Popular Posts

Wednesday, September 18, 2019

ህይወታችን እንዳልተለወጠ ሲሰማን ማድረግ ያለብን 5 ነገሮች



ሁላችንን በየጊዜው ህይወታችን እንደቆመ እንደሚገባው እንዳልተራመድን እያደግን እየተለወጥን እንዳይደለ ይሰማናል፡፡ የእስራኤል ህዝብ በእግዚአብሄር ላይ እልከኛ በመሆንና ባለመታዘዝ አርባ አመት ሙሉ አንድን ተራራ ሲዞሩ ኖረዋል፡፡ እኛም በተለያየ ጊዜ እንደ እስራኤላዊያን የሴይርን ተራራ እንደምንዞር ፣ ህይወታችን ለውጥ አልባ እንደሆነና ህይወታችን እርምጃ እንደሌለው ሲሰማን ማድረግ ያለብን 5 ነገሮች
1.      በጌታ ፊት ጊዜ መውሰድ
እርምጃችን በእውነት መቆሙን ለማረጋገጥ በጌታ ፊት ጊዜ መውሰድ ይጠይቃል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ መሰማቱ ብቻ እርምጃችን በእውነትም መቆምሙን ሊያረጋጋጥ አይችልም፡፡ እርምጃችን እንደቆመ መሰማቱ መቆማችንን ሊያሳይ ወይም ደግሞ ላያሳይ ይችላል፡፡ ስለዚህ በህይወታችን እርምጃ ማጣት ሲሰማን እውነት እድገቴ ቆሟል ወይስ አልቆመመ ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ያለመራመድ ፣ ያለማደግና ያለመለወጥ ስሜት በሚሰማን ጊዜ የእግዚአብሄርን ፊት መፈለግፍ ወርቃማ አጋጣሚ ነው፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እግዚአብሄር ትኩረታችን ፈልጎና ከእኛ ጋር ህብረትን ለማድረግ ናፍቆን ሊሆን ይችላል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እርሱን በግል እንድንፈልገው ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እግዚአብሄር ወደሚቀጥለው የህይወታችን ምእራፍ ሊያሻግረን መለወጥ ያለብንን ነገር እንድንለውጥ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እግዚአብሄር የነበርንበት የህይወት ምእራፍ በመዝጋት ስለሚቀጥለው የህይወት ምእራፍ እርሱን እንድንፈልገውና ምሪትን እንድንቀበል ምልክት እየሰጠን ሊሆን ይችላል፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11-13
2.     በእግዚአብሄር ቃል ራሳችንን ማየት
መራመድ እንዳቆምን የተሰማን እውነትም እድገታችን ቆሞ ሊሆን ይችላል፡፡ እድገትን ሊያቆም የሚችለውና ከእግዚአብሄር ጋር ያለንንን ግንኙነት እና ህብረት የሚያበላሸው ሃጢያት እና አለመታዘዘ ነው፡፡ እግዚአብሄር የመራንን መሪት ሳንከተል ሌላ ምሪትይ እንዲሰጠን መፈለግ አንችልም፡፡ እግዚአብሄር ያዘዝንን ትእዛዘ በእምነት ሳንፈፅጽም ህይወታችን እንዲለወጥ መጠበቅ የለብንም፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክለውን እምነታችንን ሳንጠቀም እምነት እንዲጨምርልን መፀለይና እምነት እንዳልጨመርን ሊሰማን አይገባም፡፡
ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 17፡5-6
እግዚአብሄር ያስረዳንን የእግዚአብሄርን ቃል ወተት መረዳት ሳንታዘዝ ጠንካራ ምግብ ለመመገብ መሞከር አይቻልም፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ልባችንን በመፈተሽና እርምጃችንን በእግዚአብሄር ቃል በመመርመር እየተራመድን ከሆነ ቆመን ከሆነ እግዚአብሄርን በማመስገን በዚያው መቀጠል ይገባናል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ራሳችንን ስንፈትሽ የሳትነው ነገር ካለ በእግዚአብሄር ፊት ሃሳባችንን ለውጠን የእግዚአብሄርን ቃል ለመታዘዝ መወሰን አለብን፡፡
ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። የያዕቆብ መልእክት 1፡22
3.     የእግዚአብሄርን እርምጃ መታገስ
እርምጃችን እንደቆመ እና ህይወታችን እንዳልተለወጠ ሲሰማን ስለእግዚአብሄር አሰራር ያለንን አመለካከት መፈተሽ አለብን፡፡ እግዚአብሄር አይቸኩልም፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። መጽሐፈ ምሳሌ 2820
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። መጽሐፈ ምሳሌ 1311
እግዚአብሄር ነገሮችን የሚያደርገው በራሱ ጊዜ እንጂ በእኛ ጊዜ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር መልካም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ነገሮችን ውብ የሚያደርገው በጊዜው ነው፡፡
ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ መጽሐፈ መክብብ 3፡1፣11
ከእኛ የሚጠበቀው በጊዜው መልካም ማድረግ ፣ መልካምን በማድረግ አለመታከትና እንዲሁም መታገስና መጠበቅ ነው፡፡
ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡9
የእግዚአብሄር ፈቃድን ካደረግን በኃላ እንኳን የተሰጠንን የተስፋ ቃል እስክናገኝ መፅናት አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድን ስላደረግን ብቻ እግዚአብሄር ነገሮች ከመቀፅበት ይሆኑልናል ብለን ካሰብን እንሳሳታለን፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ወደ ዕብራውያን 10፡36
4.     ስለደረስንበት ደረጃ እግዚአብሄርን ማመስገን
ብዙ ጊዜ ህይወታችን እድገት እንደሌለው የሚሰማን ልንሄድበት የምንፈልገውንና ያለንበትን ደረጃ ስናነፃፅር ብቻ ነው፡፡ እውነት ነው የምንሄድበትንና ያለንበትን ማነፃፀር መልካም እና አስፈላጊም ነው፡፡  ነገር ግን የመጣንበትንና ያለንበትን ስናስተያይ ደግሞ ምን ያህል ህይወታችን እንደተለወጠ እናስተውላለን፡፡ ቀድሞ የነበርንበትንና አሁን ያለንበትን ስናስተያይ አሁን እየኖርነው ያለነው ህልማችንን እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ የነበርንበትንና ያለንበትን ደረጃ ስናነፃፅር አሁን ያለንበትን ደረጃ ከጊዜ በፊት ሊደረስበት የማይችል የመሰለን እንደተራራ የገዘፈብን የህይወት ደረጃ እንደነበረ እናስተውላለን፡፡
ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡17-18
5.     እየታዘዝነው ያለውን የእግዚአብሄርን ቃል በመታዘዝ መቀጠል  
ህይወታችን ካለ እድገት እንደቆመ ሲሰማን እየታዘዝነው ያለውን የእግዚአብሄርን ቃል በመታዘዝ መቀጠል ይኖርብናል፡፡ እድገት የሚመጣው ጥቃቅን የሚመስሉ የእለት ተእለት ተደጋጋሚ ነገሮችን በፅናት በማድረግ ነው፡፡ እውነተኛ እድገት የሚመጣው ከውስጥ ወደ ውጭ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ከሰማን ከታዘዝንና ከፀናንበት እድገትና ለውጥ የማይቀር ነገር ነው፡፡
በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። የሉቃስ ወንጌል 8፡15
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ጌታ #ኢየሱስ #ፅናት #መጠበቅ #ምስጋና ##ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መለወጥ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment