Popular Posts

Thursday, September 26, 2019

በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ የመግባት አስሩ ጥቅሞች




1.      አፈጣጠራችን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ በመኖር እንዲሳካልንና እንዲከናወንልን ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ፈቃድ ሲወጣ ያልተሰራበትን ስሪት ለመስራት እንደመሞከር ነው፡፡ ቤት መጥረጊያ የተፈጠረበት አላማ አለው፡፡ ብረት መቁረጫ መጋዝ ደግሞ የተፈጠረበት ሌላ አለማ አለው፡፡ ከእግዚአብሄር ፈቃድ መውጣት ቤትን ለመጥረግ የተሰራ መጥረጊያን ብረትን ለመቁረጥ እንደተሰራ እንደመጋዝ እንደመጠቀም ነው፡፡ 
2.     ክብራችን ያለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመታዝ ውስጥ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከመታተዝ ሲወጣ ክብሩን ያጣል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን በመታተዝ በንግስና እንዲኖር ተፈጥሮአል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ፈቃድ ሲስተው ከንግስናው ይሻራል፡፡
ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ኦሪት ዘፍጥረት 2፡17
3.     ስልጣናችን ያለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማድረግ ውስጥ ነው፡፡ የሰው ስልጣን የሚመነጨው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ነገሮችን ሊገዛ የሚችለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማድረግ ለእግዚአብሄር ሲገዛ ብቻ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሲያጣው ስልጣኑን ያጣል፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ፈቃድ መከተል ቸል ሲል ነገሮች ቸል ይሉታል፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከመከተል ሲመለስ ነገሮች እርሱን ከመስማትና ከመታዘዝ ይመለሱበታል፡፡ 
ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። ኦሪት ዘፍጥረት 4፡12
4.     ጥበቃችን ያለው የእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ከማንኛውም የመድህን ድርጅት በላይ አስተማማኝ መድን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ከሰይጣን በላይ ሃያል ነገር ነው፡፡ ሰይጣን ብዙ ነገሮችን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰይጣን የእግዚአብሄርን ፈቃድ የያዘ ሰው ሊቋቋም አይችልም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚከተል ሰው ሰይጣንና በሰይጣን የሚመራ ሰው ሊያስቆመው አይችልም፡፡
በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡5
5.     ሰው በህይወቱ እውነተኛን ፍሬን የሚያየው በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ በመቆይት ብቻ ነው፡፡ ሰው በተለያየ ነገር ውስጥ ሊወጣና ሊወርድ ይችላል፡፡ ሰው ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካላገኘና ካላደረገው በስተቀር እውነተኛ ፍሬያማነት የህልም እንጀራ ነው፡፡
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። የዮሐንስ ወንጌል 15፡5፣8
6.     የደስታና የእርካታ ስሜታችን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ከመኖር ብቻ ይመጣል፡፡ እውነት ነው ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሲያደርግ በከፍታና በዝቅታ ያልፋል፡፡ ነገር ግን ህይወቱን መልስ ብሎ ሲያየው ለእግዚአብሄር በሚገባ የተኖረ ህይወት ብሎ መደሰትና መፈንደቅ የሚችለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ብቻ ነው፡፡ እውነተኛን ደስታን የሚያጣጥመው ፈቃዱን የሚያደርግ ሰው ብቻ ነው፡፡ ምንም ዋጋ ቢያስከፍል እውነተኛን እርካታን የሚረካው ፈቃዱን የሚያደርግ ሰው ብቻ ነው፡፡  
ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” መጽሐፈ መክብብ 2:25
ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። ትንቢተ ኢሳይያስ 54፡13
7.     ፈቃዱን የሚከተል ሰው የእግዚአብሄር ጥበብ ይሰጠዋል፡፡
የእግዚአብሄር ጥበብ የሚሰራው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለሚከተል ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ የሚደግፈው እግዚአብሄርን ፈቃድ የሚኖርን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር ስንፈተን መውጫውን የሚያዘጋጀው በፈቃዱ ወሰጥ ስንኖር ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስንከተል የእግዚአብሄር ጥበብ ሙሉ ለሙሉ ከእኛ ጋር ለእኛ ጥቅምና ማሸነፍ ይሰራል፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። የያዕቆብ መልእክት 1፡2-3፣5
8.     ፈቃዱን የሚከተል ሰው ብቻ ነው ዘላለለማዊ ቅርስን የሚተወው፡፡ ጊዜያዊና ምድራዊ ነገርን አድርገን ህይታችንን በከንቱ ማሳለፍ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ዘላለም የሚያስተጋባ ዘላቂን ነገርን የምናደርገው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስናደርግ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካላደረገና ለሚጠፋ መብል ለከንቱነት እንሰራለን፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። የዮሐንስ ወንጌል 6፡27
9.     የእግዚአብሄርን ህልውና የምናረጋገጥው በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ በመኖር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር አብሮን ካለ ደግሞ ምንም ሌላ ነገር አያስፈልገንም፡፡
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የዮሐንስ ወንጌል 14፡23
10.    አክሊልን የምንሸለመው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስንከተል ብቻ ነው፡፡
በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡12
ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡12-15
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ህልውና #አብሮነት #ደስታ #እርካታ #ሰላም #ጥበቃ #ቅርስ #ሽልማት #አክሊል #ፀሎት #ልመና #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ምስጋና

No comments:

Post a Comment