Popular Posts

Sunday, April 2, 2017

የእግዚአብሔርን ፀጋ የምንጥልባቸው አራቱ መንገዶች

እኛን ያቆመን የእግዚአብሄር ፀጋ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ፀጋ ውጭ እኛ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ሁሉ በእግዚአብሄር ሃይልና ፀጋ ስለሆነ በክርስትና ታላቁ ሰው ማለት ነው የሚችለው የሆንኩትን የሆንኩት በእግዚአብሄር ፀጋ ነው ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡10
የእግዚአብሄርን ፀጋ ስንጥል ማደግ እናቆማለን፡፡ የእግዚአብሄርን ፀጋ ከጣልን መውደቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ፀጋን የምንጥልበትና ማደግ የምናቆምበት ብሎም በክርስትና የምንወድቅበት ሶስት ዋና ዋና መንገዶች አሉ፡፡
የእግዚአብሄርን ፀጋ የምናጣበት ሃይል አልባ የሚያደርጉን አራቱ መንገዶች
ትህትናን መጣል  
ሰው ትህትናን ከጣለ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንደሚወድቅ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ከሰጠው ደረጃ በላይ ራሱን ከፍ አድርጎ ሲያይ ከእግዚአብሄር ጋር ይተላለፋል፡፡ እግዚአብሄር ፀጋን መስጠትና ማንሳት ከፍ ማድረግ እየፈለገ በራሱ ነገሮችን ማደርግ እንደሚችል የሚያስበውን ትእቢተኛን ሰው ግን ከመቃወም ውጭ ምንም ሊያደርገው አይችልም፡፡  
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። ያዕቆብ 4፡6
እውቀትን መጣል
ሰው ከመሬት ተነስቶ አውቆ የጨረሰ ከመሰለው በህይወቱ ማደግና መለወጥ አቁሟል ማለት ነው፡፡ ይህ ሰው ለአዲስ ተግዳሮት በእውቀት ራሱን ካላስታጠቀ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ሰው ያወቀና የጨረሰ ከመሰለው እጅግ አሰቃቂ ነው፡፡
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1-2
ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ ሆሴዕ 4፡6
በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2
እምነትን መጣል
ሰው በእግዚአብሄር ላይ መደገፍን ትቶ በራሱ ስራ ላይ ሲደገፍ ከእግዚአብሄር ፀጋ ይጎድላል፡፡ ሰው ለመዳንም ሆነ ከዳነ በኋላ ለመቀደስ ፣ ለእግዚአብሄር መንግስት ለመስራትና እግዚአብሄርን ለማስደሰት በራሱ ጉልበትና ቅልጥፍና ላይ ሲደገፍ ከእግዚአብሄር ፀጋ ይጎድላል፡፡
በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ገላትያ 5፡4
ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡30-31
ምስጋናን መጣል
ሰው ምንም ከማይወጣለት መልካም አምላክ ጋር እየኖረ ካጉረመረመና ማመስገን ካቃተው ከእግዚአብሄር ፀጋ ይጎድላል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አሰራር ላይ አቃቂር ማውጣት ከቻለ የሆነ የሳተው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር በላይ የሚያውቅ ከመሰለው የሆነ የተዛባ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር አሰራር ካልታመነ ከእግዚአብሄር ጋር በየዋህነት መኖር ፣ ራሱን መስጠት ፣ ለእግዚአብሄር በየዋህነት መስራትና ፍሬያማ መሆን ያቅተዋል፡፡   
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ማቴዎስ 25፡24-25
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት

1 comment:

  1. this is really wonderful thought. Please try to develop to book. Blessings. For more info. Use 0913189037 Alex.

    ReplyDelete