ሰይጣን የሰው ልጅ ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን የሚመጣው ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ከመስረቅ ከማረድ እና ከማጥፋት ውጭ ሌላ ተልእኮ የለውም፡፡
ሰይጣን በማይታዘዙት ልጆች ላይ የጥፋት አላማውን ይሰራል፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ኤፌሶን 2፡1-2
እኛ ግን ከጨለማው ስልጣን ስለዳንንና ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት ስለፈለስን በእኛ ላይ ስልጣን የለውም፡፡
እኛን የሚዋጋን በሃሳብ ነው፡፡ ሰይጣን ክፉ ሃሳብን ወደ አእምሮዋችን ይልካል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነውን ሃሳቡን ከተቀበልነው አላማውን ያስፈፅምብናል፡፡ ካልተቀበልነው ግን ሃሳቡና አላማው በውስጣችን ይሞታል፡፡
ሰው ሃሳቡ ከተበላሸ ህይወቱ ይበላሻል፡፡ ሰው በሃሳቡ የሃጢያትን ሃሳብ ካስተናገደ ሰው በህይወቱ የሃጢያትን ህይወት ያደርገዋል፡፡ ሰው ሃሳቡን ከሃጢያት ከጠበቀ ህይወቱን በንፅህና ይጨብቃል፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡3
ሰው በአስተሳሰብ ህይወቱ እግዚአብሄርን ከፈራ ከሃጢያት የነፃ ህይወት ይኖረዋል፡፡ ሰው አያየኝም ብሎ የሃጢያትን ሃሳብ የሚያስተናግድ ሰው ሃጢያትን ሲያደርገው ይገኛል፡፡
ሰው አስተሳሰቡ ቅጥ ያጣ መሆን የለበትም፡፡ ሰው አስተሳሰቡ ስርአት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡ ህይወታችንን በንፅህና ለመጠበቅ ማሰብ የሚገባን ነገሮች አሉ ማሰብ የማይገባን ነገሮች ደግሞ አሉ፡፡ ወደ አእምሮዋችን የመጣውን ሃሳብ ሁሉ አናስብም፡፡ በአእምሮዋችን ውስጥ እንዲቆይ የምንፈቅድለት ሃሳብ አለ፡፡ ከአእምሮዋችን በፍጥነት አሽቀንጥረን የምንጥለው ሃሳብ አለ፡፡
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ፊልጵስዩስ 4፡8
አእምሮዋችንን ከክፉ ሃሳብ ወረራ ከጠበቅን ህይወታችንን ከሰይጣን ጥቃት እንጠብቃለን፡፡
የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡5
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ሰይጣን #ዲያብሎስን #ሽንገላ #ሃሳብ #ንፅህና #ምኞት #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ስብከት #እምነት #ነፃነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment