እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር እርሱን የመሰለ እንደ እርሱ አድጎ ምድርን እንዲያስተዳድራት ሰውን በመኩና በአምሳሉ ፈጠረ፡፡
አዳም ሃጥያትን በመስራቱ የተነሳና አታድርግ የተባለውን ያንኑ ነገር በማድረግ በእግዚአብሄር ላይ ስላመፀ የእግዚአብሄርን መልክ አጣው፡፡ እግዚአብሄርን መምሰሉ በሃጢያት ምክኒያት ተበላሸ፡፡
እግዚአብሄር በሰው ህይወት ላይ መልኩን የመመለስ አላማውን አልቀየረውም፡፡ አሁንም የእግዚአብሄር አላማ ሰውን ወደ እግዚአብሄርን መምሰል መመለስ ነው፡፡
የእግዚአብሄር በሰዎች ላይ ያለው ብቸኛ አላማ ሰው ተመልሶ እግዚአብሄርን መስሎ እንዲኖር ነው፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ሰዎች ከሃጢያት ባርነት ነፃ ወጥተው እግዚአብሄርን የመምሰል ነፃነት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡
ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ ቲቶ 2፡12-13
ብዙ ሰዎች ለብዙ አይነት ጥቅም ህይወታችውን ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን ከመምሰል በላይ ጥቅምና ሐብት የለም፡፡ እግዚአብሄርንም ከሁሉም ነገራችን በላይ እርሱን መምሰላችን ያስደስተዋል፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6
ሰይጣን በምንም ብልፅግናችን ፊት ለፊት ላይላተመን ይችላል እግዚአብሄርን መልክ በእኛ ውስጥ ሲበዛ ሲያይ ግን ያንገሸግሸዋል፡፡ ሰይጣንም ምንም ስኬታችን ላያስደነግጠው ይችላል እግዚአብሄርን መምሰላችንን ግን ሊቋቋመው አይችልም፡፡ ስለዚህ ነው የእግዚአብሄር መልክ የሚታይባቸውን ሰዎች የተለያየ ዘዴ ተጠቅሞ የሚያሳድደው፡፡
በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡12
የክርስትና ትርፋችን እግዚአብሄርን መምሰል መሆኑን መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ እግዚአብሄርን ከመምሰል በላይ ክብር የለም፡፡
እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16
ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ ስለሰጠኸኝ ቃል አመሰግንሃለሁ፡፡ ቃልህን ሰምቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በህይወቴ የአንተ አላማ የራስህን ምስል ማየት መሆኑን መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሆይ ቃልህን በመስማትና በመታዘዝ አንተን ለመምሰል ራሴን እሰጣለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ሰዎች የሚከተሉዋቸውን አንተን እንድመስል የማይረዱትን ነገሮች ሁሉ እንቃለሁ፡፡ አንተን እንድመስል የሚያደርጉትን ነገሮች ሁሉ ዋጋ ቢያስከፍለኝም ለማድርግ ራሴን እሰጣለሁ፡፡ ጌታ ሆይ አንተን እንድመስል እየሰራኽኝ ስለሆነ አመሰግንሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እግዚአብሔር #ጌታ #መከተል #መከተል #መምሰል #እግዚአብሔርንመምሰል #ቃል #ተማሪ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ደቀመዝሙር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ነፍስንመካድ #መፅሃፍቅዱስ #ተከታይ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment