ኢየሱስ ለእኛ ሰው ሆኖ ወደምርድ ስለመጣ ፍፁም ምሳሌያችን ነው፡፡ ማንንም ባንከተል ኢየሱስን መከተል አለብን፡፡ ማንም ምንም የሚጎድለው ባህሪ ቢኖር ኢየሱስ በባህሪው ፍፁም ነው፡፡ ኢየሱስ ሙሉ ለሙሉ ልንከተለው የምንችለው አስተማማኝ ምሳሌያችን ነው፡፡
እኛም እንድንከተለው ከታዘዝነው የኢየሱስ ባህሪያት አንዱ ትህትናው ነው፡፡ ኢየሱስ ትሁት ነው፡፡ ከኢየሱስ ትህትና ብዙ ነገሮችን መማር እንችላለን፡፡
1. የኢየሱስ ትህትና የመነጨው ራሱን ከማወቁ ነው፡፡ ሰው ትሁት መሆን ካቃተው የበታችነት ስሜት እየተሰቃየ ነው ማለት ነው፡፡ ሰው የበታችነት ስሜት ካለበት ያንን ለማካካስ ራሱን ይኮፍሳል ትእቢተኛም ይሆናል፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለውን የክብር ቦታ የተረዳ ሰው ግን እርሱን ሊያዋርደው የሚችል ምንም ዝቅታ እንደሌለ ስለሚያምን ራሱን ማዋረድ አይቸግረውም፡፡ ስለማንነቱ እርግጠኛ ካልሆነ ሁልጊዜ በትእቢት ይነፋል፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሐንስ 13፡3-5
2. ትህትና ከላይ ከላይ የምናሳየው ሳይሆን የልብ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው በልቡ ትእቢተኛ ሆኖ በአንደበቱ የትህትና ቃሎችን ተለማምዶ ሊናገራቸው ይችላል፡፡ ሰው በልቡ ትእቢተኛ ሆኖ በአካሄዱ ትሁት ሊመስል ይችላል፡፡ እውነተኛው ትህትና የልብ ትህትና ነው፡፡ እወነተኛው ትህትና ማንም ሳይሰማን በምንናገረው ነገር ይታወቃል፡፡ የልብ ትህትና ማንም በማያየን ጊዜ በምናደርገው ነገር ይታያል፡፡
ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ማቴዎስ 11፡29
3. ትሁት ሰው ስለ ደህንነቱና ስለ ማግኘቱ በእግዚአብሄር ይታመናል፡፡ ትሁት ሰው ለመተው ለመልቀቅ ዝግጁ ነው፡፡ ትሁት ሰው የራሱ ክብር ሳይሆን የሌላውን ጥቅም ያስቀድማል፡፡ ትሁት በሚሰጠው በእግዚአብሄር ስለሚታመን ለማጣት ዝግጁ ነው፡፡ ትህትና የማይገባንን ሳይሆን የሚገባንን መተው ነው፡፡ ትህትና ንጉስ በአህያ ውርንጭላ ሲሄድ ነው፡፡
ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ማቴዎስ 21፡4-5
ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። ኢሳይያስ 53፡7
4. ትህትና እግዚአብሄርን ብቸኛ ምንጭ ከማድረግ ይመጣል፡፡ ትህትና በስሜት አለመመራት ነው፡፡ ትህትና ሃያልነት እንጂ ሽንፈት አይደለም፡፡ ትህትና ሃይልን ለክፋት ላለመጠቀም ከመወሰን ጥበብ ይመጣል፡፡
አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። ማቴዎስ 12፡19-20
5. ትህትና ሰዎችን አንድናከብር እንደ እግዚአብሄር ለሰዎች ታላቅ ዋጋ እንድንሰጥ ያደርገናል፡፡ ትህትና ሰዎችን ከመናቅ ትእቢት ነፃ ያወጣናል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3
6. ትሁት ሰው ልታይ ልታይ አይልም፡፡ ትሁት ሰው ራሱን ይደብቃል፡፡ ትሁት ሰው ለስሙ አይጋደልም፡፡ ኢየሱስ ሰዎችን ከፈወሰ በኋላ ለማንም አትንገሩ ይል ነበር፡፡ የኢየሱስ ትኩረት የሰዎች መጠቀም እንጂ የራሱ ስም ዝና አልነበረም፡፡
ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ፦ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው። ማቴዎስ 17፡9
7. ትሁት ሰው እግዚአብሄር በሌላው እንደሚጠቀም ያምናል፡፡ ትሁት ሰው ራሱን አንድ ለእናቱ (ሱፐር ስታር) አድርጎ አያይም፡፡ ትሁት ሰው ሌሎችን በማገልገል በማንሳትና በመጥቀም ይረካል፡፡
እርሱም፦ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ማቴዎስ 8፡26
8. ትሁት ሰው ያለው ነገር ሁሉ የእግዚአብሄር እንደሆነ ስለሚያምን ስለማጣት ምንም አይሰጋም፡፡ ትሁት ሰው ቀድሞ ራሱን ስላዋረደ ማንም ሊያዋርደው አይችልም፡፡ ትሁት ሰው ህይወቱን ቀለል ስላደረገና ውስብስብ የቅንጦትን ህይወት ስለሚሸሽ ለእግዚአብሄር የሚመች አገልጋይ ይሆናል፡፡
ኢየሱስም፦ ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ሉቃስ 9፡58
9. ትህትና ገመናን ይሸፍናል፡፡ ትህትና ከውድ ልብስ በላይ ሞገስ የሚሰጥ ልብስ ነው፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5
10. ትሁትና የእግዚአብሄርን መንፈስ ይስባል፡፡ ካለን ምንም ነገር በላይ ትህትናችን እግዚአብሄርን ይማርከዋል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። ኢሳይያስ 66፡1-2
11. እንደ ትህትና የተሻለ አስተማማኝ ዋስትና የለም፡፡ እግዚአብሄር ከትሁቱ ጋር ይወግናል፡፡ እግዚአብሄር ለተዋረደው ይዋጋል፡፡ እግዚአብሄር ለትሁታን ፀጋን ይሰጣል፡፡
ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ። ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው። ምሳሌ 22፡4
በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ምሳሌ 3፡34
12. ትህትና ከእግዚአብሄር የሆነን ክብር መቀበያ ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ ትህትና በህይወታችን እንዲሆንልን የምንፈልገውን ነገር መጠየቂያ መንገድ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ፊልጵስዩስ 2፡9
እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡6
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment