Popular Posts

Saturday, October 5, 2019

ኢሬቻ ባህል ወይስ ሃይማኖት ?



ስለኢሬቻ በዓል የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ በአል ነው የሚሉ ወገኖች ይህንን ያሉበት ምክንያታቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ በአል ነው የሚሉ ወገኖች የኢሬቻ በአል የዋቄፈታ እምነት ተከታዮች የሚያከብሩት በአል ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡
የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ በአል አይደለም የሚሉም ምክኒያታቸውን የሚሰጡ ወገኖችም አሉ፡፡ የኢሬቻ በአል ብሄራዊ የምስጋና ቀን ነው እንጂ የዋቄፈታ እምነት ተከታዮች የሚያከብሩት በአል ብቻ አይደለም የሚሉ ወገኖችም አስታያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ስለዚህ የኢሬቻ በአል የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ሊያከብሩት የሚችሉት የምስጋና በአል እንደሆነ ምክኒያታቸውን ይሰጣሉ፡፡
የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ የኢሬቻ በአል ባህላዊ በአል ይሁን ሃይማኖታዊ በዚህ ላይ ምንም አስተያየት መስጠት አይችልም፡፡ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ የሰው ልጅ ጥናትን አንትሮፖሎጂ ስላላጠና በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አይሞክርም፡፡
ሰዎች ስለክርስትና ሃይማኖት ሳያውቁ አስተያየት መስጠታቸው እንደሚያሳስታቸው ሁሉ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ ስለህዝብ ጥናት ሳያጠና ኢሬቻ ሃይማኖት ነው ባህል የሚለውም አስተያየት ቢሰጥ ሌሎችን ሊያሳስት ይችላል፡፡ እውቀቱ ስለሌለው ከሚናገር ይልቅ ዝም ቢል ይበልጥ እንደምታከብሩት ያስባል፡፡
ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፥ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው። ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ፦ ባለ አእምሮ ነው ይባላል። መጽሐፈ ምሳሌ 1727-28
እውነት ነው አሁን አሁን እንደዚህ አይነት የህዝብ በአላት ከሃይማኖት በአልነታቸው አልፎ የብሄርትኝነት ስሜት መገለጫ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ አሁን አሁን እንደ እነዚህ አይነት የህዝብ በአላት የፖለቲካ ስሜትን መግለጫ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ሰው ብሄርተኝነቱንና የፖለቲካ ስሜቱን መግለፁ ምንም ችግር የለውም፡፡
ክርስትና የሌሎችን ባህል በማክበር ይታወቃል፡፡ ክርስትና የሌሎችን ቋንቋ በመቀበል ይታወቃል፡፡
ኢየሱስ የመጣው ለእስራኤላዊያን ብቻ አልነበረም፡፡ ኢየሱስ ለነገዶችና ለቋንቋዎች ሁሉ መጥቶዋል፡፡ ስለዚህ የሚገርመን በመጨረሻው ዘመን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የዳኑት ሰዎች የሚገኙት ከእስራኤል ነገድ ብቻ አደለም፡፡ በመጨረሻው ዘመን ብዙ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የተለያ ነገድ ያላቸው ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላም እንደሚኖሩ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡
ክርስትና የማንም ባህልና ነገድ ተቃዋሚ አይደለም፡፡ ክርስትና የሌላውን ነገድና ቋንቋ የመለወጥ እና አንድ የማድረግ አላማ የለውም፡፡ ክርስትና የሰዎች ልብ ለእግዚአብሄር የመለወጥ እና የማስገዛት እንጂ ሰዎችን ሁሉ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ነገድ የማድረግ አላማ ግብም የለውም፡፡
ክርስትና አላማው በሃጢያት ምክንያት ከእግዚአብሄር የተለያዩ ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ስራ ከእግዚአብሄር ጋር እንዲታረቁና የእግዚአብሄር ሴትና ወንድ ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ 
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። የዮሐንስ ወንጌል 111-13
ኢየሱስ በምድር ላይ ሰመላስ ፈሪሳዊያኑን ስለወጋችሁ የእግዚአብሄርን ቃል ትሽራላቸሁ ብሎ ገስፆዋቸዋል፡፡
ባህልና ክርስትና አብረው የሚሄዱበት ብዙ አጋጣሚዎች አለ፡፡ ባህልና ክርስትና አብረው የማይሄዱበት ጊዜ ሲያጋጥም ስለ ክርስትና ባህልን መተው ግድ ይላል፡፡ ስለክርስቶስ ብለን ማንኛውንም እንደእግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ባህል ለመተው ዝግጁ ነን፡፡
ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። የሉቃስ ወንጌል 1426
ነገር ግን ባህልና የክርስትና ሃይማኖት ድንበራቸው እስከማይለይ ድረስ መቀላቀል የለባቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡  
እኔ ግን እኔ ከተረዳሁት የክርስትና እምነት አንፃር የኢሬቻ በአል ባህልነት እስከምን ድረስ እንደሆነ እና የኢሬቻ በአል ከምን ሲያልፍ  እንደሚሳሳት ከማውቃት እውቀት በዚህች አጭር ፅሁፍ ከእግዚአብሄር ቃል ላካፍል ወደድኩ፡፡
1.            ኢሬቻ የምስጋና ቀን ከሆነ ምንም ችግር የለውም
ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች እውነት ኢሬቻ ከምንም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የተለየ የምስጋና ቀን ከሆነ እሰየው የሚያስብል ልምምድ ነው፡፡ በኢሬቻ ከባህል የተለየ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መካተት ግን በእሳት እንደመጫወት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ማመስገኑ መልካም ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ማመስገኑ የሚወጣለት ምንም ነገር የለም፡፡
እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤ መዝሙረ ዳዊት 921
ነገር ግን እግዚአብሄርን ከማመስገን የሚቀድም በጣም እስቸኳይ ነገር አለ፡፡
በሃጢያት ምክንያት ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ተጣልቷል፡፡ ሰው በሃጢያቱ ምክንያት ከእግዚአብሄር ክብር የተለየ በመንፈስ ሙት ነው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ጋር የነበረው የአባትና የልጅ ግንኙነቱ ተቋርጧል፡፡
ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ኦሪት ዘፍጥረት 217
ሰው እግዚአብሄርን ከማመስገኑ በፊት ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ አለበት፡፡ በክርስቶስ ከእግዚአብሄ ጋር ያልታረቀ ሰው ከሰይጣን ጥቃት ስር ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ለማመስገን ከተያዘበት ከሰይጣን ስልጣን ስር ማምለጥ አለበት፡፡
በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 21-2
ሰው እግዚአብሄርን ከማመስገኑ በፊት የሚያመሰግነውን እግዚአብሄርን ማወቅ አለበት፡፡ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው እግዚአብሄር ደግሞ ራሱን የገለፀው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ጋር ተጣልቷል፡፡ ሰው ስለሃጢያቱ በመስቀል ላይ የሞተውን ኢየሱስን ካልተቀበለ በስተቀር ለዘላለም ከእግዚእብሄር ይለያል፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። የዮሐንስ ወንጌል 316
እግዚአብሄር ስለሃጢያቱ ዋጋን እንዲከፍል ወደምድር የላከውን ኢየሱስን ካልተቀበለ የእግዚአብሄር ፍርድ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ህይወትን አያየም፡፡ 
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 336
2.            ሁሉም ሰው እግዚአብሄርን አያመልክም
አንዳንድ ሰዎች ሁሉም ሰው እግዚአብሄርን ነው የሚያመልከው ይላሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሁሉም መንገድ ወደ እግዚአብሄር ያደርሳል ብለው የአጋንንትን ትምህርት ሰምተው ውሸትን ያምናሉ፡፡ ሁሉም መንገድ ወደ እግዚአብሄር አያደርስም፡፡ ወደ እግዚአብሄር የሚያደርሰው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። የዮሐንስ ወንጌል 146
ሰው እግዚአብሄርን ከማመስገኑ በፊት መንገድና ህይወት እውነት የሆነውን ኢየሱስን መቀበል ግዴታ አለበት፡፡ ሰው መንገድ በሆነው በኢየሱስ ብቻ ወደ እግዚአብሄር ይደርሳል፡፡ ሰው ህይወት የሆነውን ኢየሱስን ሲቀበል ብቻ ከሞት ወደ ህይወት በመሸጋገር የዘላለም ህይወት ያገኛል፡፡ ሰው እውነት የሆነውን ኢየሱስን በመቀበል ብቻ ከስህተት ይድናል ከእግዚአብሄር ሃሳብ ጋር ይገናኛል፡፡ 
3.            ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ነገር ሁሉ ከእግዚአብሄር አይደለም
