እኛ እያንዳንዳችን በተለያየም ምክኒያት ወደዚህ
ምድር መጥተናል፡፡ አንዳንዶች በፖለቲካ ተሰደው መጥተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ህይወትን ለመለወጥ በሚል ምክኒያት በዚህ አገር ይኖራሉ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ እህት ወንድም ተከትለው መጥተዋል፡፡ ሌሎቹ በጋብቻ የመጡ ብዙ አሉ፡፡
መልካምን ነገር የሚሰጠው እግዚአብሄር ነው፡፡
እያንዳንዳችን የመጣነው እግዚአብሄር በርን ከፍቶልን ነው፡፡ እግዚአብሄር በርን ካልከፈተ ማናችንም እዚህ አገር አንመጣም ነበር፡፡
ብዙዎች እዚህ አገር ለመምጣት እየተመኙና እየፀለዩ
ያልተሳካላቸው አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከእኛ እዚህ አገር ለመምጣት ከነበረን እድል በላይ በላይ የተሻለ እድል ኖሮዋቸው ያልመጡ አሉ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ ሌሎች አውሮፓ አገሮችና አሜሪካ የመሄድ እድል አዘይነበራቸው እግዚአብሄር እዚህ ስለከፈተላቸው ብቻ ልባቸው ተነሳስቶ
መጥተዋል፡፡
ብዙዎቻችን ባለታሰበ መልኩ በሮች ተከፍቶልን የመጣነው
እግዚአብሄር ስለፈቀደ ነው፡፡
ይህን አገር የሰጠን ሰው አይደለም፡፡ ይህን አገር
የሰጠን እግዚአብሄር ነው፡፡ እንደሰው ቢሆን አልቆልን ነበር፡፡ እግዚአብሄር እንደሰው አይደለም፡፡
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን እስራኤል እንዲህ ይበል፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፥ ቍጣቸውን በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር፤ በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ፈሳሽ ባለፈ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር። ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ። መዝሙረ ዳዊት 124፡1-6
እዚህ አገር ያለነው በሰው ችሮታ አይደለም፡፡
እዚህ አገር ያለነው የእግዚአብሄር ፈቃድ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ እዚህ አገር ያለነው እግዚአብሄር ሰዎችን ስለተጠቀመ ነው፡፡ እዚህ
ምድር ላይ ያለነው እግዚአብሄር ሰዎችን ስለያዘልን ነው፡፡ በዚህ ምድር ያለነው እግዚአብሄር ላባን ለያቆብ በህልም እንደገሰፀው
በእግዚአብሄር ገስፀው ነው፡፡
የአባቴ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት ከእኔ ጋር ባይሆንስ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ድካም አየ፥ ትናንትም ገሠጸህ። ኦሪት ዘፍጥረት 31፡42
እዚህ አገር ያሉ አንዳንድ ሰዎች እኛ እዚህ አገር
መኖራችን አይፈልጉም፡፡ አንዳንዶቹ በህይወታቸው ስላለው ችግር ሁሉ ተጠያቂ እንደሆንን የሰይጣንን ውሸት ያምናሉ፡፡ አንዳንዶቹ እኛ
ብቻ ሳይሆን ከሌላ አገር የመጡት የውጭ ዜጎች ሁሉ ቢወጡላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ችግራቸውን አይፈታም፡፡
እኛን ለማስወጣት ብዙም ጊዜ ሞክረዋል፡፡ በፊት
በፊት ሊያስወጡን ቢፈልጉ በቀላሉ እንደሚያስወጡን ያስቡ ነበር፡፡ አሁን ግን ብዙ ሙከራቸው ብዙ ጊዜ ከሸፈ በኃላ እኛን ማስወጣት
እንደማይችሉ ተረድተውታል፡፡ አሁን ያላቸው አንድ መሳሪያ ማስፈራራት ነው፡፡ እኛን ለማስፈራራት ብዙ አጭር የስልክ የፅሁፍ መልክቶች
በዋትስአፕ በመሳሰሉት ለአመታት ሲሰራጩ ቆይተዋል፡፡ እኛ ፈርተን እንድንወጣ ብዙ ማስፈራሪያዎች ተደርገዋል፡፡ ፍርሃት ከሰይጣን
ነው፡፡ ፍርሃትን የሚጠቀመው ሰይጣን ነው፡፡ የፍርሃት አላማ ደግሞ እኛን ከመኖር ከመስራትና ከመውጣት ከመግባት ማገድ ነው፡፡ ፍርሃትን
ሰምተን መኖርን ከቆምን ሰይጣን ባለድል ይሆናል፡፡ ፍርሃትን ሳንሰማ በጥንቃቄ ከኖርን ሰይጣን የመስረቅ ግቡን አይመታም፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡10
ልንፈራው
የሚገባው አግዚአብሄርን ብቻ ነው፡፡ ልናመልከውና ልንቀድሰው የሚገባው እግዚአብሄርን ብቻ ነው፡፡ ክፉ በማድረግ የሃገሪቱን ህግ
በመጣስ መከራን አንቀበል እንጂ ከዚያ ውጭ ያለውን ፈርተን መቆም የለብንም፡፡ በሚጠብቀን በእግዚአብሄር ታማኝነት ታምነን መጠንቀቅ
እንጂ መቆም አይገባንም፡፡
ማስፈራራታቸውንም
አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3
ለአመታትም በተነሱት ጥቃቶች እግዚአብሄር ከልሎናል፡፡
እግዚአብሄር ከብዙዎቹ ጥቃቶች አስመልጦናል፡፡ ከጥቃቱ እቅድ አንፃር ምልክቱን ብቻ ነው ያየነው፡፡ ሰዎች የፈለጉትን አላደረጉብንም፡፡
እግዚአብሄር ታማኝነቱን በተደጋጋሚ አሳይቶናል፡፡ እግዚአብሄር አብዝቶናል አስፍቶንማል፡፡
እንደማንኛውም ህዝብ በድህነትና በስራ አጥነት
የሚሰቃይ ህዝብ ቢሆንም በአጠቃላይ ህዝቡ መልካም ህዝብ ነው፡፡ ካልወጣችሁ እንዲህ እናደርጋችሁዋለን የሚለው ማስፈራሪያ በጥቂት
በቅናተኞችና በክፉ ሰዎች የሚጠቀመው የሰይጣን ምኞት ነው፡፡ ሰይጣን ደግሞ የተሸነፈ ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን የተፈረደበት ጠላት ነው፡፡
ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት
ነው። የዮሐንስ ወንጌል
16፡11
እዚህ አገር ያለነው ሰይጣን አስኮናኞች ኑሩ ስላለን
አይደለም፡፡ እዚህ አገር ያለነው በሰይጣን ምህረት አይደለም፡፡ እዚህ አገር ያለነው በሰይጣን በጎ ፈቃድ አይደለም፡፡ እዚህ አገር
ያለነው በእግዚአብሄር ምህረት ነው፡፡
ዜጎቹ በዚህ ምድር እንዲወለዱ ያደረገው እግዚአብሄር
እኛንም እዚህ ምድር እንድንገባና እንድንኖር በሮችን ከፍቶዋል፡፡ ይህን ምድር እንደ ትውልድ አገር ለዜጎቹ የሰጣቸው እግዚአብሄር
እኛንም ይህንን ምድር እንድንሰራበት እና እግዚአብሄርን እንድናመልክ ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ምድር እንዲወለዱ የፈቀደላቸው እግዚአብሄር
እኛም እዚህ ምድር መጥተን በህይወትም በቃልም ወንጌልን እንድንሰብክ የእግዚአብሄርን በጎነት እንድንናገር ልኮናል፡፡
በእግዚአብሄር እይታ እነርሱ ለመኖር መብት እንዳላቸው
ሁሉ እኛም ለመኖር መብት አለን፡፡
ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ። መዝሙረ ዳዊት 24፡1
እዚሁ ምድር ካልቀጠልንና በዚህ ምድር መኖሪያ
ጊዜያችን ሲያበቃ ደግሞ እግዚአብሄር ወደምድራችን ይመልሰናል ወይም ደግሞ ሌሎች ምድሮችን ይከፍትልናል፡፡ እዚህ ምድር ኑሮዋችንን
አገልግሎታቸንን እስክንጨርስ የትም አንሄድም፡፡ በችኮላና በፍርሀት ምንም አናደርግም፡፡
እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም። ትንቢተ ኢሳይያስ 52፡12
እንዲያውም በሚቀጥሉት ዘመናት ልጆቻቸን አድገው
ተምረው ሰርተው አገሪትዋን ያሳድጋሉ፡፡ በሚቀጥሉት ዘመናት ልጆቻችን በፖለቲካ በኢኮኖሚ በትምህርት በጤና ሃገሪቱንም ራሳቸውንም
ያድጋሉ ይሰፋሉ፡፡
በዚህ አገር የህንድ ማህበረሰብ እንዳለው ሁሉ
በሚመጡት ዘመናት የኢትዮጲያ ማህበረስብ እየበዛ እየሰፋ እያየለ ይሄዳል፡፡ ከሌሎች አገሮች መጥተው በዚህ እንደሚኖሩ ሌሎች ትልልቅ
ማህበረሰቦች ሁሉ የኢትዮጲያ ማህበረሰብ ይሰፋል ይበዛል ያብባል፡፡
በሃገሪቱ ላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንረዳለን፡፡
የፖለቲካ መሪዎች ለህዝቡ እንደ አባት መሆን ነበረባቸው፡፡ ህዝቡን በቅንንነት ማገልገል ትተው ራሳቸውን በሚያበለፅጉ በአንድንድ
የፖለቲካ መሪዎች እናዝናለን፡፡ እግዚአብሄር በጥበብ የሚያስተዳድሩዋትን በጎ መሪዎችን እንዲሰጣት ስለምድሪቱ እንፀልያለን፡፡
የስደተኛ ችግር የደቡብ አፍሪካ ብቻ ችግር አደለም፡፡
ከአሜሪካ እስከአውስትራሊያ ከኖርዌይ እስከ ጃፓን የስደተኝነት ችግር የአለም ችግር ነው፡፡
በምድራቸው ያለውን የዜጋውንም ሆነ የስደተኛውን
ህዝብ ደህንነት መጠበቅ የአሩ መሪዎች ሃላፊነት ነው፡፡ በምድራቸው የሚኖረውን ህዝብ ስኬታማ ማድረግ አገሪትዋን ስኬታማ ማድረግ
ነው፡፡ በምድራቸው እስከኖርን ድረስ የአገሪቱ የሰው ሃብት ነን፡፡ እኛን መቀበልና በሚገባ በፍትህና በሰላም ማስተዳደር ክብራቸው
ነው፡፡
በምድሪቱ ላይ እንድንኖር የተቀበሉንን ሰዎች እናመሰግናለን፡፡
ከሁሉም በላይ በምድሪቱ ላይ እንምድንኖር ሞገስን የተሰጠንን እግዚአብሄርን ከልባችን አናመሰግናለን፡፡
በዚህም ምድር ላይ ያለነው ሌላ ምድር ስለሌለ
አይደለም፡፡ የተሳካልን በዚህ መድር ላይ ስላለን አይደለም፡፡ የተሳካልን እግዚአብሄር ስላሳካልን ነው፡፡ በምድሪቱ ላይ የምንኖረው
የሚበላና የሚጠጣ ፈልገን አይደለም፡፡ በዚህ ምድር ላይ ያለነው እግዚአብሄር በምድሪቱ ላይ የመኖራችን ልዩ አላማ እንዳለው ስለምናንም
ነው፡፡ በምድሪቱ ላይ ያለነው ሌሎችን ለማገልገል እኛም ለመጠቀም ነው፡፡
የትኛውም አገር የራሱ ጥቅም እና የራሱ ተግዳሮት
እንዳለው ሁሉ ደቡብ አፍሪካም የራሱ በጎ ጎኖችና ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ተግዳሮቶቹን በትግስት አልፈን እግዚአብሄር በህይወታችን ያየውን
አላማ ከመፈፀም የሚያግደን የለም፡፡ ይህን የእግዚአብሄርን አላማ ለመፈፀም ምንም የሚያግደን ነገር አይኖርም፡፡ ይህን የእግዚአብሄር
ፈቃድ ለመፈፀም በፊታችን የሚቆም ማንም ሰው አይኖርም፡፡
በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ
ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡5
በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ።
መዝሙረ ዳዊት 37፡3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር
share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አትፍራ #ታመን #መሪ
No comments:
Post a Comment