Popular Posts

Monday, September 16, 2019

19ኙ የጥበብ ጉድለት አደጋዎች


የህይወት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ አላቸው፡፡ መልስ የሌለው ጥያቄ መፍትሄ የሌለው ችግር መውጫ የሌለው ፈተና የለም፡፡ የሚያስፈልገን ጥበብ ነው፡፡ ጥበበ ከጎደለን ግን በህይወታችን ለእነዚህ አደጋዎች እንጋለጣለን፡፡
ጥበብ በጎደለን መጠን የህይወት አደጋችን እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። የያዕቆብ መልእክት 1፡5
1.      የጥበብ ጉድለት ያለንን ነገር ሁሉ ለማይረባና ለማያጠግብ እንጀራ እንድናውለው ያደርገናል፡፡ ጥበብ ሲጎድለን የዋጋ አሰጣጣችን ይዛባል፡፡ ጥበብ ሲጎድለን የከበረውን ከተዋረደው መለየት ያቅተናል፡፡ ጥበብ ሲጎድለን ዋጋ ለሌለው ዋጋ እንሰጣለን ለከበረው የሚገባውን ክብር እንሰጥም፡፡
ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ትንቢተ ኢሳይያስ 55፡2
2.     የጥበብ መጉደል ከእኛ የተለዩ ሰዎችን ባለመቀበልና በመግፋት የአካላችንን አንዱን እንድንጥል ያደርገናል፡፡
እግዚአብሄር ወደ አየልን የህይወት አላማ እንድንደርስ የሚረዱን ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ የህይወታችን መፍትሄ ሁሉ እኛ ውስጥ የለም፡፡ እግዚአብሄር ለህይወታችን የሚያስፈልገውን እኛ ውስጥ ግን የሌለውን ነገር ሁሉ ያስቀመጠው በሌሎች ውስጥ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሌሎች ውስጥ ለእኛ ያስቀመጠውን በረከት መጠቀንም የምንችለው ከእኛ የተለዩትን ሰዎች ለመለወጥ ባለመሞከር ነው፡፡ እግዚአብሄር በሌሎች ውስጥ ለእኛ ያስቀመጠውን በረከት መጠቀንም የምንችለው ሌሎችን በጥበብ መያዝ ስንችል ብቻ ነው፡፡ 
አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡17-18
3.     ጥበብ መጉደል ሁሉንም ሰው በአንድ አይን እንድንመለከትና የሰውን ልዩነት ተረድተን እንደ እያንዳንዳንዱ ሰው ጥንካሬ እና ድካም እንዳንይዘው እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ከሁሉም ሰው ተመሳሳይ ነገር ከጠበቅን እንሳሳታለን፡፡ ሁሉንም ሰው ተመሳሳይ ለማድረግ ከሞከርን እኛ ውስጥ የሌለውን የሰዎችን ልዩ ስጦታ እንገድላለን፡፡ 
እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡7
4.     የጥበብ ጉድለት ለፈጠረን ለእግዚአብሄር የሚገባውን የክብር ስፍራ እንዳንሰጥ ያደርገናል፡፡ የጥበብ መጉደል ከፈጠረን ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት እንድምንኖር እንዳናውቅ ያደርገናል፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 1፡7
5.     ጥበብ ሲጎድለን ለህጉ ዋና ነገር የሚገባውን ትኩረት እንዳንሰጥ ያደርገናል፡፡ ጥበብ ሲጎድለን ህይወት የሚሰጠውን የህጉን መንፈስ ትተን የህጉን ፊደል እንድንከተል ያደርገናል፡፡
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። የማቴዎስ ወንጌል 23፡23
6.     የጥበብ መጉደል ለገንዘብና ለቁሳቁስ የማይገባውን ክብር እንድንሰጥ ያደርገናል፡፡ የጥበብ መጉደል ለገንዘብ ካለአቅሙ ከፍተኛ ግምት እንድንሰጥና ለገንዘብ እንድንጎመጅ ያደርገናል፡፡
የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። የሉቃስ ወንጌል 12፡15
7.     የጥበብ መጉደል የህይወት ቁልፍ ያለው ሃያል ባለጠጋ እና ጥበበኛ ጋር እንደሆነ በማሳመን ያሳስተናል፡፡ የጥበብ መጉደል ትኩረታችንን ከእግዚአብሄር ላይ እንድናነሳ እና ሃይል ባለጠግናትና ጥበብ ላይ እንድናደርግ ያደርጋል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24
8.     የጥበብ መጉደል መናገር በሌለብን ጊዜ እንድንናገር ዝም ማለት ባለብን ጊዜ እንድንናገር ያደርገናል፡፡ ጠቢብ መቼ እንደሚናገር መቼ ዝም እንደሚል ማስተዋል ይመራዋል፡፡
ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል። ትንቢተ አሞጽ 5፡13
9.     የጥበብ መጉደል ነገራችንን በልክ እንዳናደርግ ይፈታነናል፡፡ ከራሳችን አልፈን ለሌላው የምንተርፈው ነገራችንን በልክ ስናደርግ ያለኝ ይበቃኛል ስንል ብቻ ነው ፡፡ 
አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም። 2 ወደ ጢሞቴዎስ 4፡5
10.    የጥበብ መጉደል በቅንጦትና በመሰረታዊ ፍላጎት መካከል እንዳንለይ ያደርገናል፡፡ እግዚአብሄር እረኛችን ነው የሚያሳጣን የሚያስፈልገን ነገር የለም፡፡ ሰው በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን መለየት ካልቻለ ህይወቱ አያርፍም፡፡ ሰው በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ካልቻለ ሞልቶ የማይሞላውን ቅንጦት በማሟላት ሩጫ ህይወቱን ያባክናል፡፡ ሰው በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ካልቻለ በጭንቀት ታስሮ እግዚአብሄር ያስቀመጠለትን የህይወት አላማ ከግብ ማድረስ አይችልም፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ . . . አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6-9
11.     ጥበብ ማጣት እውነተኛውን የህይወት ምንጭ ትተን ውሃ የማይዝ ጉድጉዋድ እንድንቆፍር ያደረገናል፡፡ ጥበብ እውነተኛውን የህይወት ምንጭ እግዚአብሄርን እንድንፈልግ ያስተምረናል፡፡
ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም ጕድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጕድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል። ትንቢተ ኤርምያስ 2፡13
12.    የጥበብ ጉድለት እኛን ለማይመስሉ እና ከእኛ ለተለዩ ሰዎች ልባችን እንዲጠብ ያደርገናል፡፡ የጥበብ ጉድለት እኛን የማይመስሉንን ሰዎች በጥበብ ከመያዝ ይልቅ ጨፍልቀን እኛን እንዲመስሉ በምናደርገው ሙከራ እንድንጥላቸው ያደርገናል፡፡ የጥበብ ጉድለት ከእኛ ለየት ያሉት ሰዎች ውስጥ እግዚአብሄር ያስቀመጠልንን በረከት በመጣል በእጦት እና በሽንፈት እንድንኖር ያደርገናል፡፡
እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 4፡29
13.    የጥበብ መጉደል ያለንን ውስን ጉልበት ባላስፈላጊ ነገር ላይ እንድናባክን ያደርጋል፡፡ የጥበብ ጉድለት ቅድሚያ መስጠት ላለብን ነገር ቅድሚያ እንዳንሰጥ ስለሚያደርገን ብዙ ዘርተን ትንሽ እንድንሰበስብ ያደርጋል፡፡ በተቃራኒው ጥበብን ማግኘት  ማስተዋል ባለበት በትንሽ ስራ ብዙ ውጤት እንድናገኝ ይረዳናል፡፡
የሰነፍ ሥራ ያደክመዋል ወደ ከተማ መሄድ አያውቅምና። መጽሐፈ መክብብ 10፡15
14.    የጥበብ መጉደል ሰው ዝም ብሎ መስራትና መጣር ብቻ እንጂ በውጤቱና በግኝቱ እንዳይሰደሰት ማስተዋል ይነሳዋል፡፡ ጥበብ መጉደል ህይወታችንን እንደልጅ በሚገባ እንዳንደሰትበት ያደርገናል፡፡ ህይወት ሃላፊነትና ሸክም ብቻ ሳይሆን እንድንደሰትበት የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ ጥበብ ያስተምረናል፡፡ ጥበብ በሰራነው ነገር ፣ ባገኘነው ነገርና በደረስንበት ደረጃ እንድንደሰት ያስተምረናል፡፡ 
እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና። እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። መጽሐፈ መክብብ 5፡18-19
15.    የጥበብ መጉደል ባላስፈላጊ ፉክክርና ውድድር ውስጥ ህይወታችንን እንድናባክን ያደርጋል፡፡
ጠቢብ ሰው ስኬቱን የሚለካው እግዚአብሄር በሰጠው የስራ ሃላፊነት ብቻ ነው፡፡ ጠቢብ ሰው ጎረቤቱ በሆነ ነገር በምንም ነገር ከጎረቤቱ ማነሱም ሆነ መብለጡ ስለስኬቱ ወይም ስለውድቀቱ አይነግረውም፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
16.   የጥበብ መጉደል ትክክለኛውን ጊዜ እንዳንለይ ያደርገናል፡፡ በትክክለኛው ጊዜ ውስጥ የሚለቀቅ ልዩ ሃይልና ስኬት አለ፡፡ ልክ ከጊዜው በፊት ልክ እንደጊዜው ነገሮች ውብ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መጽሐፈ መክብብ 3፡1
17.    ጥበብ ከጎደለን ውብና ድንቅ ተደርገን ለልዩ አላማ እንደተፈጠረን ስለማንረዳ ሌላውን ለመምሰል በመጣጣር አንዷን ልዩ ህይወታችንን በከንቱ እናባክናታለን፡፡
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙረ ዳዊት 139፡14
18.    የጥበብ ጉድለት የእግዚአብሄርን እርምጃ እና ፍጥነት እንዳንታገሰው ያደርጋል፡፡ እግዚአብሄር አይቸኩልም፡፡ የእግዚአብሄርን እርምጃ ፍጥነት ከታገስን ፀፀትን በማትጨምረው እውነተኛ በረከት ውስጥ እንገባለን፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። መጽሐፈ ምሳሌ 28፡20
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። መጽሐፈ ምሳሌ 13፡11
19.   የጥበብ ጉድለት ከፍቅር ውጭ በመኖር ህይወታችን ዋጋ እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡2-3
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ጥበብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማስተዋል #እምነት #ፈተና #ፀሎት #ጌታ #የእግዚአብሄርቃል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment