Popular Posts

Saturday, September 14, 2019

መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው




በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ። በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡18-19
ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ። ከእናንተ መካከል እውነተኞቹ ተለይተው ይታወቁ ዘንድ፣ ይህ መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው። (አዲሱ መደበኛው ትርጉም) 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡18-19
ሃዋርያው ጳውሎስ በቤተክርስትያን ውስጥ ስለተነሳው መከፋፈልና እና መለያየት ሲናገር መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው ይላል፡፡
ቤተክርስትያን ከእውነት ቃል ስታ ካለመለያየት በአንድነት ልትቀጥል ትችላለች፡፡ ቤተክርስትያን ከእውነት ቃል መሳትዋ ለእግዚአብሄርም ለእግዚአብሄርም ህዝብ አይጠቅምም፡፡
ቤተክርስትያን እውነትን በማመቻመች ካለመከፋፈል በአንድነት መቀጠልዋ ለቤተክርስትያን ተልእኮ መሳካት እንቅፋት ነው፡፡
ቤተክርስትያን በባህል እና በወግ ተጠላልፋ እግዚአብሄር በምድር ላይ ያስቀመጣትን የወንጌል ስብከት አላማ ዘንግታ ካለመለያየት በአንድነት መኖርዋ የቤተክርስትያንን ንፅህና አያሳይም፡፡ 
ቤተክርስትያን እውነትን ጥላ በሃይማኖት መልክ ብቻ ባለመከፋፈልና በውሸት አንድነት ልትቀጥል መቻልዋ ይህ ከመለያየት የከፋ ውድቀት እንጂ የቤተክርስትያንን ስኬት አያሳይም፡፡
በቤተክርስትያን ውስጥ ውዝብ ከተነሳ ውዝግቡ ቤተክርስትያን በትጋት መፍታት ያለባትን ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ በቤተክርስትያን ውዝግብ ተነሳ ማለት የተሳሳቱት መሪዎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ወይም በቤተክርስትያን ወዝግብ እና መለያየት ተነሳ ማለት ለውዝግቡ መነሳት ጥፋተኞቹ ተከታዮች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የተሳሳቱት የቤተክርስትያን ችግር መንስኤ የሆኑት የቤተክርስትያን መሪዎች ወይም ተከታዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የቤተክርስትያን መሪዎች ወይም ተከታዮች ለውዝግቡ እና ለመለያየቱ ሁለቱም ያደረጉት አስተዋፅኦ ሊኖር ይችላል፡፡ የቤተክርስትያን መሪዎችም ይሁን ተከታዮች ይብዛም ይነስም ውዝግቡን በያዙበት መንገድ ሁለቱም ጥፋተኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በቤተክርስትያን ውዝግብ በሚነሳ ጊዜ መሪዎችም ሆነ ተከታዮች ሰይጣን ስፍራን እንዳያገኝ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ መሪዎችም ሆነ ተከታዮች ስለእውነት ብለው ችግሩን ከማባባስ ይልቅ ይልቅ ለመፍትሄው አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡  
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።  ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27
ከመሪዎችም ይሁን ከተከታዮች ወገን ቅን ልብ ይጠይቃል፡፡ ጥያቄውን የሚጠይቁት ተከታዮች ጥያቄ የምጠይቀው በእውነት ነው? ብለው ራቸውን ደጋግመው ሊጠይቁ ይገባል፡፡  
እግዚአብሄር ከመሪዎችም ይሁን ከተከታዮችም ወገን ለመቆም እውነትን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ሃይል ካለው ፣ ገንዘብ ካለው ፣ ዝና ካለው ወይም ደግሞ ተሰሚነት ካለው ወገን ጋር ሳይሆን እውነት ያለው ሰው ከእርሱ ጋር ይሆናል፡፡ ምንም ዝነኛ ባለጠጋ ታዋቂ ብንሆን ከእውነት ጋር መወገን እንጂ ከእውነት ተቃራኒ ሆነን ምንም ልናደርግ አንችለም፡፡ እውነት የሌለው ሰው ደግሞ መሪም ይሁን ተከታይ እግዚአብሄር አብሮት አይሆንም፡፡ መሪዎችም ይሁን ተከታዮች እውነት የያዙ ሰዎች ተቃውመው አይቀጥሉም፡፡ እውነት የያዙ ሰዎች እግዚአብሄር ከእነርሱ ጋር ይሆናል፡፡
ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡8
በአጠቃላይ ከእኛ የተለየውን ሰው ለመረዳት ቅንነት ይጠይቃል፡፡
ተከታዮች የምንጠይቀውን ጥያቄ በቅንነት መጠየቃችንን እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡ እግዚአብሄር ከማንም ጋር አይወግንም፡፡ እግዚአብሄር ከቅኖች ጋር ግን ይወግናል፡፡ የምንጠይቀውን ጥያቄ ስንጠይቅ ሌላ የተደበቀ አላማ አለን ወይስ የለንም? ብሎ ራስን መፈተሽ ይጠይቃል፡፡ የተደበቀ ምክኒያት ካለን ያንን ድብቅ አላማችንን መተው መመለስ ይጠበቅብናል፡፡ ልባችንን ፈትሸን የተደበቀ አጀንዳ እንደሌለን ካረጋገጥን ደግሞ ከእውነት ጋር መወገን ይጠበቅብናል፡፡ 
በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ 22፡24-26
እንደ መሪ ተከታዮች የሚጠይቁትን ጥያቄ በቅንነት ካየነው እና ለእውነተኛው ችግር መፍትሄ ለመስጠት ከሰራን ሃላፊነታችንነ ሁሉ እንወጣለን፡፡ እንደ መሪ ተከታዮች የሚጠይቁትን ጥያቄ በቅንነት ካየነው ሌላው ጥያቄ እግዚአብሄር የሚመልሰው ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሚጠየቅን ጥያቄ ካለምንም ቅድመ ግምት በቅንነት ካላየንና እንደዚህ ያሉት እንዲህ ሊያደርጉ ፈልገው ነው በማለት እውነተኛውን ጥያቄ ለመመለስ ቸል ካልን ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡ መሪዎች እውነተኛውን ጥያቄ በቅንነት ካላዩት እና በእውነተኝነት መመለስ ካልፈለጉ መሪዎቹ ተከታዮችን ተከታዮች ደግሞ መሪዎቹን ያጣሉ፡፡
በዚህ ወሳኝ ጊዜ የቤተክርስትያን መሪዎች ብስለት የሚለካው ከቁጣና ከእልህ ነፃ ሆነው እውነተኛ እንደሆነ የሚያምኑበትን ጥያቄ እንደ እግዚአብሄር ቃል በመመለሳቸው ነው፡፡
ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። የያዕቆብ መልእክት 1፡19-20
ቅንነት ካለ ፍቅር ካለ እውነተኝነት ካለ ተቀራርቦ መነጋገር ብዙ ችግሮችን ይፈታል፡፡ ነገር ግን ቅንንት ከጎደለ ፍቅር ከሌለና እውነተኝነት ከጠፋ ሊፈታ የሚችለው ችግር ሁሉ ገዝፎ መበታተንን ያመጣል፡፡ እግዚአብሄርን በቅንነት ማገልገል የሚፈልግ ሰው እና ድብቅ አጀንዳ የሌለው ሰው በመቀራረበ በመነጋገር የሚያጣው ምንም ነገር የለም፡፡
አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡5
እግዚአብሄርን በቅንነት ማገልገል የሚፈልግ ሰው እና ድብቅ አጀንዳ የሌለው ሰው ከእርሱ የተለየውን የሌላውን ወገን ሃሳብ ለመረዳት በትህትና ይቀርባል፡፡ እግዚአብሄርን በቅንነት ማገልገል የሚፈልግ ሰው እና ድብቅ አጀንዳ የሌለው ሰው ባልንጀራው ከእርሱ እንዲሻል አስቦ በትህትና ይቆጥራል፡፡ እግዚአብሄርን በቅንነት ማገልገል የሚፈልግ ሰው እና ድብቅ አጀንዳ የሌለው ሰው ሌላውን ለማስደሰት የሌላውን እውነተኛ ጥያቄ ለመመለስ ይሰራል፡፡ 
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡3
የቤተክርስትያን መሪዎች ተቀራርበው ለመነጋገር ትህትና ከጎደላቸው ራሳቸው መሸከም የሚገባቸውን የቤተክርስትያንን አስተዳደር ሸክም በከንቱ ለተከታዮች ያሸክማሉ፡፡ የቤተክርስትያን መሪዎች ተቀራርበው ለመነጋገር ትህትና ከጎደላቸው አንዱ ስለሌላው ክፋትን እየተናገሩ ተከታዮቻቸውን የራሳቸው ለማደረገ በሚያደርጉት ክፉ ዘመቻ ተከታዮች መስማት የሌላባቸውን የቤተክርስትያን ሚስጥር በመስማትና መሸከም የሌለባቸውን ሸክም ካላቅማቸው በመሸከም ይበተናሉ፡፡ ራሳቸው መሸከም የሚገባቸውን የቤተክርስትያንን አስተዳደር ሸክም በከንቱ ለተከታዮች ያሸክማሉ፡፡
በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡19
አሁን ፈተናው ማነው ቅን በቅንነት ጥያቄን የጠየቀ ወይም በቅንንት መልስን የመለሰ የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሄር በደፈናው የሚቆመው ከመሪም ሆነ ከተከታይ ጋር ሳይሆን ከቅኖች ጋር ነው፡፡
አሁን ፈተናው ማነው እውነተኛ እውነትን የያዘ ተከታይ እውነትን የያዘ መሪ የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሄር ከመሪም ሆነ ከተከታይ ጋር ሳይሆን ከእውነተኛ መሪም ሆነ ተከታይ ጋር ይቆማል፡፡
አሁን ጥያቄው በእርጋታና በፍቅር ውዝግቡን ሊፈታ የሚችል እውነተኛው ማነው የሚለው ነው፡፡
አሁን ፈተናው ማነው በፍቅር የሚመላለሰው ተከታይ በፍቅር የሚመላለስ መሪ የሚለው ነው፡፡ አሁን ፈተናው ማነው ከጥላቻ ራሱን የሚጠብቅ መሪና እና ተከታይ የሚለው ነው፡፡ ፍቅር የሌለበት ነገር ምንም አይጠቅምም፡፡ እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሄር ይኖራል፡፡ እግዚአብሄር ከፍቅር ሃሳብ ጋር ይወግናል፡፡ እግዚአብሄር በጭፍኑ ከመሪም ሆነ ከተከታይ ጋር ሳይሆን ከእውነተኛ ወገን ጋር ይቆማል፡፡
አሁን ፈተናው ለወገኔ ይጠቅማል በማለት የሚመላለሰው መሪው ነው ተከታዪ የሚለው ነው፡፡ አሁን ፈተናው ማነው በወገንተኝነት እና በራስ ወዳድነት የሚኖረው የሚለው ነው፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡3-4
እውነተኛውን ጥያቄ ጥያቄ ከመጠየቅና እውነተኛውን መልስ ከመመለስ ይልቅ በቡድን ተካፋፍሎ ድንጋይን መወርወር ቤተክርስትያንን ያዳክማል እንጂ ለማንም አይጠቅምም፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
 ለተጨማሪ ፅሁፎችhttps://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶችhttps://www.youtube.com/user/awordm/videos
#መለያየት #አዲስ #መዋጀት #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ንስሃ #አቁማዳ #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ኦርቶዶክስ #ተዋህዶ #ጌታ #ማሪያም #መላእክት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ሰላም ትግስት #ልጅ

No comments:

Post a Comment