነው፡፡ የሰውን ትክክለኛ ደረጃ ልናይ የምንችለው ሰውን በእግዚአብሄር ስናየው ብቻ ነው፡፡ ሰውን በትክክል የምናየው በእግዚአብሄር ፍጥረትነቱ ስናየው ብቻ ነው፡፡ ሰውን ከእግዚአብሄር ፍጥረትነቱ ባነሰ መመዘኛ መዝነነው ልናውቀው በፍፁም እንችልም፡፡ ሰውን በእግዚአብሄር መመዘኛ በተለየ መልኩ በስጋ መዝነነው እንሳሳታለን እንጂ ትክክል ልንሆን እንችልም፡፡

የሰውን ትክክለኛ ደረጃ ማወቅ የምንችለው እግዚአብሄር እንደሚያይ ስናየው ብቻ ነው፡፡

እኛም እንደሰባኪው ወደእውነቱ መመለስ አለብን፡፡

እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መጽሐፈ መክብብ 9፡11

ሰውን በሰውኛ መመዘኛ መመዘን የሰውን ዋጋ ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡

ሰውን በትክክል ልንመዝን የምንችለው በክርስቶስ ስንመዝነው ብቻ ነው፡፡ ሰውን በክርስቶስ ማየት ካልቻልን ትክክለኛ ደረጃውን ማወቅ ይሳነናል፡፡ ሰው ከክርስቶስ ውጭ በስጋ መዝነን በትክክለኛ ማንነቱ ልናውቀው እና እንደሚገባ ልንይዘው እንችልም፡፡

ስለዚህ እኛም ተመልሰን ሰውን በስጋ ላለማወቅ እስካልወሰንን ድረስ የሰውን እውነተኛ ዋጋ መረዳት ያቅተናል፡፡ ተመልሰን ሰውን በክርስቶስ ለማየት ካልወሰንን በስተቀር ሰውን መረዳት በፍፁም አንችልም፡፡

ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


No comments:

Post a Comment