ብዙ ሰዎች ከተፈጥሮ በላይ የሆነን ነገር ሲያዩ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሄር ያደረገው ይመስላቸዋል፡፡
የእስራኤልን ህዝብ ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዲያወጣ እግዚአብሄር ሙሴን በድንቅና በተአምራት ሲልከው በግብፅ የነበሩ መተተኞችን ጠንቋዮች እና አስማተኞች ከተፈጥሮ በላይ በሆነ ድንቅ የራሳቸውን ሃይል አሳይተው ነበር፡፡ ከተፈጥሮ ስራ በላይ የሆነ ነገር ሁሉ እግዚአብሄር አይደለም፡፡
ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በባሮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነች። ፈርዖንም ጠቢባንንና መተተኞችን ጠራ፤ የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ ደግሞ አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች። ኦሪት ዘጸአት 710-12
4.            መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሄር አይደለም
በአለም ላይ ያለው ሁለት አይነት መንፈስ ብቻ ነው፡፡ ከሁለቱ አይነት መንፈሶች የተለየ ገለልተኛ መንፈስ የለም፡፡ የክርስቶስ መንፈስ አለ፡፡ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ አለ፡፡ እውነተኛ መንፈስ አለ፡፡ ሃሰተኛ መንፈስ አለ፡፡ የክርስቶስን መንፈስ ካልተከተልን ወደድንም ጠላንም የምንከተለው የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስን ነው፡፡
ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 1 የዮሐንስ መልእክት 41-3
5.            ስለሰዎች በመፀለይ
እውነትን የተረዳን ሁላችን ለሰዎች ሁሉ መፀለይና መማለድ ይጠበቅብናል፡፡ ሰው መቼም አሁን ልሳሳት ብሎ አይሳሳትም፡፡ አንድን ህዝብ በአጠቃላይ መናቅ መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ የማንወደውን ህዝብ ማገልገል እንችልም፡፡ የማንወደውንና የማናዝልትን ህዝብ ለማልገል እግዚአብሄር አይጠቀምብንም፡፡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን ስለክልሉ ህዝብ ብሎም ስለሃገሩ ለመፀለይ እድሉን መጠቀም ይኖርብናል፡፡
ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።  የማቴዎስ ወንጌል 936
እኛ እውነትን የምናውቅ የምናውቀውን በትጋት ማካፈልና ስለሌሎች መዳን መፀለይ ግዴታ አለብን፡፡ 
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1 ወደ ጢሞቴዎስ 21-4
ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። ወደ ሮሜ ሰዎች 91-2
በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። 1 የጴጥሮስ መልእክት 315
6.            የሰይጣን ስራ ማፍረስ
ሰዎች ከእግዚአብሄር ህይወት ቢርቁ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ሰይጣን እንጂ ሰው አይደለም፡፡ ሰይጣን የሰው ጠላት ነው፡፡ የሰይጣን አላማ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ከዚህ ሌላ ምንም አላማ የለውም፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 1010
ኢየሱስም የተገለጠው የዲያቢሎስን ስራ እንዲያፈርስ ነው፡፡
ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። 1 የዮሐንስ መልእክት 39
መፅሃፍ ቅዱስ ዲያብሎስን ተቃወሙት ከእናንትም ይሸሻል እንደሚል ሰይጣን የሰዎችን ህይወት እንዳያጠፋ እንዳይሰርቅና እንዳያጠፋ ልንቃወመው ይገባል፡፡ ጦርነታቸን ከሰው ልጆች ጋር አይደለም፡፡ ጦርነታችን የሰው ልጆችን አሳሳቶ ወደሲኦል ሊወስድ ከሚሰራው ከሰይጣን ጋር ነው እንጂ፡፡
በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥  2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 103-5
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መንፈስቅዱስ #ፈትኑ #ባህል #ሃይማኖት #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #እርኩስመንፈስ #ሰይጣን #ኢሬቻ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ኦሮሞ #ዋቄፈታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment