ፃድቃን ማናቸው የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ፅድቅ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡
ፅድቅ ካለፍርሃትና ካለበታችነት ስሜት በእግዚአብሄር ፊት መቆም ነው፡፡
ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ጋር ተጣልቷል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ ነው ፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒትት ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ተለያይቷል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ጠላት ነው፡፡ ፃዲቅ ማለት በክርስቶስ የመስቀል ሞትና ትንሳኤ ከእግዚአብሄር ጋር የታረቀና ካለሃፍረት ፣ካለበታችነት ስሜትና ካለፍርሃት በእግዚአብሄር ፊት በድፍረት የሚቆም ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ዕብራውያን 4፡16
ፅድቅ ማለት ተቀባይነት ማግኘት ማለት ነው፡፡
ፃድቃን ማለት ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሃጢያት እዳቸውን እንደከፈለ ስላመኑ በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት የእግዚአብሄር ልጆች የሆኑ ማለት ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐንስ 1፡12
ፅድቅ ማለት ተቀባይነት ያለው ፣ ንፁህና ትክክል ማለት ነው፡፡
ፃድቃን ማለት በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ምክኒያት ሃጢያታቸው ስለተደመሰሰላቸው ከዚህ በፊት ሃጢያት እንዳላደረጉ ተደርገው እንደንፁህ ሰው በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ማለት ነው፡፡ ፃድቃን ኢየሱስ የእነርሱንም ሃጢያት ወስዶ የእርሱን ፅድቅ የሰጣቸው ናቸው፡፡
እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21
ፅድቅ ማለት ፀደቀ ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ህይወትን መዝራት መለምለም ማለት ነው፡፡
በሃጢያት ምክኒያት ሁሉም ሰው በመንፈሱ ሙት ነው፡፡ በመንፈሱ ሙት የሆነው ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ስራ በኩል ህይወትን ሲያገኝ ህይወትን ዘራ ለመለመ ፀደቀ ይባላል፡፡
ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። ሮሜ ሰዎች 3፡23-24
ፅድቅ ማለት በእግዚአብሄር አሰራር ማመን ማለት ነው፡፡
ፃድቃን ማለት በእግዚአብሄር አሰራር የሚያምኑ አማኞች ማለት ነው፡፡ ፃድቃን ማለት ለመዳን ዘመናቸውን ሁሉ የሚሰሩ ማለት ሳይሆን ፃድቃን ማለት እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ የተቀበሉ ፣ ኢየሱስ በእነርሱ ምትክ በመስቀል ላይ እንደሞተና የሃጢያታቸውን እዳ ሁሉ እንደከፈለ የሚያምኑና የመዳንን ነፃ ስጦታ በእምነት የተቀበሉ ማለት ነው፡፡
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ኤፌሶን 2፡8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፃዲቅ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ፃድቃን #መዳን #ፀጋ #ህይወት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment