እግዚአብሄር ልጅ ስለሆንን ብቻ ለኑሮ የሚያስፈልገንን
ነገር ይሰጠናል፡፡ በክርስትና ህይወታቸን ስኬታማ ለመሆን ለዚህ እውነት እግዚአብሄር አይናችንን ሊከፍት ይገባል፡፡ ይህን ካልተረዳን
የእስራኤል ህዝብ የሴይርን ተራራ እንደዞረ እኛም ካለውጤት ህይወታችንን እንፈጃለን፡፡
አንድ ልጅ አባቱ የሚንከባከበው የሚያስፈልገውን
ነገር ሁሉ የሚያሟላለት ስራ ስለሰራ ፣ ምርታማ ስለሆነና ገንዘብ ስለሚያመጣ አይደለም፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ስለተወለደ ልጅ ስለሆነ
ብቻ ከተወለደ ቀን ጀምሮ አባት ልጁን የመንከባከብ ግዴታ አለበት፡፡
አባት ልጅን የሚንከባከበው በቤተሰቡ ውስጥ ስለተወለደ
ብቻ ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ የተወለደን ልጅ መንከባከብ የአባት ግዴታ ነው፡፡ የአባት አቅርቦት የልጅነት መብት ነው፡፡ ዛሬ ስራ
ይህን ያህል ሰአት ሰርቷል ብሎ አይደለም አባት ሃላፊነቱን የሚወጣው፡፡ ልጅም በማለዳ ወደ ስራ ሄዶ አይደለም ከአባቱ ምሳ የሚጠይቀው፡፡
እንዲሁም እግዚአብሄር የሚንከባከበን የሚያስፈልገንን
ነገር የሚያሟላልን ልጅ ስለሆንን ብቻ እንጂ ስራ ስለሰራን ስላልሰራን አይደለም፡፡
እግዚአብሄር እንድንሰራ የሚፈልገው ስራ የምድር
ጨው የመሆንና የአለም ብርሃን የመሆን ጥሪ ነው፡፡ በምድር ላይ ያለነው ለመብላትና ለመጠጣት ለመልበስ አይደለም፡፡ በምድር ላይ
ያለነው ከመብላትና ከመልበስ በላይ ለከበረ ስራ ነው፡፡ በጨለማ ላሉት ብርሃን መንገዱን እነዲያዩ ብርሃን አነሆናቸዋለን፡፡
እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ማቴዎስ 5፡13-14
የእኛ ስራ ክህንነት ነው፡፡
ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን
የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤2ኛ ቆሮንቶስ 5፡18
የመጀመሪያው ጥሪያችን መልክተኝነት ነው፡፡ የክርስቶስ
አምባሳደሮች ነን፡፡ በምድር ያለነው እግዚአብሄርን እና መንግስቱን ለመወከል ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መልካም ለሰዎች እናሳያለን፡፡
የእግዚአብሄርን መልካምነትና መሃሪነት በድርጊታችንና በቃላችን እናንፀባርቃለን፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16
እግዚአብሄርን በመፍራት ሰዎች እግዚአብሄርን እንዲፈሩ
እናበረታቸዋለን፡፡ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር የሚታረቁበትን የመዳን እውቀት ቃል እንሰጣቸዋለን፡፡ እኛ ከሃጢያት የዳንን ሰው ከሃጢያት
መዳን እንደሚችል ሞዴል እንሆናቸዋለን፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡20
ዋናው ስራችንና ቅጥራችን ክህንነት ነው፡፡ የሙሉ
ጊዜ ካህናት ነን፡፡ በገንዘብ የተገዙትን ክርስቲያን ባሪያዎች እንኳን ጌታን የሚያገለግሉ እንደሆኑና ብድራትን የሚከፍላው የቀጠራቸው
እግዚአብሄር እንደሆነ ጥሪያቸውም ክህንነት እንደሆነ ሐዋሪያው ጳውሎስ የሚያስረዳቸው፡፡
ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። ቆላስይስ 3፡24
የክህነነት ስራችንን እየሰራን ግን ሌሎች የሙያ
ስራዎችን በመስራት ገንዘብን እናገኛለን፡፡ እግረመንገዳችንን በምንሰራው ስራ ጌታ በምድር ላይ የሚያስፈልገንን ነገር እንድናሟላ
ይረዳናል፡፡ እግዚአብሄር ስራ እንድንሰራ የሚፈልገው ስራ ካልሰጠሁት ምን ይውጠዋል ብሎ አይደለም፡፡ ስራ ካልሰራ እኔ ከየት አምጥቼ
እንከባከበዋለሁ ብሎም አይደለም፡፡ ይህ የምድራዊ ስራ ቢኖርም ባይኖርም ጌታ እኛን ይንከባከበናል ያኖረናል፡፡ እግዚአብሄር የሚንከባከበን
ሌላ ስራ ስለሰራን ስላልሰራን ሳይሆን ልጅ ስለሆንን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሰዎች ስለሚበሉት ፣ ስለሚጠጡትና ስለሚለብሱት አንዳይጨነቁ
ጌታ ኢየሱስ ያስተማረው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን?
ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ
የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
በእግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ ስራ መቀጠር መብላት
መጠጣት መልበስ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም፡፡ በክርስትና የመጀመሪያው ጥሪያችን ክህንነት ነው፡፡ ሌላው ስራ ከሙሉ ጊዜ የክህንነት አገልግሎታችን
ጎን ለጎን የምናደርገው ነው፡፡ በክርስትና ካለሌላ ሙያ መኖር እንችላለን ካለ ክህንነት ግን መኖር አንችልም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ልጅነት #አቅርቦት #አማርኛ
#ስብከት #መዳን
#መፅሃፍቅዱስ #ቃል
#ጥሪ #ክህንነት
#ስራ #መልክተኛ
#አምባሳደር #ብርሃን #ጨው #ልጅነት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment