Popular Posts

Wednesday, May 24, 2023

የትዳር የምድር ተልእኮ


እግዚአብሄር በትዳር ውስጥ ያለውን ልዩ አላማ ከእግዚአብሄር ቃል መረዳት እና ትዳር በመጀመሪያ በራሱ በእግዚአብሄር የተቋቋመበትን አላማ ማሳካት ወደር የከሌለው የህይወት ሃላፊነት ነው፡፡ 
ትዳር የእግዚአብሄር ዲዛይን ወይም ንድፍ ነው፡፡ ትዳር የሰው እጅ ስራ አይደለም፡፡ ትዳር ሰው ችግር ሲገጥመው ችግሩን ለመፍታት የቆረቆረው ተቋም አይደለም፡፡ ትዳር ከሰው መፈጠር ጋር ተያይዞ የታቀደ የእግዚአብሄር የጥንት /ኦሪጅናል/ እቅድ ነው፡፡ 
እግዚአብሄር በትዳር ያምናል፡፡ እግዚአብሄር ሁለት የተለያዩ ሰዎች ሁለት አስተዳደግ ሁለት ባህል ሁለት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ወንድና ሴት በፍቅር ተጣምረው በትዳር የእግዚአብሄርን ፍቅር ለአለም ሊያንፀባርቁ እንደሚችሉ እግዚአብሄር ያምናል፡፡ እግዚአብሄር ትዳር እንደሚሰራ ያምናል፡፡ እግዚአብሄር ትዳር የሚሰራበትን መንገድ እና አቅርቦት ሁሉ አዘጋጅቶ ትዳርን ለሰዎች ሰጠ፡፡ እግዚአብሄር ትዳርን ሰጠ፡፡ ትዳር የእግዚአብሄር መልካም ስጦታ ነው፡፡ 
ትዳር እንዲሰራ እና እንዲሰምር ብሎም የተፈጠረበትን አላማ እንዲያሳካ እግዚአብሄር ፀጋ እና ፍቅርን  ለሰው ልጆች ሰጠ፡፡ 
ትዳር የራሱ የእግዚአብሄር ሃሳብ በመሆኑ ሁልጊዜ በራሱ በእግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ ይደገፋል፡፡ ሰው ራሱን ለእግዚአብሄር ሃሳብ ትሁት ያድርግ እንጂ እግዚአብሄር ትዳርን በሙሉ ሃይሉ ይደግፈዋል፡፡ ሰው በራስ ወዳድነት የእግዚአብሄርን ሃሳብ አይጣል እንጂ እግዚአብሄር የራሱን ተቋም ትዳርን ባለው ነገር ሁሉ ይደግፋል፡፡ 
የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው። ኦሪት ዘፍጥረት 5፡1-2
የትዳር አላማ በባልና በሚስት የጥንካሬ እና የልስላሴ ባህሪ የእግዚአብሄር ሙሉ መልክ ማሳየት እና ማንፀባረቅ ነው፡፡ 
እግዚአብሄር ወንድና ሴትን በመልክ ፈጠረ፡፡ የእግዚአብሄርን ሙሉ መልክ የሚያንፀባርቁት ወንድ እና ሴት ናቸው፡፡ 
ወንድ የእግዚአብሄርን ጥንካሬ ዲሲፒሊን መሪነት ባህሪ ሲያንፀባርቅ ሴት ደግሞ የእግዚአብሄርን ርህራሄ ፍቅር ይቅር ባይነት እንክብካቤ ባህሪ ታሳያለች፡፡ በወንድ እና በሴት ሙሉው የእግዚአብሄር መልክ በትዳር ውስጥ ይታያል፡፡ 
እግዚአብሄርን ሙሉ ለሙሉ የሚያንጸባርቀው የባል እና የሚስት ትዳር ነው፡፡
የወንድ እን የሴት ትዳር የክርስቶስ እና የቤተክርስትያን ግንኙነት እና አንድነት ነፀብራቅ ነው፡፡ 
ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡29-33
እግዚአብሄር የተልእኮ አምላክ ነው፡፡ ትዳር የእግዚአብሄር ተልእኮ አለው፡፡ 
ትዳር በዝምታ ስለ እግዚአብሄር መኖር ይናገራል፡፡ 
ትዳር በዝምታ ስለእግዚአብሄር ፍቅር ይናገራል፡፡ 
ትዳር በዝምታ ስለእግዚአብሄር ትእግስት ይናገራል፡፡ 
ትዳር በዝምታ ስለክርስቶስ እና ስለቤተክርስትያን አንድነት ይናገራል፡፡ 
ሰይጣን ስለእግዚአብሄር የሚናገር እግዚአብሄርን የሚያስታውስ ነገርን ሁሉ ይቃወማል፡፡ ሰይጣን በትዳር ውስጥ ያለውን የእግዚአብሄርን ሙሉ መልክ ለማጥፋት የሚጥረው ለዚህ ነው፡፡ 
ሰይጣን ይህን መልክ በላጲስ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወጥቶዋል፡፡ ግን በክርስቶስ የመስቀል ስራ ስለተሸነፈ በትዳር ያለውን የእግዚአብሄርን የወንድ እና የሴት መልክ በማጥፋት አይሳካለትም፡፡ 
ስለእግዚአብሄር መኖር በሚጠራጠር እና በሚክድ ትውልድ መካከል ስለእግዚአብሄር መኖር ስለፍቅሩ የምናሳየው ትዳራችንን እንደእግዚአብሄር ተልእኮ በሚገባ ስንይዘው ነው፡፡ 
ስለ እውነተኛ ቤተክርስትያን መኖር በሚጠራጠረው ትውልድ መካከል የክርስቶስ እና የቤተክርስትያንንን ግንኙነት እና አንድነት የማንፀባረቅ የእግዚአብሄር መንግስት ተልእኮዋችንን የምንወጣው እግዚአብሄር በሰጠን ትዳር ተጠቅመን ነው፡፡ 
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

No comments:

Post a Comment