Popular Posts

Wednesday, May 17, 2023

ወንጌልን ስበክ ካስፈለገ ቃልን ተጠቀም

 


ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለልንን የሃጢያት ዋጋ ለእኛ ነው ብለን የተቀበልን ሁላችን ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር ከመለያየት ድነናል፡፡ ታዲያ በክርስቶስ የዳንን ሁላችን በአለም ላይ ያለነው ለስራ ነው፡፡ በምድር ያለነው ለሌሎች ስለክርስቶስ እንድንመሰክር ነው፡፡ በምድር የቆየነው ለሌሎች የእግዚአብሄርን መንገድ እንድናሳይ ነው ለሌሎች ብርሃንን ልናበራ ነው፡፡ እንደዳንን ወደጌታ ያልተሰበሰብነው ለሌሎች እውነተኛውን የህይወት ደረጃ እንድናሳይ ነው፡፡

እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡9

ይህንን ምስክርነት የምንሰጠው በኑሮዋችን ነው፡፡ ኑሮዋችንን ስለምምናገረው ነገር እውነተኝነት ኑሮዋችን ካልመሰከረ ሰዎች አይቀበሉም፡፡ ሰዎች ከምንናገረው ቃል በላይ የሚያምኑት አካሄዳችንን ነው፡፡ የምንናገረው ነገር የምንኖረውን ነገር ለመግለፅ እንጂ ንግግር ብቻ በራሱ በቂ ምስክርነት አይደለም፡፡

የጌታ ኢየሱስ ተከታዮች ስንሆን የመጀመሪያው ሙያችን ከእግዚአብሄር ጋር ታረቁ ብለህን በቃልም ይሁን በህይወት መመስከር ነው፡፡

ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡6-8

በድሮ ዘመን በገንዘብ ስለተገዙት ባሪያዎች እንኳን ሃዋሪያው ጳውሎስ ሲናገር በስራችሁ ቦታ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው ይላቸዋል፡፡ ስለዚህ ለምድር ጌቶቻችሁ ለታይታ ሳይሆን በሙሉ ልብ ታዘዙ እና ተገዙ ይላቸዋል፡፡ ምንም ባሪያዎች ቢሆኑ እንደክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች የመጀመሪያው ሃላፊነታቸው የእግዚአብሄርን መልካምነት እና እውነተኝነት በህይወታቸው እና በስራቸው ማንፀባረቅ ነው፡፡

ሰዎች ከስብከት ቃላችን ይልቅ የሚያምኑት ህይወታችንን ነው፡፡ ወጥተን እንኳን ስንሰብክ ሰዎች የሚቀበሉን የምንናገረውን ነገር እና የምንኖረውን ኑሮ አንድነት እና ልዩነት በሚገባ አስተያይተው ብቻ ነው፡፡ የምንናገረው የቃል ስብከት እንደ ክርስትያን ከምንኖረው ኑሮ ጋር አብሮ ካልሄደ አይቀበሉትም፡፡ ሰዎች እውነተኛውን ከሃሰተኛው የሚለዩት በህይወት ልዩነት ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ከሃጢያት ሊያድናችሁ መጣ ብለን እየሰበክን እኛ ከሃጢያት የዳነ ህይወት ካላሳየን ሰዎች በርካሽ ንግግር የምናታልላቸው ስለሚመስላቸው አይቀበሉንም፡፡ ሰዎች የስብከት ቃላችንን የሚቀበሉበት መሰረቱ የምኖረው ህይወት ምስክርነት ነው፡፡

እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። የማቴዎስ ወንጌል 5፡.13-16

የአለም ብርሃን መሆናችን የህይወት ዘይቤያችን መልካምነታችን እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ በጨለማው በስግብግብ አለው ውስጥ  በመልካም ስራችን  በብርሃን መገለጣችን የእግዚአብሄር መልካምነትን ያንፀባርቃል፡፡

በዚህ ራስ ወዳድ በሆነ በጨለማ አለም መካከል ስንኖር በፍቅር እና በመልካም ስራ መገለጣችን እግዚአብሄርን ፍቅር እና መልካምነት ያሳያል፡፡ በዚህን በንፉግ የጨለማ አለም ውስጥ የእግዚአብሄርን መልካምነት የምናሳየው በመልካምነት ብርሃን ስንገለጥ ብቻ ነው፡፡

በዚህ በደካማ አለም መካከል ስንኖር እኛ ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን የሚያስችል ሃይል ወይም ፀጋ የምናሳየው ሰዎች በተለምዶ የማይጠብቁትን መልካምነት ስናደርግ ብቻ ነው፡፡

እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። የማቴዎስ ወንጌል 5፡40-41

በዚህ አለም ሰዎች የሚጋደሉበትን ነገር እኛ ግን ስንንቀው ስለእግዚአብሄር መልካምነት እንመሰክራለን፡፡ በዚህ በጨለማው አለም ሰዎች የሚያጉረመርሙበትን እኛ ግን ካለማጉረምረም ስናደርገው ከእኛ ጋር ስላለው ስለእግዚአብሄር ፀጋ እንመሰክራለን፡፡

በምድር የተለመደው ጥላቻ ነው፡፡ በጥላቻ በተሞላ አለም ውስጥ እርስ በእርሳችን ስንዋደድ ሰዎች ሁሉ ካለ ትምህርት የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እንደሆንን ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ፡፡

እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 17፡22-23

እጅግ በተከፋፈለ አለም ካለ ቃል ስብከት በአንድነታችን ብቻ ክርስቶስ እንደተወደደበት መውደድ መጠን ክርስቶስ እንደወደደን አለም ያውቃል፡፡

እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። የዮሐንስ ወንጌል 13፡35

በተቃራኒው ለቅዱሳን እንደሚገባ ካልኖርን ግን በእኛ ምክኒያት በመልካም ስራችን በመመስገን ፋንታ የጌታ ስም ይሰደባል፡፡

እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ። ወደ ሮሜ ሰዎች 2፡23-24

ህይወታችን ብቻ ታላቅ የስብከት እና የማሳመን ሃይል አለው፡፡

እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡1-2

ሃዋርያው ጴጥሮስ ለሚስቶች "በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ" መንፈሳዊ ስብከት ወይም ትምህርት ሳያስፈልጋቸው በሚስቶች ኑሮ ተማርከው እነርሱን ሊመስሉ እንደሚችሉ በህይወት ዘይቤ ውስጥ ስላለው ታላቅ ሃይል ያስተምራል፡፡

ሙሉ የህይወት ክፍላችንን ስለሚጠይቅ በቃል ከመስበክ በላይ በኑሮ መስበክ ይከብዳል፡፡ በአስተሳሰባችን በአነጋገራችን በአደራረጋችን ሁሉ ቀኑን ሙሉ ሁልቀን ክርስቶስን በህይወት እንሰብከዋለን፡፡ ህይወታችን ሰዎች ክርስቶስን እንዲወዱት እና ሊከተሉት እንዲወስኑ ያደርጋል ወይም ህይወታችን ውበቱ እንዳይታይ ይሸፍናል፡፡ እንደክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች የምናደርገው ማንኛውም ሃሳብ ንግግር እና ድርጊት የክርስቶስን ስም ይሸከማል፡፡

ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤የሐዋርያት ሥራ 9፡15

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


No comments:

Post a Comment