Popular Posts

Thursday, April 6, 2017

የበይ ተመልካች

እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ኢሳይያስ 55፡1-2
እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡ እግዚአብሄር ለሁላችንም እኩል እድል ሰጥቶናል፡፡ እስኪ ግን እነዚህን ሁለት አይነት ሰዎች እንመልከት፡፡ እኛንስ ራሳችንን ከሁለቱ አይነት ሰዎች በየትኛው ነው የምንመድበው?
አንዱ በገና ኢየሱስ ተወለደ ፣ በስቅለት ኢየሱስ ሞተ ፣ በትንሳኤ ደግሞ ኢየሱስ ከሞት ተነሳ እያለ እንደ ታሪክ በአመት ሶስቴ እያስታወሰ ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ ከዚህ ከኢየሱስ ከከፈለው የሃጢያት እዳ ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ በመሆን በአመት 365 ቀን ከሃጢያት እስራት ነፃ ወጥቶ ይኖራል፡፡
አንዱ ለሁሉ ሰው በተገለጠው በዚህ የነፃ ስጦታ ተጠቃሚ በመሆን የእግዚአብሄር ልጅ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ኢየሱስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ እያለ እንደታሪክ እያወራ ከዚህ ነፃ ስጦታ አንዳች ተጠቃሚ ሳይሆን የበይ ተመልካች ይሆናል፡፡
አንዱ በዚህ በሚያስችል የእግዚአብሄር ፀጋ ስጦታ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት በመካድ ከሃጢያት የበላይነትን ኑሮ ያጣጥማል፡፡ ሌላው ደግሞ ነፃነት በኢየሱስ ተዘጋጅቶ እያለ በሃጢያት እስራት ተተብትቦ የሃጢያት መጫወቻ ሆኖ ዘመኑን ይፈጃል፡፡ አንዱ በእግዚአብሄር ፀጋ ራስን የመግዛትን ፍሬ በህይወቱ ይጠግባል፡፡ ሌላው ደግሞ በእግዚአብሄር ፀጋ ራሱን እንዴት እንደሚገዛ ባለማወቅ የሰይጣን ጥቃት ሰለባ ሆኖ ይኖራል፡፡  
አንዱ እግዚአብሄርን በመምሰል እግዚአብሄርን ደስ እያሰኘ በእግዚአብሄርም ደስ እየተሰኘ ይኖራል፡፡ ሌላው ደግሞ እግዚአብሄርን መምሰል እንደ ሰማይ ርቆበት ተስፋ ይቆርጣል፡፡  
እግዚአብሄር ግን ለሁሉም ግብዣን አዘጋጅቷል፡፡ እግዚአብሄር ልዩ ልጅ የለውም፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡
ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡11-14
ኢየሱስ ስለሃጢያትችን በመሞቱና የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ በመክፈሉ ሁላችንም በነፃነት መኖር እንችላለን፡፡ ሰዎችን ከባርነት ቀንበርት የሚያድን የእግዚአብሄር ፀጋ ለሁሉም ሰው ተዘጋጅቷል፡፡
አንዱ ኢየሱስ የሞተበትን ምክኒያት ሙሉ በሙሉ በመረዳት 365 ቀን የበረከቱ ተካፋይ ሲሆን ሌላው ግን እንደ ባህል በአመት አንዴ በማስታወስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞት ዋጋ የከፈለበት አላማ በህየወቱ ሳይፈፀም ይቀራል፡፡  
መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአመፃ ሁሉ እንዲቤዠን ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ አሁንም ከሃጢያት ካልዳንክ ኢየሱስ የሞተበት አላማ በህይወትህ ገና አልተፈፀመም፡፡  
በአሉን ልታከብር ስትዘጋጅ እኔስ የኢየሱስ ሞት ተጠቃሚ ሆኛለሁ ወይስ እንደ ወግ በአመት አንዴ ነው የማስታውሰው ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ ኢየሱስ የሞተበት አላማ በህይወትህ ካልተፈፀመ በአመት አንዴ በአሉን ማስታወስህ የበይ ተመልካች ወይም ቲፎዞ እንጂ ሌላ ምንም አያደርግህም፡፡  
መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡14 
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መቤትዠ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እውቀት #ምስጋና #ትህትና #ልብ #እምነት

No comments:

Post a Comment