Popular Posts

Thursday, May 11, 2023

እምነት የሚሰራበት መንገድ

 


እምነት በእግዚአብሄር የተሰጠን በምድር እያለን ከመንፈሳዊው አለም ጋር ተገናኝነት በመንፈሳዊው አለም  ጉዳያችንን እንድናስፈፅምበት ነው፡፡

ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ማድረግ አንችልም፡፡ ካለእመነት በመንፈሳዊው አለም ያለንን የልጅነት ስልጣን በመጠቀም ነገሮችን መለወጥ አንችልም፡፡ እምነት የሚሰራበትን መንገድ መማር ያለብን ለዚህ ነው፡፡

እምነት በስሜት ወይም በምኞት አይመጣም፡፡ የሚሰራው እምነት የሚገኝበት የራሱ መንገድ አለው፡፡ እምነት የሚመጣው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡

እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17

የእምነት እርምጃ የመጀመሪያው ሃላፊነት ስላለንበት ሁኔታ የእግዚአብሄርን ቃል መፈለግ ነው፡፡ ስላለሁበት ሁኔታ እግዚአብሄር ምን ይላል? የሚለውን መመለስ የእምነት ቁልፍ እርምጃ ነው፡፡ በእምነት ስለምፈልገው ነገር የእግዚአብሄር ቃል ምን ይላል የሚለውን ጥያቄ በትክክል መመለስ ሊታለፍ የማይገባው የእምነት ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ቃል የእግዚአብሄርን ሃሳብ ካገኘን በኋላ በእምነት የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማድረግ ዝግጁ ነን ማለት ነው፡፡

በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፡14-15

የእግዚአብሄርን ልብ ከተረዳን በኋላ የምንፈልገውን በእግዚአብሄር ፊት ማድረግ አለብን፡፡ በእምነት ማድረግ ብቻ አይደለም ነገር ግን በእምነት ማሰብ ፣ በእምነት መናገር እና በእምነት መራመድ ይኖርብናል፡፡

አስተሳሰባችን ከእምነት እርምጃችን ጋር አብሮ መሄድ ይኖርበታል፡፡ በእምነት ፀልየን በልባችን መጠራጠር የለብንም፡፡ በእምነት ፀልየን የጥርጥር ንግግር መናገር የለብንም ነገር ግን ንግግራችን ከቃሉ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል፡፡ በእምነት ፀልየን የፍርሃት ኑሮ መኖር የለብንም፡፡ ነገር ግን በድፍረት መመላለስ አለብን፡፡

እምነት ስለማናየውን ነገር የሚያረጋገጥ በመሆኑ ያመንነው ነገር እስኪሆን ድረስ እንደተደረገልን ሆነን በፅናት እና በምስጋና መጠበቅ ይኖርብናል፡፡  

እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። የማርቆስ ወንጌል 11፡23-24

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 


No comments:

Post a Comment