Popular Posts

Monday, September 2, 2019

ዓለም አቀፋዊው የአገልግሎት ህግ



ሁላችንም እግዚአብሄር በምድር ያስቀመጠንን አላማ ፈፅመን ማለፍ እንፈልጋለን፡፡ ሁላችንም እግዚአብሄርን አገልግለን ማለፍ እንፈልጋለን፡፡ የሁላችንም ህልምና ጥማት ሰዎችን በማገልገል ጌታን እንደሚገባው ማገልገል ነው፡፡ የሁላችንም ቅናት በዘመናችን የእግዚአብሄርን ፈቃድ አገልግለን ማለፍ ነው፡፡
ባልረካንበትና ባልጠገብንበት ዘርፍ ሌላውን ማርካትና ማጥገብ አንችልም፡፡ ባልተገለገልንበትና ባልተጠቀምንበት ዘርፍ ሌላውን መጥቀም አንችልም፡፡ ባልረካንትና በቃኝ ባላልንበት የህይወት ክፍል ሌላውን ማገልገል አንችልም፡፡
የሰው ፍላጎት አያልቅም፡፡ ፍላጎታችንን የምንገታው እኛው ነን፡፡ ራሳችንን የምግዛው እኛ ነን እንጂ አንድ ቀን ፍላጎታችን አያልቅም፡፡ አንድ ቀን ፍላጎታችን ያበቃል ብለን ካሰብን ጌታን ሳናገልግል እናልፋለን፡፡ ፍላጎት አያልቅም፡፡ ፍላጎት አያበቃም፡፡ ለፍላጎት ገደብን የምናበጀው እኛ ነን፡፡ የሰው ፍላጎት በራሱ ገደብ የለውም፡፡ ለፍላጎታችን ገደብ የሚኖረው እኛ ገደብ ባበጀንለት መጠን ብቻ ነው ፡፡
ያለኝ ይበቃኛል ማለት ያለብን እኛ ነን፡፡ እኛ ነን ከዚህ በላይ አያስፈልገኝም ማለት ያለብን፡፡ ከዚህ በላይ ምን ይሰራልኛል ብለን ተጨማሪን ነገር ከመከተል መመለስ ያለብን እኛ ነን፡፡ እኛ ነን እኔ በቃኝ ላለው ደግሞ ላካፍል ማለት ያለብን፡፡ ከዚህ በላይ አያስፈልገኝንም በማለት ፍላጎታችንን መግታት ያለብን እኛ ነን፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6-8
ሌላውን ማገልገል የምንችለው በቃኝ ባልን መጠን ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም አገልግሎታችን ያለኝ ይበቃኛል ከሚለው አስተሳሰባችን ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡ አገልግሎታችን በቃኝ ካልንበት መጠን በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ በህይወታችን 10 በመቶ ያለኝ ይበቃኛል ካለን ማገልገል የምንችለው 10 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በህይወታችን 50 በመቶ ያለኝ ይበቃኛል እያልን ከዚያ በላይ ማገልገል የማይታሰብን ነው፡፡ አይበቃኝም ብለን በምስኪንነት አስተሳሰብ የዋጥነውን ለሌላው ማካፈል አንችልም፡፡ ለሌላው ማካፈል የምችለው በቃኝ ብለን ያስተረፍነውን ብቻ ነው፡፡
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11
ራሱን ያማጠነ ሰው ብቻ ነው ለሌላው መትረፍ የሚችለው፡፡ ሌላውን የምንጠቅመውና የምንባርከው ራሳችንን ባማጠንንበት መጠን ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#መሰረታዊፍላጎት #ይበቃኛል #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment