Popular Posts

Follow by Email

Saturday, April 29, 2017

ገዳም አይቀድስም ከተማ አያረክስም

ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረን ለእግዚአብሄርና ለእግዚአብሄር ብቻ ለመኖር ከመፈለጋችን የተነሳ ከከተማ ወጥተን የሆነ ቦታ ሄደን ብቻችንን ብንሆን እንመኛለን፡፡ በአካባቢያችን ያለውን የሰውን የአለማዊነት ምኞት በመፀየፍ ነፍሳችን ትጨነቃለች፡፡
ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና፡፡ 2ኛ ጴጥሮስ 2፡7-8
ችግሩ ግን ሃጢያት ያለው በከተማ ውስጥ አይደለም፡፡ ቅድስም ያለው በገዳም ውስጥ አይደለም፡፡ ሃጢያት ያለው በሰው ልብ ውስጥ ነው፡፡
ለውጭው ነገራቸው እጅግ የሚጨነቁትንና ውጫዊ ነገር ያረክሰናል ብለው ለሚያስቡት ፈሪሳዊያን ኢየሱስ የውጭ ነገር ሰውን እንደማያረክስ ሰውን የሚያረክሰው የሰው የልብ ሃሳብ እንደሆነ ያስተምራቸዋል፡፡ ክፉ ሃሳብ የሚመጣው ከትልቅ ከተማ ውስጥ አይደለም፡፡ ክፉ ሃሳብ የሚወጣው ከሰው ልብ ውስጥ ነው፡፡  
ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ማቴዎስ 15፡18-19
ስለዚህ ኢየሱስ በልባቸው እንዲቀደሱ ቅድስና በቦታ ለውጥ ሳይሆን ቅድስና በልብ ለውጥ እንደሚመጣ ሲያስተምራቸው እንመለከታለን፡፡፡ ሰው ልቡን ከክፉ ሃሳብ ካጠራ አለሙን ከተማም ይሁን ገጠር ያጠራዋል፡፡ ሰው የልቡ ሃሳብ ከክፋት ካልጠራ ግን ከተማም ይኑር ገዳምም ይግባ ዋጋ ከአለም እርኩሰት መለየት አይችልም፡፡   
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። ማቴዎስ 23፡25-26
ስለዚህ ነው ሰው አለምን ከመምሰል የሚድነው ገዳም በመኖር ወይም ከተማ ባለመኖር ሳይሆን ሰው አለምን የማይመስለው በአስተሳሰብ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ሰው በእግዚአብሄር ቃል አስተሳሰብ በልቡ መታደስ ካለተለወጠ የትም የትም ቢኖር አለማዊ አስተሳሰብ ይኖረዋል፡፡ ሰው ደግሞ በእግዚአብሄር ቃል አስተሳሰቡ ከተለወጠ ቅልጥ ያለው መሃል ከተማ እየኖረ አለምን ሳይመስል በቅድስና እግዚአብሄርን አስከብሮ ይኖራል፡፡
ኢየሱስ በቃሉ አማካኝነት እዚሁ በአለም እያለን እንድንቀደስ እንጂ ከአለም እንዲያወጣን አልፀለየም ፡፡  
ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ዮሃንስ 17፡15-17
አለምም የሚባለው የሃጢያተኝነት ምኞት እንጂ ከተማ አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #አእምሮ #ልብ #ገዳም #አለም #እግዚአብሔርንመፍራት #ጥበብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment