Popular Posts

Saturday, April 1, 2017

በፈተና ጊዜ መተው የሌለብን ስድስት ነገሮች

በክርስትና ሁልጊዜ የማሸነፉ ጥበብ በሚገጥመን ማንኛውም ፈተና ማድረግ የምንችለውን አድርገን ለእግዚአብሄር ፈንታ በመስጠቱ ላይ ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገር የእግዚአብሄርና የሰው የአጋርነት ስራ ነው፡፡ እኛ መስራት የማንችለው እግዚአብሄር የሚሰራልን ነገር አለ፡፡ እኛ ደግሞ የምንሰራው ነገር አለ፡፡ ታዲያ የእኛን ስራ ሰርተን ለእግዚአብሄር ፈንታ መስጠት ብልህነት ነው፡፡
ከመጣባቸው ከታላቅ መከራ የተነሳ ወደ እግዚአብሄር የጮሁና እግዚአብሄር በድንቅ የመለሰላቸው ሰዎች ምስክርነት የተሞላ መፅሃፍ ነው መፅሃፍ ቅዱስ፡፡  
በፈታኝ የውጥረት ወቅት ማድረግ የሌለብን ስድስት ነገሮች፡፡
1.      ፀሎትን አለመተው  
 እውነት ነው ሰው ወደ ውጥረት ከመግባቱና ፈተና ከመምጣቱ በፊት ነው ወደ ፈተና እንዳይገባ መፀለይ ያለበት፡፡ በሰላ ጊዜ የማይፀልይ ሰው ብርቱ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በፈተና ወቅት ለራስ ጊዜ መስጠት እና ወደ እግዚአብሄር መጮኽን መተው የለብንም፡፡ እግዚአብሄር የልብን ጩኸት ስለሚሰማ በራችንን ዘግተን የምንፀልይበትም እድሉን ባናገኝ ልባችንን ለእርዳታ ወደ እግዚአብሄር ማንሳት ይገባናል፡፡ መውጫ የሌለ በሚመስልበት ሁኔታ እግዚአብሄር መውጫውን በጥበብ አማካኝነት ያካፍለናል፡፡  
 ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6
 ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት . . . ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ያዕቆብ 1፡2-5
 2.     እረፍትን አለመተው - አለመጨነቅ
 ማድረግ የምንችለውንና ማድርግ የማንችለውን ለይተን ማወቅ በክርስትና ስኬታማ ያደርገናል፡፡ ሰው ማድረግ የሚችለውን አድርጎ ካላረፈና ለእግዚአብሄር ፈንታን ካልሰጠ እግዚአብሄር እንዳይሰራ ያደርገዋል፡፡ ሰው ማድረግ የሚችለውን ካደረገ በኋላ ማረፍ ይኖርበታል፡፡ የሚያስጨንቀንን ነገር ለእግዚአብሄር መስጠት መልሰንም አለመውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ እኛ ስናርፍና እድሉን ለእግዚአብሄር ስንሰጠው በነገራችን ላይ ይሰራል፡፡
 እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
 3.     ምስጋናን አለመተው
በውጥረትም ጊዜ እግዚአብሄር ከእኛ ምስጋናን ይጠብቃል፡፡ እንዲያውም እውነተኛ ትህትናችን የሚለካው በፈተና ጊዜ ስናመሰግነው ነው፡፡ እውነተኛ የምስጋና መስዋእት የሚባለው ላለማመስገን ብዙ ምክኒያቶች ያገኘን ሲመሰለን ያንን የስንፍና ሃሳብ ሁሉ አልፈን የምናመሰግነው ምስጋና ለየት ያለ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ የማጉረምረም ትምክታችንን ዋጥ አድርገን የምንሰጠው በቀላሉ ያልመጣ የምስጋና መስዋእት ነው፡፡
ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ መዝሙር 50፡14
 4.     እምነትን አለመጣል - ፍርሃትንና ጥርጥርን አለማስተናገድ
 እምነት ብቸኛው የማሸነፊያ መንገዳችን ሰለሆነ ውጥረቶች በህይወታችን የሚመጡት እምነታችንን ሊያስጥሉ ነው፡፡ እምነታችንን ካላስጣሉን ውጥረት አይሳካለትም አላማውም ተጨናግፏል፡፡ የውጥረት አላማው ፈተናውን ማግዘፍና እግዚአብሄርንም ማሳነስ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያሳስ ሃሳብ በልባችን አለመፍቀድ ውጥረትን በአሸናፊነት እንድናልፈው ይረዳናል፡፡ ፈተና በፍርሃት ከምነሄደው ጉዞ ካስቆመን ብቻ ነው ስኬታማ የሚሆነው፡፡ ጊዞዋችንን ከቀጠልን ወደፈተና ሳንገባ እናልፈዋለን፡፡   
 አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡28
 ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ፦ እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። ማርቆስ 5፡36
 5.     የወንድሞችን ህብረት አለመተው
 በውጥረትና በፈተና ጊዜ አብረውን ሊቆሙ የሚችሉትን የወንድሞችን ህብረት አለመተው ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ ወንድሞች በሚናገሩት ቃል የሚያስችልን ሃይል በፀጋ ያካፍሉናል፡፡  
 ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ኤፌሶን 4፡29
 በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ዕብራውያን 10፡25
 6.     ደስታን አለመተው
 በውጥረት ጊዜ ደስታን መተው አይገባንም፡፡ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ ያለውን የእግዚአብሄርን ቃል ትእዛዝ መተው የለብንም፡፡ ደስ ይበላችሁ ብሎ ካዘዘ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ደስታ የውሳኔ ጉዳይ እንጂ የስሜት ጉዳይ አይደለም፡፡ ደስ እንዳይለን ምንም ምክኒያት የለንም፡፡ እግዚአብሄር እረኛችን ነው የሚያሳጣንም የለም፡፡ አባታችን እግዚአብሄር ከመሆኑ በፊት ሁሉን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስደንቀው ነገር የለም፡፡ ፈተናው በእኛ ላይ የሚያራግፈው የማያስፈልገውን ነገር ብቻ እንጂ እኛን አያገኘንም፡፡ በፈተና ሙሉ የሚያደርገንና ወደሚቀጥለው ደረጃ የሚያሸጋግረን እድገት ስለሚመጣ ደስ ይበለን፡፡  
 ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። ያዕቆብ 1፡2-4
 ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ፈተና #ውጥረት #ፀሎት #ጥበብ #እምነት #ህብረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ደስታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምስጋና #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

No comments:

Post a Comment