Popular Posts

Sunday, September 22, 2019

ሁልጊዜ የፀሎት መልሳችንን የምንቀበልባቸው አምስቱ ጥበቦች



ከልባችን የፀለይናቸው ፀሎቶች ሁሉ ተመልሰዋል፡፡
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የማቴዎስ ወንጌል 7፡7
የሚለምነውም ሁሉ ይቀበላል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር መንገድ እንጂ በእኛ መንገድ አንቀበልም፡፡ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ጊዜ እንጂ በእኛ ጊዜ አናገኝም፡፡ ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡ ነገር ግን የሚከፈትልን በእኛ ሁኔታ ሳይሆን በእግዚአብሄር ሁኔታ ነው፡፡
የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። የማቴዎስ ወንጌል 7፡8
1.      እግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን በእርግጥ ይመልሳል፡፡ እግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን በችኮላ አይመልስም፡፡ እግዚአብሄር ፀሎታችንን በጊዜው እንጂ በችኮላ አይመስለስም፡፡ እግዚአብሄር ማንም አይቀድመውም፡፡ እግዚአብሄር ጊዜ አያልፍበትም፡፡ እግዚአብሄር ከአላማው ጋር እንጂ ከጊዜ ጋር አይሮጥም፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ነገር ስለሚያይ እኛ እንደምንቸኩል አይቸኩልም፡፡ እግዚአብሄር እኛ በቸኮልንበት ጊዜ የፀሎት መልሳችንን በችኮላ ስላልመለሰ ያልተመለሰ ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚለምነው ሁሉ በጊዜውና በሰአቱ በእግዚአብሄር መንገድ ይቀበላል፡፡
ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? የሉቃስ ወንጌል 18፡1፣7፣8
2.     የፀሎት ምለሳችን ሁሉ ይመጣል፡፡ ነገር ግን የፀሎት መልሳችን በጣም በጓጓን ጊዜ ላይመለስ ይችላል፡፡ ለፀሎት መልሳችን በጣም መጓጓት አይናችንን ከእግዚአብሄር ላይ አንስተን የፀሎት መልሳችን ላይ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለፀሎት መልሳችን በጣም መጓጓት የፀሎት መልሳችንን ጣኦት እንድናደርገው ያደርገናል፡፡ ለእግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን ለመመለስ ትክክለኛው ጊዜ ከመጠን ያለፈ መጓጓታችን ሲበርድልን ነው፡፡ እግዚአብሄር አንዳንዴ ፀሎታችንን የሚመልሰው ከመጠን ያለፈ ጉጉታችንን ከጨረስን በኃላ ነው፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላል ነገር ግን የለመንነውን ሁሉ ከመጠን በላይ በጓጓን ጊዜ አንቀበልም፡፡ ከመጠን በላይ መጓጓት የፀሎት መልሳችንን እንደሚገባ እንዳንይዘው ያደርገናል፡፡ ለፀሎት መልሳችን ከመጠን ያለፈ መጓጓት የፀሎት መልሳችንን እንድናመልከው ይፈትነናል፡፡
3.     የፀሎት መልሳችን በቅንጦት አይመለስም፡፡ እግዚአብሄር የሚያቀርበው እንደፍላጎታችን መጠን ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ፍላጎት ባለብን የህይታችን ክፍል በብዙ እንቀበላለን፡፡ ብዙ ፍላጎት በሌለን በህይወታችን ክፍል በብዙ አንቀበልምን፡፡ ብዙ ፍላጎት ላለበት ሰው እግዚአብሄር በብዙ ያቀርብለታል፡፡ ጥቂት ፍላጎት ላለለው ሰው በብዙ አያቀርብም፡፡ እግዚአብሄር በብዙ ካቀረበለን አሁንም ባይሆን ወደፊት ብዙ ፍላጎት እየመጣ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከላቀረበ ፍላጎት የለብንም ማለት ነው ብለን ማመን እና እግዚአብሄርን ማመስገን አለብን፡፡ ቀድሞ እንኳን ብዙ ካቀረበ ብዙ ፍላጎት እየመጣ ነው ብለን ለወደፊት ማስቀመጥ እንጂ ሁሉንም አቅርቦት በምቾቶቻችን መክፈል ወይም በቅንጦት ላይ ማዋል የለብንም፡፡
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡3
4.     የፀሎት መልሳችን ሞቲቫችን ሲጣራ ይመልሳል፡፡ ብዙ ጊዜ ስንፀልይ በሁለት መነሻ ሃሳቦች እንፀልያለን፡፡ አንዱ በፀሎት መልሳችን እግዚአብሄርን የማክበር ንፁህ የልብ መነሻ ሃሳብ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሌላው ሰው መብለጥ ታዋቂ መሆን ባለጠጋ መሆን ወይም ደግሞ ከሰው ሁሉ በልጦ ሃያል መሆን ነው፡፡ እግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን በእኛ ጊዜ ሳይሆን በራሱ ጊዜ ሲመልስ ንፁህ ያልሆነው የልባችን መነሻ ሃሳብ ከቀነሰ በኃላ ነው፡፡ ስጋችን የፀሎት መልሳችን እንዲመልስ የሚፈልገው ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅም ሳይሆን ለራሱ ምቾት ነው፡፡ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል ነገር ግን ብዙ ጊዜ የፈለግነውን ሁሉ እንዳለገኘን የሚሰማን የስጋ መነሻ ሃሳባችን ከጠፋ በኃላ የጸሎት መልሳችን ስለሚመለስ ነው፡፡
ሃና ልጅ የምትፈልገው የልብዋ መነሻ ሃሳብ ለእግዚአብሄር መልሳ ለመስጠት ሲሆን እግዚአብሄር መለሰላት፡፡
እርስዋም፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 1፡11
5.     የፀሎት መልሳችን ካደግን በኃላ ይመለሳል፡፡ ክርስቶስን የምንከተል ሁላችንም በየቀኑ እያደግን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፀሎት መልሳችን እንዳልተመለሰ የሚሰማን ከፀሎት ጥያቄው አልፈን ወደሌላ የፀሎት ጥያቄ ውስጥ ከገባን በኃላ ስለሚመለስ ነው፡፡ እኛ ህይወታችን አድጎና የፀሎት ጥያቄያችን አድጎ ወደሌላ ከፍ ወዳለ የፀሎት ጥያቄ ውስጥ ከገባን በኃላ የበፊቱ የፀሎት መልሳችን ስለሚመጣ ያልተመለሰ ይመስለናል፡፡ የሚፈልገውም ያገኛል፡፡ የቀድሞውን የፀሎት ርእሳችንን አልፈን ሌላ ነገር በመፈለግ ላይ ስለተጠመድን የመጀመሪያውን የፀሎት መልስ ያገኘን  አይመስለንም፡፡
አብዝተን እንድንቀበል አብዝተን እንለምን፡፡ መቼ እንደምናገኝ ሳናስብ አብዝተን እንፈልግ፡፡ እንዴት እንደሚከፈት ሳንጨነቅው አብዝተን አናንኳኳ፡፡  
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። የማቴዎስ ወንጌል 78
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ለምኑ #ፈልጉ #አንኳኩ #ይቀበላል #ያገኛል #ይከፈትለታል #ቃል #ብልፅግና #ሃብት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርቃል  #የእግዚአብሔርፈቃድ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment